1 Thessalonians (Amharic)

1 Thessalonians (Amharic)

1

1:1b.1TH.001.001ጳውሎስና ስልዋኖስ ጢሞቴዎስም፥ በእግዚአብሔር አብ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም ወደምትሆን ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች ቤተ ክርስቲያን፤ ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስም ጸጋ ሰላምም ለእናንተ ይሁን።

1:2b.1TH.001.002በጸሎታችን ጊዜ ስለ እናንተ ስናሳስብ፥ የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥ እግዚአብሔርን ሁል ጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤

1:4b.1TH.001.004በእግዚአብሔር የምትወደዱ ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ተመረጣችሁ አውቀናልና።

1:5b.1TH.001.005ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣምና፤ በእናንተ ዘንድ ስለ እናንተ እንዴት እንደ ነበርን ታውቃላችሁ።

1:6b.1TH.001.006ደግሞ እናንተ ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር ተቀብላችሁ፥ እኛንና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፤

1:7b.1TH.001.007ስለዚህም በመቄዶንያና በአካይያ ላሉት ምእመናን ሁሉ ምሳሌ ሆናችሁላቸው።

1:8b.1TH.001.008ከእናንተ ወጥቶ የጌታ ቃል በመቄዶንያና በአካይያ ብቻ አልተሰማምና፥ ነገር ግን ምንም እንድንናገር እስከማያስፈልግ ድረስ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚሆን እምነታችሁ በሁሉ ስፍራ ተወርቶአል።

1:9b.1TH.001.009እነርሱ ራሳቸው ወደ እናንተ መግባታችን እንዴት እንደነበረ ስለ እኛ ይናገራሉና፤ ለሕያውና ለእውነተኛ አምላክም ታገለግሉ ዘንድ፥ ከሙታንም ያስነሳውን ልጁን እርሱንም ኢየሱስን ከሚመጣው ቍጣ የሚያድነንን ከሰማይ ትጠብቁ ዘንድ፥ ከጣዖቶች ወደ እግዚአብሔር እንዴት ዘወር እንዳላችሁ ይናገራሉ።

2

2:1b.1TH.002.001ወንድሞች ሆይ፥ ራሳችሁ ወደ እናንተ መግባታችን ከንቱ እንዳልሆነ ታውቃላችሁና።

2:2b.1TH.002.002ነገር ግን እንደምታውቁት በፊልጵስዩስ አስቀድመን መከራ ተቀብለን ተንገላትተንም፥ በብዙ ገድል የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ እንናገር ዘንድ በአምላካችን ደፈርን።

2:3b.1TH.002.003ልመናችን ከስሕተት ወይም ከርኵሰት ወይም ከተንኰል አልነበረምና፤

2:4b.1TH.002.004ነገር ግን ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም።

2:5b.1TH.002.005እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤

2:6b.1TH.002.006የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።

2:7b.1TH.002.007ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤

2:8b.1TH.002.008እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።

2:9b.1TH.002.009ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።

2:10b.1TH.002.010በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤

2:11b.1TH.002.011ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና።

2:13b.1TH.002.013ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።

2:14b.1TH.002.014እናንተ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በይሁዳ የሚኖሩትን በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉትን የእግዚአብሔርን ማኅበሮች የምትመስሉ ሆናችኋልና፤ እነርሱ ከአይሁድ መከራ እንደ ተቀበሉ፥ እናንተ ደግሞ ያንን መከራ ከአገራችሁ ሰዎች ተቀብላችኋልና።

2:15b.1TH.002.015እነዚያም ጌታን ኢየሱስን ደግሞ ገደሉ ነቢያትንም እኛንም አሳደዱ፥ እግዚአብሔርንም ደስ አያሰኙም፥ ሰዎችንም ሁሉ ይቃወማሉ፥

2:16b.1TH.002.016ሁልጊዜ ኃጢአታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ አሕዛብ እንዲድኑ እንዳንናገራቸው ይከለክሉናልና። ነገር ግን ቍጣው ወደ እነርሱ ፈጽሞ ደርሶአል።

2:17b.1TH.002.017እኛ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ በልብ ያይደለ ፊት ለፊት ለጥቂት ጊዜ አጥተናችሁ፥ በብዙ ናፍቆት ፊታችሁን ለማየት እጅግ ሞከርን፤

2:18b.1TH.002.018ወደ እናንተ ልንመጣ ወደን ነበርና፥ እኔ ጳውሎስም አንድና ሁለት ጊዜ፥ ሰይጣን ግን አዘገየን።

2:19b.1TH.002.019ተስፋችን ወይስ ደስታችን ወይስ የትምክህታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ፊት በመምጣቱ እናንተ አይደላችሁምን?

