Matthew (Amharic)
1
1:1b.MAT.001.001የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ።
1:2b.MAT.001.002አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤
1:3b.MAT.001.003ይሁዳም ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስም ኤስሮምን ወለደ፤
1:4b.MAT.001.004ኤስሮምም አራምን ወለደ፤ አራምም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤
1:5b.MAT.001.005ሰልሞንም ከራኬብ ቦኤዝን ወለደ፤ ቦኤዝም ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤
1:6b.MAT.001.006እሴይም ንጉሥ ዳዊትን ወለደ።
1:7b.MAT.001.007ሰሎሞንም ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓምም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤
1:8b.MAT.001.008አሣፍም ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥም ኢዮራምን ወለደ፤ ኢዮራምም ዖዝያንን ወለደ፤
1:9b.MAT.001.009ዖዝያንም ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታምም አካዝን ወለደ፤
1:10b.MAT.001.010አካዝም ሕዝቅያስን ወለደ፤ ሕዝቅያስም ምናሴን ወለደ፤ ምናሴም አሞፅን ወለደ፤
1:11b.MAT.001.011አሞፅም ኢዮስያስን ወለደ፤ ኢዮስያስም በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ።
1:12b.MAT.001.012ከባቢሎንም ምርኮ በኋላ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤
1:13b.MAT.001.013ዘሩባቤልም አብዩድን ወለደ፤ አብዩድም ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄምም አዛርን ወለደ፤
1:14b.MAT.001.014አዛርም ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅም አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤
1:15b.MAT.001.015ኤልዩድም አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛርም ማታንን ወለደ፤ ማታንም ያዕቆብን ወለደ፤
1:16b.MAT.001.016ያዕቆብም ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን የወለደች የማርያምን እጮኛ ዮሴፍን ወለደ።
1:17b.MAT.001.017እንግዲህ ትውልድ ሁሉ ከአብርሃም እስከ ዳዊት አሥራ አራት ትውልድ፥ ከዳዊትም እስከ ባቢሎን ምርኮ አሥራ አራት ትውልድ፥ ከባቢሎንም ምርኮ እስከ ክርስቶስ አሥራ አራት ትውልድ ነው።
1:18b.MAT.001.018የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበረ። እናቱ ማርያም ለዮሴፍ በታጨች ጊዜ ሳይገናኙ ከመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።
1:19b.MAT.001.019እጮኛዋ ዮሴፍም ጻድቅ ሆኖ ሊገልጣት ስላልወደደ በስውር ሊተዋት አሰበ።
1:20b.MAT.001.020እርሱ ግን ይህን ሲያስብ፥ እነሆ የጌታ መልአክ በሕልም ታየው፥ እንዲህም አለ። የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፥ ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ።
1:21b.MAT.001.021ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።
1:22b.MAT.001.022በነቢይ ከጌታ ዘንድ።
1:23b.MAT.001.023እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።
1:24b.MAT.001.024ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቅቶ የጌታ መልአክ እንዳዘዘው አደረገ፤ እጮኛውንም ወሰደ፤
1:25b.MAT.001.025የበኩር ልጅዋንም እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ ስሙንም ኢየሱስ አለው።
2
2:1b.MAT.002.001ኢየሱስም በይሁዳ ቤተ ልሔም በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን በተወለደ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሰብአ ሰገል። የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።
2:3b.MAT.002.003ንጉሡ ሄሮድስም ሰምቶ ደነገጠ፥ ኢየሩሳሌምም ሁሉ ከእርሱ ጋር፤
2:4b.MAT.002.004የካህናትንም አለቆች የሕዝቡንም ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ ክርስቶስ ወዴት እንዲወለድ ጠየቃቸው።
2:5b.MAT.002.005እነርሱም። አንቺ ቤተ ልሔም፥ የይሁዳ ምድር፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት።
2:7b.MAT.002.007ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠርቶ ኮከቡ የታየበትን ዘመን ከእነርሱ በጥንቃቄ ተረዳ፥
2:8b.MAT.002.008ወደ ቤተ ልሔምም እነርሱን ሰድዶ። ሂዱ፥ ስለ ሕፃኑ በጥንቃቄ መርምሩ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ እኔ ደግሞ መጥቼ እንድሰግድለት ንገሩኝ አላቸው።
2:9b.MAT.002.009እነርሱም ንጉሡን ሰምተው ሄዱ፤ እነሆም፥ በምሥራቅ ያዩት ኮከብ ሕፃኑ ባለበት ላይ መጥቶ እስኪቆም ድረስ ይመራቸው ነበር።
2:10b.MAT.002.010ኮከቡንም ባዩ ጊዜ በታላቅ ደስታ እጅግ ደስ አላቸው።
2:11b.MAT.002.011ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።
2:12b.MAT.002.012ወደ ሄሮድስም እንዳይመለሱ በሕልም ተረድተው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ሄዱ።
2:13b.MAT.002.013እነርሱም ከሄዱ በኋላ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በሕልም ለዮሴፍ ታይቶ። ሄሮድስ ሕፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ፥ እስክነግርህም ድረስ በዚያ ተቀመጥ አለው።
2:14b.MAT.002.014እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ።
2:16b.MAT.002.016ከዚህ በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንደ ተሣለቁበት ባየ ጊዜ እጅግ ተቆጣና ልኮ ከሰብአ ሰገል እንደ ተረዳው ዘመን በቤተ ልሔምና በአውራጃዋ የነበሩትን፥ ሁለት ዓመት የሆናቸውን ከዚያም የሚያንሱትን ሕፃናት ሁሉ አስገደለ።
2:17b.MAT.002.017ያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ፥ ድምፅ በራማ ተሰማ፥ ልቅሶና ብዙ ዋይታ፤ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች፥ መጽናናትም አልወደደችም፥ የሉምና የተባለው ተፈጸመ።