2:20b.1TH.002.020እናንተ ክብራችን ደስታችንም ናችሁና።

3

3:1b.1TH.003.001ስለዚህ ወደ ፊት እንታገሥ ዘንድ ባልተቻለን ጊዜ፥ በአቴና ብቻችንን ልንቀር በጎ ፈቃዳችን ሆነ።

3:2b.1TH.003.002ስለ እምነታችሁም እንዲያጸናችሁና እንዲመክራችሁ ወንድማችንን የእግዚአብሔርንም አገልጋይ ከእኛ ጋርም አብሮ በክርስቶስ ወንጌል የሚሠራውን ጢሞቴዎስን ላክነው፤

3:3b.1TH.003.003በዚህ መከራ ማንም እንዳይናውጥ፥ ለዚህ እንደ ተመረጥን ራሳችሁ ታውቃላችሁና።

3:4b.1TH.003.004በእውነት ከእናንተ ጋር ሳለን፥ መከራ እንቀበል ዘንድ እንዳለን አስቀድመን እንነግራችሁ ነበር፤ እንዲሁም ደግሞ ሆነ፥ ይህንም ታውቃላችሁ።

3:5b.1TH.003.005ስለዚህ እኔ ደግሞ ወደ ፊት እታገሥ ዘንድ ባልተቻለኝ ጊዜ። ፈታኝ ምናልባት ፈትኖአቸዋል ድካማችንም ከንቱ ሆኖአል ብዬ እምነታችሁን ለማወቅ ላክሁ።

3:6b.1TH.003.006አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለ እምነታችሁና ስለ ፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥ እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥

3:7b.1TH.003.007ስለዚህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ በእምነታችሁ በኩል በችግራችንና በመከራችን ሁሉ ስለ እናንተ ተጽናናን፤

3:8b.1TH.003.008እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና።

3:9b.1TH.003.009ፊታችሁን ልናይ በእምነታችሁም የጎደለውን ልንሞላበት ሌሊትና ቀን ከመጠን ይልቅ እየጸለይን በአምላካችን ፊት ከእናንተ የተነሣ ስለምንደሰተው ደስታ ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር በእናንተ ምክንያት ምን ያህል ምስጋና እናስረክብ ዘንድ እንችላለን?

3:11b.1TH.003.011አምላካችንና አባታችን ራሱ ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እናንተ መንገዳችንን ያቅና፤

3:12b.1TH.003.012ጌታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ሲመጣ፥ በአምላካችንና በአባታችን ፊት በቅድስና ነቀፋ የሌለበት አድርጎ ልባችሁን ያጸና ዘንድ፥ እኛ ደግሞ ለእናንተ እንደምንሆን ጌታ እርስ በእርሳችሁ ያላችሁን ለሁሉም የሚሆን ፍቅራችሁን ያብዛ ይጨምርም።

4

4:1b.1TH.004.001እንግዲህ በቀረውስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ልትመላለሱ እግዚአብሔርንም ደስ ልታሰኙ እንዴት እንደሚገባችሁ ከእኛ ዘንድ እንደ ተቀበላችሁ፥ እናንተ ደግሞ እንደምትመላለሱ፥ ከፊት ይልቅ ትበዙ ዘንድ በጌታ በኢየሱስ እንለምናችኋለን እንመክራችሁማለን።

4:2b.1TH.004.002በጌታ በኢየሱስ የትኛውን ትእዛዝ እንደ ሰጠናችሁ ታውቃላችሁና።

4:3b.1TH.004.003ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤

4:4b.1TH.004.004ከዝሙት እንድትርቁ፥ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፥ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ እንዲያውቅ፤

4:6b.1TH.004.006አስቀድመን ደግሞ እንዳልናችሁና እንደ መሰከርንላችሁ፥ ጌታ ስለዚህ ነገር ሁሉ የሚበቀል ነውና ማንም በዚህ ነገር አይተላለፍ ወንድሙንም አያታልል።

4:7b.1TH.004.007ለርኵሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና።

4:8b.1TH.004.008እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፥ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ።

4:9b.1TH.004.009እናንተ ራሳችሁ እርስ በርሳችሁ ልትዋደዱ በእግዚአብሔር ተምራችኋልና ስለ ወንድማማች መዋደድ ማንም ይጽፍላችሁ ዘንድ አያስፈልጋችሁም፤

4:10b.1TH.004.010እንዲሁ በመቄዶንያ ሁሉ ላሉት ወንድሞች ሁሉ ታደርጋላችሁና። ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ከፊት ይልቅ ልትበዙ፥ በጸጥታም ትኖሩ ዘንድ ልትቀኑ፥ የራሳችሁንም ጉዳይ ልትጠነቀቁ፥ እንዳዘዝናችሁም፥ በውጭ ባሉት ዘንድ በአገባብ እንድትመላለሱ፥ አንዳችም እንዳያስፈልጋችሁ በእጃችሁ ልትሠሩ እንለምናችኋለን።

4:13b.1TH.004.013ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፥ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን።

4:14b.1TH.004.014ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፥ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና።

4:15b.1TH.004.015በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና፤ እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉቱን አንቀድምም፤

4:16b.1TH.004.016ጌታ ራሱ በትእዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምፅ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፥ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመው ይነሣሉ፤

4:17b.1TH.004.017ከዚያም በኋላ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው፥ ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።

4:18b.1TH.004.018ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።

5

5:1b.1TH.005.001ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ዘመናትና ስለ ወራት ምንም እንዲጻፍላችሁ አያስፈልጋችሁም፤

5:2b.1TH.005.002የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና።

5:3b.1TH.005.003ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም።

5:4b.1TH.005.004እናንተ ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም፥

5:5b.1TH.005.005ሁላችሁ የብርሃን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም፤

5:6b.1TH.005.006እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ።

5:7b.1TH.005.007የሚያንቀላፉ በሌሊት ያንቀላፋሉና፥ የሚሰክሩም በሌሊት ይሰክራሉና፤

5:8b.1TH.005.008እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤

5:9b.1TH.005.009እግዚአብሔር ለቍጣ አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ።

5:10b.1TH.005.010የምንነቃም ብንሆን፥ የምናንቀላፋም ብንሆን፥ ከእርሱ ጋር አብረን በሕይወት እንኖር ዘንድ ስለ እኛ ሞተ።

5:11b.1TH.005.011ስለዚህ እናንተ ደግሞ እንደምታደርጉ፥ እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ አንዱም አንዱም ሌላውን ያንጸው።

5:12b.1TH.005.012ወንድሞች ሆይ፥ በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም ታውቁ ዘንድ፥ ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ ታከብሩአቸው ዘንድ እንለምናችኋለን። እርስ በርሳችሁ በሰላም ሁኑ።

5:14b.1TH.005.014ወንድሞች ሆይ፥ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ ድፍረት የሌላቸውን አጽኑአቸው፤ ለደካሞች ትጉላቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ።

5:15b.1TH.005.015ማንም ለሌላው በክፉ ፈንታ ክፉ እንዳይመልስ ተጠንቀቁ፥ ነገር ግን ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ለሁሉም መልካሙን ለማድረግ ትጉ።

5:16b.1TH.005.016ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤

5:17b.1TH.005.017ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።

5:19b.1TH.005.019መንፈስን አታጥፉ፤

5:20b.1TH.005.020ትንቢትን አትናቁ፤ ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ፤

5:22b.1TH.005.022ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር ራቁ።

5:23b.1TH.005.023የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ።

5:24b.1TH.005.024የሚጠራችሁ የታመነ ነው፥ እርሱም ደግሞ ያደርገዋል።

5:25b.1TH.005.025ወንድሞች ሆይ፥ ስለ እኛ ጸልዩ።

5:26b.1TH.005.026ከወንድሞች ሁሉ ጋር በተቀደሰ አሳሳም ሰላምታ ተሰጣጡ።

5:27b.1TH.005.027ይህ መልእክት ለቅዱሳን ወንድሞች ሁሉ እንዲነበብ በጌታ አምላችኋለሁ።

5:28b.1TH.005.028የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።


Holder of rights
Multilingual Bible Corpus

Citation Suggestion for this Object
TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. 1 Thessalonians (Amharic). 1 Thessalonians (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8AAC-B