2:19b.MAT.002.019ሄሮድስም ከሞተ በኋላ፥ እነሆ፥ የጌታ መልአክ በግብፅ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶ።
2:20b.MAT.002.020የሕፃኑን ነፍስ የፈለጉት ሞተዋልና ተነሣ፥ ሕፃኑን እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል አገር ሂድ አለ።
2:21b.MAT.002.021እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ።
2:22b.MAT.002.022በአባቱም በሄሮድስ ፈንታ አርኬላዎስ በይሁዳ እንደ ነገሠ በሰማ ጊዜ፥ ወደዚያ መሄድን ፈራ፤ በሕልምም ተረድቶ ወደ ገሊላ አገር ሄደ፤
2:23b.MAT.002.023በነቢያት። ናዝራዊ ይባላል የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ ናዝሬት ወደምትባል ከተማ መጥቶ ኖረ።
3
3:1b.MAT.003.001በዚያም ወራት መጥምቁ ዮሐንስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ብሎ በይሁዳ ምድረ በዳ እየሰበከ መጣ።
3:3b.MAT.003.003በነቢዩ በኢሳይያስ። የጌታን መንገድ አዘጋጁ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮህ ሰው ድምፅ የተባለለት ይህ ነውና።
3:4b.MAT.003.004ራሱም ዮሐንስ የግመል ጠጉር ልብስ ነበረው፥ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ ምግቡም አንበጣና የበረሀ ማር ነበረ።
3:5b.MAT.003.005ያን ጊዜ ኢየሩሳሌም ይሁዳም ሁሉ በዮርዳኖስም ዙሪያ ያለ አገር ሁሉ ወደ እርሱ ይወጡ ነበር፤
3:6b.MAT.003.006ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ በዮርዳኖስ ወንዝ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር።
3:7b.MAT.003.007ዳሩ ግን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎች ወደ ጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ፥ እንዲህ አላቸው። እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ?
3:8b.MAT.003.008እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤
3:9b.MAT.003.009በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን እንደምትሉ አይምሰላችሁ፤ እላችኋለሁና። ከነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር ይችላል።
3:10b.MAT.003.010አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
3:11b.MAT.003.011እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል፤
3:12b.MAT.003.012መንሹም በእጁ ነው፥ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፥ ስንዴውንም በጎተራው ይከታል፥ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።
3:13b.MAT.003.013ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
3:14b.MAT.003.014ዮሐንስ ግን። እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር።
3:15b.MAT.003.015ኢየሱስም መልሶ። አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት።
3:16b.MAT.003.016ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤
3:17b.MAT.003.017እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።
4
4:1b.MAT.004.001ከዚያ ወዲያ ኢየሱስ ከዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው፥
4:2b.MAT.004.002አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከጦመ በኋላ ተራበ።
4:3b.MAT.004.003ፈታኝም ቀርቦ። የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ፥ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ በል አለው።
4:4b.MAT.004.004እርሱም መልሶ። ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል አለው።
4:5b.MAT.004.005ከዚህ በኋላ ዲያቢሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና እርሱን በመቅደስ ጫፍ ላይ አቁሞ።
4:6b.MAT.004.006መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
4:7b.MAT.004.007ኢየሱስም። ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።
4:8b.MAT.004.008ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ።
4:9b.MAT.004.009ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ አለው።
4:10b.MAT.004.010ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።
4:11b.MAT.004.011ያን ጊዜ ዲያቢሎስ ተወው፥ እነሆም፥ መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።
4:12b.MAT.004.012ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ።
4:13b.MAT.004.013ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ።
4:14b.MAT.004.014በነቢዩም በኢሳይያስ። የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው
4:17b.MAT.004.017የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ ኢየሱስ። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር።
4:18b.MAT.004.018በገሊላ ባሕር አጠገብ ሲመላለስም ሁለት ወንድማማች ጴጥሮስ የሚሉትን ስምዖንን ወንድሙንም እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፥ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና።
4:19b.MAT.004.019እርሱም። በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።
4:20b.MAT.004.020ወዲያውም መረባቸውን ትተው ተከተሉት።
4:21b.MAT.004.021ከዚያም እልፍ ብሎ ሌሎችን ሁለት ወንድማማች የዘብዴዎስን ልጅ ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ከአባታቸው ከዘብዴዎስ ጋር በታንኳ መረባቸውን ሲያበጁ አየ፤ ጠራቸውም።
4:22b.MAT.004.022እነርሱም ወዲያው ታንኳይቱንና አባታቸውን ትተው ተከተሉት።
4:23b.MAT.004.023ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ ይዞር ነበር።
4:24b.MAT.004.024ዝናውም ወደ ሶርያ ሁሉ ወጣ፤ በልዩ ልዩ ደዌና ሥቃይም ተይዘው የታመሙትን ሁሉ አጋንንትም ያደሩባቸውን በጨረቃም የሚነሣባቸውን ሽባዎችንም ወደ እርሱ አመጡ፥ ፈወሳቸውም።
4:25b.MAT.004.025ከገሊላም ከአሥሩ ከተማም ከኢየሩሳሌምም ከይሁዳም ከዮርዳኖስም ማዶ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
5
5:1b.MAT.005.001ሕዝቡንም አይቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ በተቀመጠም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀረቡ፤
5:2b.MAT.005.002አፉንም ከፍቶ አስተማራቸው እንዲህም አለ።
5:3b.MAT.005.003በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
5:4b.MAT.005.004የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው፥ መፅናናትን ያገኛሉና።
5:5b.MAT.005.005የዋሆች ብፁዓን ናቸው፥ ምድርን ይወርሳሉና።
5:6b.MAT.005.006ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፥ ይጠግባሉና።
5:7b.MAT.005.007የሚምሩ ብፁዓን ናቸው፥ ይማራሉና።
5:8b.MAT.005.008ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።
5:9b.MAT.005.009የሚያስተራርቁ ብፁዓን ናቸው፥ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና።
5:10b.MAT.005.010ስለ ጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው፥ መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።
5:11b.MAT.005.011ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ።
5:12b.MAT.005.012ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፥ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።
5:13b.MAT.005.013እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም።
5:14b.MAT.005.014እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም።
5:15b.MAT.005.015መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል።
5:16b.MAT.005.016መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ።
5:17b.MAT.005.017እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም።
5:18b.MAT.005.018እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።
5:19b.MAT.005.019እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።
5:20b.MAT.005.020እላችኋለሁና። ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።
5:21b.MAT.005.021ለቀደሙት። አትግደል እንደ ተባለ ሰምታችኋል፤ የገደለም ሁሉ ፍርድ ይገባዋል።
5:22b.MAT.005.022እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።
5:23b.MAT.005.023እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፥
5:24b.MAT.005.024በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።
5:25b.MAT.005.025አብረኸው በመንገድ ሳለህ ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ፤ ባላጋራ ለዳኛ እንዳይሰጥህ ዳኛም ለሎሌው፥ ወደ ወህኒም ትጣላለህ፤
5:26b.MAT.005.026እውነት እልሃለሁ፥ የመጨረሻዋን ሳንቲም እስክትከፍል ድረስ ከቶ ከዚያ አትወጣም።
5:27b.MAT.005.027አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
5:28b.MAT.005.028እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።
5:29b.MAT.005.029ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻልሃልና።
5:30b.MAT.005.030ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ ቆርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነትህ በገሃነም ከሚጣል ይልቅ ከአካላትህ አንድ ቢጠፋ ይሻላልና።
5:31b.MAT.005.031ሚስቱን የሚፈታት ሁሉ የፍችዋን ጽሕፈት ይስጣት ተባለ።
5:32b.MAT.005.032እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን የሚፈታ ሁሉ አመንዝራ ያደርጋታል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል።
5:33b.MAT.005.033ደግሞ ለቀደሙት። በውሸት አትማል ነገር ግን መሐላዎችህን ለጌታ ስጥ እንደተባለ ሰምታችኋል።
5:34b.MAT.005.034እኔ ግን እላችኋለሁ። ከቶ አትማሉ፤ በሰማይ አይሆንም የእግዚአብሔር ዙፋን ነውና፤
5:35b.MAT.005.035በምድርም አይሆንም የእግሩ መረገጫ ናትና፤ በኢየሩሳሌምም አይሆንም የታላቁ ንጉሥ ከተማ ናትና፤
5:36b.MAT.005.036በራስህም አትማል፥ አንዲቱን ጠጉር ነጭ ወይም ጥቁር ልታደርግ አትችልምና።
5:37b.MAT.005.037ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን፤ ከነዚህም የወጣ ከክፉው ነው።
5:38b.MAT.005.038ዓይን ስለ ዓይን ጥርስም ስለ ጥርስ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
5:39b.MAT.005.039እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤
5:40b.MAT.005.040እንዲከስህም እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት፤
5:41b.MAT.005.041ማንም ሰው አንድ ምዕራፍ ትሄድ ዘንድ ቢያስገድድህ ሁለተኛውን ከእርሱ ጋር ሂድ።
5:42b.MAT.005.042ለሚለምንህ ስጥ፥ ከአንተም ይበደር ዘንድ ከሚወደው ፈቀቅ አትበል።
5:43b.MAT.005.043ባልንጀራህን ውደድ ጠላትህንም ጥላ እንደ ተባለ ሰምታችኋል።
5:44b.MAT.005.044እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥ የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤ እርሱ በክፎዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና።
5:46b.MAT.005.046የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?
5:47b.MAT.005.047ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?
5:48b.MAT.005.048እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ።
6
6:1b.MAT.006.001ለሰዎች ትታዩ ዘንድ ምጽዋታችሁን በፊታቸው እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ፤ ያለዚያ በሰማያት ባለው አባታችሁ ዘንድ ዋጋ የላችሁም።
6:2b.MAT.006.002እንግዲህ ምጽዋት ስታደርግ፥ ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
6:3b.MAT.006.003አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።
6:5b.MAT.006.005ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
6:6b.MAT.006.006አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።
6:7b.MAT.006.007አሕዛብም በመናገራቸው ብዛት እንዲሰሙ ይመስላቸዋልና ስትጸልዩ እንደ እነርሱ በከንቱ አትድገሙ።
6:8b.MAT.006.008ስለዚህ አትምሰሉአቸው፤ ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና።
6:9b.MAT.006.009እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ። በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፥
6:10b.MAT.006.010ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤
6:11b.MAT.006.011የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤
6:12b.MAT.006.012እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤
6:13b.MAT.006.013ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን።
6:14b.MAT.006.014ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤
6:15b.MAT.006.015ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።
6:16b.MAT.006.016ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።
6:17b.MAT.006.017አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።
6:19b.MAT.006.019ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤
6:20b.MAT.006.020ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤
6:21b.MAT.006.021መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዚያ ይሆናልና።
6:22b.MAT.006.022የሰውነት መብራት ዓይን ናት። ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤
6:23b.MAT.006.023ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፥ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል። እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፥ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ!
6:24b.MAT.006.024ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።
6:25b.MAT.006.025ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ስለ ነፍሳችሁ በምትበሉትና በምትጠጡት፥ ወይም ስለ ሰውነታችሁ በምትለብሱት አትጨነቁ፤ ነፍስ ከመብል ሰውነትም ከልብስ አይበልጥምን?
6:26b.MAT.006.026ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?
6:27b.MAT.006.027ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?
6:28b.MAT.006.028ስለ ልብስስ ስለ ምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴት እንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፤
6:29b.MAT.006.029አይደክሙም አይፈትሉምም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩ ሁሉ ከነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም።
6:30b.MAT.006.030እግዚአብሔር ግን ዛሬ ያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህ የሚያለብሰው ከሆነ፥ እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ እናንተንማ ይልቁን እንዴት?
6:31b.MAT.006.031እንግዲህ። ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤
6:32b.MAT.006.032ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና።
6:33b.MAT.006.033ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።
6:34b.MAT.006.034ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ፤ ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል።
7
7:1b.MAT.007.001እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና፥ በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል።
7:3b.MAT.007.003በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?
7:4b.MAT.007.004ወይም ወንድምህን። ከዓይንህ ጉድፍ ላውጣ ፍቀድልኝ እንዴትስ ትለዋለህ? እነሆም፥ በዓይንህ ምሰሶ አለ።
7:5b.MAT.007.005አንተ ግብዝ፥ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ ከወንድምህ ዓይን ጉድፉን ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።
7:6b.MAT.007.006በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ።
7:7b.MAT.007.007ለምኑ፥ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፥ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፥ ይከፈትላችሁማል።
7:8b.MAT.007.008የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፥ የሚፈልገውም ያገኛል፥ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።
7:9b.MAT.007.009ወይስ ከእናንተ፥ ልጁ እንጀራ ቢለምነው፥ ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ሰው ነው?
7:10b.MAT.007.010ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይሰጠዋልን?
7:11b.MAT.007.011እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ፥ በሰማያት ያለው አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?
7:12b.MAT.007.012እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና።
7:13b.MAT.007.013በጠበበው ደጅ ግቡ፤ ወደ ጥፋት የሚወስደው ደጅ ሰፊ፥ መንገዱም ትልቅ ነውና፥ ወደ እርሱም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፤
7:14b.MAT.007.014ወደ ሕይወት የሚወስደው ደጅ የጠበበ፥ መንገዱም የቀጠነ ነውና፥ የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው።
7:15b.MAT.007.015የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ።
7:16b.MAT.007.016ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን?
7:17b.MAT.007.017እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።
7:18b.MAT.007.018መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።
7:19b.MAT.007.019መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል።
7:20b.MAT.007.020ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።
7:21b.MAT.007.021በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።
7:22b.MAT.007.022በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል።
7:23b.MAT.007.023የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።
7:24b.MAT.007.024ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል።
7:25b.MAT.007.025ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፥ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።
7:26b.MAT.007.026ይህንም ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል።
7:27b.MAT.007.027ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።
7:28b.MAT.007.028ኢየሱስም ይህን ነገር በጨረሰ ጊዜ ሕዝቡ በትምህርቱ ተገረሙ፤ እንደ ጻፎቻቸው ሳይሆን
7:29b.MAT.007.029እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና።
8
8:1b.MAT.008.001ከተራራም በወረደ ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
8:2b.MAT.008.002እነሆም፥ ለምጻም ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ እያለ ሰገደለት።
8:3b.MAT.008.003እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው። ወዲያውም ለምጹ ነጻ።
8:4b.MAT.008.004ኢየሱስም። ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ አለው።
8:5b.MAT.008.005ወደ ቅፍርናሆምም በገባ ጊዜ የመቶ አለቃ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥
8:6b.MAT.008.006ብላቴናዬ ሽባ ሆኖ እጅግ እየተሣቀየ በቤት ተኝቶአል ብሎ ለመነው።
8:7b.MAT.008.007ኢየሱስም። እኔ መጥቼ እፈውሰዋለሁ አለው።
8:8b.MAT.008.008የመቶ አለቃውም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በቤቴ ጣራ ከታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን ቃል ብቻ ተናገር፥ ብላቴናዬም ይፈወሳል።
8:9b.MAT.008.009እኔ ደግሞ ለሌሎች ተገዥ ነኝና፥ ከእኔም በታች ጭፍራ አለኝ፤ አንዱንም። ሂድ ብለው ይሄዳል፥ ሌላውንም። ና ብለው ይመጣል፥ ባሪያዬንም። ይህን አድርግ ብለው ያደርጋል አለው።
8:10b.MAT.008.010ኢየሱስም ሰምቶ ተደነቀና ለተከተሉት እንዲህ አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ በእስራኤል እንኳ እንዲህ ያለ ትልቅ እምነት አላገኘሁም።
8:11b.MAT.008.011እላችኋለሁም፥ ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር በመንግሥተ ሰማያት ይቀመጣሉ፤
8:12b.MAT.008.012የመንግሥት ልጆች ግን በውጭ ወደ አለው ጨለማ ይጣላሉ፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
8:13b.MAT.008.013ኢየሱስም ለመቶ አለቃ። ሂድና እንዳመንህ ይሁንልህ አለው። ብላቴናውም በዚያች ሰዓት ተፈወሰ።
8:14b.MAT.008.014ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ቤት ገብቶ አማቱን በንዳድ ታማ ተኝታ አያት፤
8:15b.MAT.008.015እጅዋንም ዳሰሰ፥ ንዳዱም ለቀቃት፤ ተነሥታም አገለገለቻቸው።
8:16b.MAT.008.016በመሸም ጊዜ አጋንንት ያደረባቸውን ብዙዎችን ወደ እርሱ አመጡ፤ በነቢዩ በኢሳይያስ። እርሱ ድካማችንን ተቀበለ ደዌያችንንም ተሸከመ የተባለው ይፈጸም ዘንድ፥ መናፍስትን በቃሉ አወጣ፥ የታመሙትንም ሁሉ ፈወሰ።
8:18b.MAT.008.018ኢየሱስም ብዙ ሰዎች ሲከቡት አይቶ ወደ ማዶ እንዲሻገሩ አዘዘ።
8:19b.MAT.008.019አንድ ጻፊም ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።
8:20b.MAT.008.020ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።
8:21b.MAT.008.021ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው።
8:22b.MAT.008.022ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።
8:23b.MAT.008.023ወደ ታንኳም ሲገባ ደቀ መዛሙርቱ ተከተሉት።
8:24b.MAT.008.024እነሆም፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን እስኪደፍናት ድረስ በባሕር ታላቅ መናወጥ ሆነ፤ እርሱ ግን ተኝቶ ነበር።
8:25b.MAT.008.025ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ አድነን፥ ጠፋን እያሉ አስነሡት።
8:26b.MAT.008.026እርሱም። እናንተ እምነት የጎደላችሁ፥ ስለ ምን ትፈራላችሁ? አላቸው፤ ከዚህ በኋላ ተነሥቶ ነፋሱንና ባሕሩን ገሠጸ፥ ታላቅ ጸጥታም ሆነ።
8:27b.MAT.008.027ሰዎቹም። ነፋሳትና ባሕርስ ስንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው? እያሉ ተደነቁ።
8:28b.MAT.008.028ወደ ማዶም ወደ ጌርጋሴኖን አገር በመጣ ጊዜ፥ አጋንንት ያደሩባቸው ሁለት ሰዎች ከመቃብር ወጥተው ተገናኙት፤ እነርሱም ሰው በዚያ መንገድ ማለፍ እስኪሳነው ድረስ እጅግ ክፉዎች ነበሩ።
8:29b.MAT.008.029እነሆም። ኢየሱስ ሆይ፥ የእግዚአብሔር ልጅ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ጊዜው ሳይደርስ ልትሣቅየን ወደዚህ መጣህን? እያሉ ጮኹ።
8:30b.MAT.008.030ከእነርሱም ርቆ የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማራ ነበር።
8:31b.MAT.008.031አጋንንቱም። ታወጣንስ እንደሆንህ፥ ወደ እሪያው መንጋ ስደደን ብለው ለመኑት። ሂዱ አላቸው።
8:32b.MAT.008.032እነርሱም ወጥተው ወደ እሪያዎቹ ሄዱና ገቡ፤ እነሆም፥ የእሪያዎቹ መንጋ ሁሉ ከአፋፉ ወደ ባሕር እየተጣደፉ ሮጡ በውኃም ውስጥ ሞቱ።
8:33b.MAT.008.033እረኞችም ሸሹ፥ ወደ ከተማይቱም ሄደው ነገሩን ሁሉ አጋንንትም በአደሩባቸው የሆነውን አወሩ።
8:34b.MAT.008.034እነሆም፥ ከተማው ሁሉ ኢየሱስን ሊገናኝ ወጣ፥ ባዩትም ጊዜ ከአገራቸው እንዲሄድላቸው ለመኑት።
9
9:1b.MAT.009.001በታንኳም ገብቶ ተሻገረና ወደ ገዛ ከተማው መጣ።
9:2b.MAT.009.002እነሆም፥ በአልጋ የተኛ ሽባ ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን። አንተ ልጅ፥ አይዞህ፥ ኃጢአትህ ተሰረየችልህ አለው።
9:3b.MAT.009.003እነሆም፥ ከጻፎቹ አንዳንዱ በልባቸው። ይህስ ይሳደባል አሉ።
9:4b.MAT.009.004ኢየሱስም አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አለ። ስለ ምን በልባችሁ ክፉ ታስባላችሁ?
9:5b.MAT.009.005ኃጢአትህ ተሰረየችልህ ከማለት ወይስ። ተነሣና ሂድ ከማለት ማናቸው ይቀላል?
9:6b.MAT.009.006ነገር ግን በምድር ላይ ኃጢአትን ያስተሰርይ ዘንድ ለሰው ልጅ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ፥ በዚያን ጊዜ ሽባውን። ተነሣ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ አለው።
9:7b.MAT.009.007ተነሥቶም ወደ ቤቱ ሄደ።
9:8b.MAT.009.008ሕዝቡም አይተው ተደነቁ፥ ለሰውም እንዲህ ያለ ሥልጣን የሰጠ እግዚአብሔርን አከበሩ።
9:9b.MAT.009.009ኢየሱስም ከዚያ አልፎ በመቅረጫው ተቀምጦ የነበረ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው አየና። ተከተለኝ አለው። ተነሥቶም ተከተለው።
9:10b.MAT.009.010በቤቱም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ፥ እነሆ፥ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች መጥተው ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ተቀመጡ።
9:11b.MAT.009.011ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን። መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል? አሉአቸው።
9:12b.MAT.009.012ኢየሱስም ሰምቶ። ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤
9:13b.MAT.009.013ነገር ግን ሄዳችሁ። ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው።
9:14b.MAT.009.014በዚያን ጊዜ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ቀርበው። እኛና ፈሪሳውያን፥ ብዙ ጊዜ የምንጦመው፥ ደቀ መዛሙርትህ ግን የማይጦሙት ስለ ምንድር ነው? አሉት።
9:15b.MAT.009.015ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ሚዜዎች ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ ሊያዝኑ ይችላሉን? ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ወራት ይመጣል፥ በዚያ ጊዜም ይጦማሉ።
9:16b.MAT.009.016በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል።
9:17b.MAT.009.017በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ።
9:18b.MAT.009.018ይህንም ሲነግራቸው፥ አንድ መኰንን መጥቶ። ልጄ አሁን ሞተች፤ ነገር ግን መጥተህ እጅህን ጫንባት፥ በሕይወትም ትኖራለች እያለ ሰገደለት።
9:19b.MAT.009.019ኢየሱስም ተነሥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተከተለው።
9:20b.MAT.009.020እነሆም፥ ከአሥራ ሁለት ዓመት ጀምሮ ደም የሚፈስሳት ሴት በኋላው ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፤
9:21b.MAT.009.021በልብዋ። ልብሱን ብቻ የዳሰስሁ እንደ ሆነ፥ እድናለሁ ትል ነበረችና።
9:22b.MAT.009.022ኢየሱስም ዘወር ብሎ አያትና። ልጄ ሆይ፥ አይዞሽ፤ እምነትሽ አድኖሻል አላት። ሴቲቱም ከዚያች ሰዓት ጀምራ ዳነች።
9:23b.MAT.009.023ኢየሱስም ወደ መኰንኑ ቤት በደረሰ ጊዜ፥ እምቢልተኞችንና የሚንጫጫውን ሕዝብ አይቶ።
9:24b.MAT.009.024ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችምና ፈቀቅ በሉ አላቸው። በጣምም ሳቁበት።
9:25b.MAT.009.025ሕዝቡን ግን ከአስወጡ በኋላ ገብቶ እጅዋን ያዛት፥ ብላቴናይቱም ተነሣች።
9:26b.MAT.009.026ያም ዝና ወደዚያ አገር ሁሉ ወጣ።
9:27b.MAT.009.027ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች። የዳዊት ልጅ ሆይ፥ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት።
9:28b.MAT.009.028ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ፥ ኢየሱስም። ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው። አዎን፥ ጌታ ሆይ አሉት።
9:29b.MAT.009.029በዚያን ጊዜ። እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ።
9:30b.MAT.009.030ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ።
9:31b.MAT.009.031ኢየሱስም። ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው። እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ።
9:32b.MAT.009.032እነርሱም ሲወጡ እነሆ፥ ጋኔን ያደረበትን ዲዳ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
9:33b.MAT.009.033ጋኔኑንም ካወጣው በኋላ ዲዳው ተናገረ። ሕዝቡም። እንዲህ ያለ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልታየም እያሉ ተደነቁ።
9:34b.MAT.009.034ፈሪሳውያን ግን። በአጋንንት አለቃ አጋንንትን ያወጣል አሉ።
9:35b.MAT.009.035ኢየሱስም በምኩራቦቻቸው እያስተማረ፥ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ፥ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ፥ በከተማዎችና በመንደሮች ሁሉ ይዞር ነበር።
9:36b.MAT.009.036ብዙ ሕዝብም ባየ ጊዜ፥ እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው።
9:37b.MAT.009.037በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። መከሩስ ብዙ ነው፥ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው፤
9:38b.MAT.009.038እንግዲህ የመከሩን ጌታ ወደ መከሩ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት አላቸው።
10
10:1b.MAT.010.001አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው።
10:2b.MAT.010.002የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም ይህ ነው፤ መጀመሪያው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን ወንድሙ እንድርያስም፥ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብም ወንድሙ ዮሐንስም፥
10:3b.MAT.010.003ፊልጶስም በርተሎሜዎስም፥ ቶማስም ቀራጩ ማቴዎስም፥ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም ታዴዎስም የተባለው ልብድዮስ፥
10:4b.MAT.010.004ቀነናዊውም ስምዖን ደግሞም አሳልፎ የሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ።
10:5b.MAT.010.005እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤
10:6b.MAT.010.006ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ።
10:7b.MAT.010.007ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ።
10:8b.MAT.010.008ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ።
10:9b.MAT.010.009ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥
10:10b.MAT.010.010ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።
10:11b.MAT.010.011በምትገቡባትም በማናቸይቱም ከተማ ወይም መንደር፥ በዚያ የሚገባው ማን እንደ ሆነ በጥንቃቄ መርምሩ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ።
10:12b.MAT.010.012ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ፤
10:13b.MAT.010.013ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት፤ ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ።
10:14b.MAT.010.014ከማይቀበላችሁም ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ፥ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ።
10:15b.MAT.010.015እውነት እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ይቀልላቸዋል።
10:16b.MAT.010.016እነሆ፥ እኔ እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ።
10:17b.MAT.010.017ነገር ግን ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል፥ በምኩራቦቻቸውም ይገርፉአችኋልና ከሰዎች ተጠበቁ፤
10:18b.MAT.010.018ለእነርሱና ለአሕዛብም ምስክር እንዲሆን፥ ስለ እኔ ወደ ገዥዎች ወደ ነገሥታትም ትወሰዳላችሁ።
10:19b.MAT.010.019አሳልፈውም ሲሰጡአችሁ፥ የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ፤
10:20b.MAT.010.020በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ፥ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁምና።
10:21b.MAT.010.021ወንድምም ወንድሙን፥ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ ይገድሉአቸውማል።
10:22b.MAT.010.022በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
10:23b.MAT.010.023በአንዲቱ ከተማም መከራ ቢያሳዩአችሁ ወደ ሌላይቱ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁና፥ የሰው ልጅ እስኪመጣ ድረስ የእስራኤልን ከተማዎች አትዘልቁም።
10:24b.MAT.010.024ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፥ ባሪያም ከጌታው አይበልጥም።
10:25b.MAT.010.025ደቀ መዝሙር እንደ መምህሩ፥ ባሪያም እንደ ጌታው መሆኑ ይበቃዋል። ባለቤቱን ብዔል ዜቡል ካሉት፥ ቤተሰዎቹንማ እንዴት አብዝተው አይሉአቸው!
10:26b.MAT.010.026እንግዲህ አትፍሩአቸው፤ የማይገለጥ የተከደነ፥ የማይታወቅም የተሰወረ ምንም የለምና።
10:27b.MAT.010.027በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮም የምትሰሙትን በሰገነት ላይ ስበኩ።
10:28b.MAT.010.028ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ።
10:29b.MAT.010.029ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም።
10:30b.MAT.010.030የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
10:31b.MAT.010.031እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
10:32b.MAT.010.032ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤
10:33b.MAT.010.033በሰው ፊትም የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ።
10:34b.MAT.010.034በምድር ላይ ሰላምን ለማምጣት የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማምጣት አልመጣሁም።
10:35b.MAT.010.035ሰውን ከአባቱ፥ ሴት ልጅንም ከእናትዋ፥ ምራትንም ከአማትዋ እለያይ ዘንድ መጥቻለሁና፤
10:36b.MAT.010.036ለሰውም ቤተ ሰዎቹ ጠላቶች ይሆኑበታል።
10:37b.MAT.010.037ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፤
10:38b.MAT.010.038መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም።
10:39b.MAT.010.039ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።
10:40b.MAT.010.040እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።
10:41b.MAT.010.041ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።
10:42b.MAT.010.042ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።
11
11:1b.MAT.011.001ኢየሱስም አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ማዘዝ በፈጸመ ጊዜ በከተሞቻቸው ሊያስተምርና ሊሰብክ ከዚያ አለፈ።
11:2b.MAT.011.002ዮሐንስም በወህኒ ሳለ የክርስቶስን ሥራ ሰምቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከና።
11:3b.MAT.011.003የሚመጣው አንተ ነህን? ወይስ ሌላ እንጠብቅ? አለው።
11:4b.MAT.011.004ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤
11:5b.MAT.011.005ዕውሮች ያያሉ አንካሶችም ይሄዳሉ፥ ለምጻሞችም ይነጻሉ ደንቆሮችም ይሰማሉ፥ ሙታንም ይነሣሉ
11:6b.MAT.011.006ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው።
11:7b.MAT.011.007እነዚያም ሲሄዱ ኢየሱስ ለሕዝቡ ስለ ዮሐንስ ሊናገር ጀመረ እንዲህም አለ። ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ?
11:8b.MAT.011.008ነፋስ የሚወዘውዘውን ሸምበቆን? ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ቀጭን ልብስ የለበሰ ሰውን? እነሆ፥ ቀጭን ልብስ የለበሱ በነገሥታት ቤት አሉ።
11:9b.MAT.011.009ወይስ ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ፥ ከነቢይም የሚበልጠውን።
11:10b.MAT.011.010እነሆ፥ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ
11:11b.MAT.011.011ተብሎ የተጻፈለት ይህ ነውና። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ በመንግሥተ ሰማያት ግን ከሁሉ የሚያንሰው ይበልጠዋል።
11:12b.MAT.011.012ከመጥምቁም ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፥ ግፈኞችም ይናጠቋታል።
11:13b.MAT.011.013ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ፤
11:14b.MAT.011.014ልትቀበሉትስ ብትወዱ፥ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።
11:15b.MAT.011.015የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
11:16b.MAT.011.016ነገር ግን ይህን ትውልድ በምን እመስለዋለሁ? በገበያ የሚቀመጡትን ልጆች ይመስላሉ፥ እነርሱም ባልንጀሮቻቸውን እየጠሩ።
11:17b.MAT.011.017እንቢልታ ነፋንላችሁ ዘፈንም አልዘፈናችሁም ሙሾ አወጣንላችሁ ዋይ ዋይም አላላችሁም ይሉአቸዋል።
11:18b.MAT.011.018ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፥ እነርሱም። ጋኔን አለበት አሉት።
11:19b.MAT.011.019የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፥ እነርሱም። እነሆ፥ በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጭ፥ የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ይሉታል። ጥበብም በልጆችዋ ጸደቀች።
11:20b.MAT.011.020በዚያን ጊዜ የሚበዙ ተአምራት የተደረገባቸውን ከተማዎች ንስሐ ስላልገቡ ሊነቅፋቸው ጀመረ እንዲህም አለ።
11:21b.MAT.011.021ወዮልሽ ኮራዚ፤ ወዮልሽ ቤተ ሳይዳ፤ በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና።
11:22b.MAT.011.022ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።
11:23b.MAT.011.023አንቺም ቅፍርናሆም፥ እስከ ሰማይ ከፍ አልሽን? ወደ ሲኦል ትወርጃለሽ፤ በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና።
11:24b.MAT.011.024ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል።
11:25b.MAT.011.025በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ የሰማይና የምድር ጌታ፥ ይህን ከጥበበኞችና ከአስተዋዮች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤
11:26b.MAT.011.026አዎን፥ አባት ሆይ፥ ፈቃድህ በፊትህ እንዲህ ሆኖአልና።
11:27b.MAT.011.027ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም።
11:28b.MAT.011.028እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፥ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።
11:29b.MAT.011.029ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤
11:30b.MAT.011.030ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።
12
12:1b.MAT.012.001በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር።
12:2b.MAT.012.002ፈሪሳውያንም አይተው። እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።
12:3b.MAT.012.003እርሱ ግን እንዲህ አላቸው። ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ፥ እርሱ ያደረገውን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ገባ ካህናትም ብቻ እንጂ እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን?
12:5b.MAT.012.005ካህናትም በሰንበት በመቅደስ ሰንበትን እንዲያረክሱ ኃጢአትም እንዳይሆንባቸው በሕጉ አላነበባችሁምን?
12:6b.MAT.012.006ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
12:7b.MAT.012.007ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር።
12:8b.MAT.012.008የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።
12:9b.MAT.012.009ከዚያም አልፎ ወደ ምኩራባቸው ገባ።
12:10b.MAT.012.010እነሆም፥ እጁ የሰለለች ሰው ነበረ፤ ይከሱትም ዘንድ። በሰንበት መፈወስ ተፈቅዶአልን? ብለው ጠየቁት።
12:11b.MAT.012.011እርሱ ግን። ከእናንተ አንድ በግ ያለው በሰንበት በጉድጓድ ቢወድቅበት፥ ይዞ የማያወጣው ሰው ማን ነው?
12:12b.MAT.012.012እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው።
12:13b.MAT.012.013ከዚያም በኋላ ሰውየውን። እጅህን ዘርጋ አለው። ዘረጋትም፥ እንደ ሁለተኛይቱም ደህና ሆነች።
12:14b.MAT.012.014ፈሪሳውያን ግን ወጥተው እንዴት አድርገው እንዲያጠፉት ተማከሩበት።
12:15b.MAT.012.015ኢየሱስም አውቆ ከዚያ ፈቀቅ አለ። ብዙ ሰዎችም ተከተሉት፥ ሁሉንም ፈወሳቸው፥ እንዳይገልጡትም አዘዛቸው፤
12:16b.MAT.012.016በነቢዩ በኢሳይያስ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እንዲህ ሲል።
12:18b.MAT.012.018እነሆ የመረጥሁት ብላቴናዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ወዳጄ፤ መንፈሴን በእርሱ ላይ አኖራለሁ፥ ፍርድንም ለአሕዛብ ያወራል።
12:19b.MAT.012.019አይከራከርም አይጮህምም፥ ድምፁንም በአደባባይ የሚሰማ የለም።
12:20b.MAT.012.020ፍርድን ድል ለመንሣት እስኪያወጣ፥ የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም የሚጤስን የጥዋፍ ክርም አያጠፋም።
12:21b.MAT.012.021አሕዛብም በስሙ ተስፋ ያደርጋሉ።
12:22b.MAT.012.022ከዚህም በኋላ ጋኔን ያደረበትን ዕውር ዲዳም ወደ እርሱ አመጡ፤ ዕውሩም ዲዳውም እስኪያይና እስኪናገር ድረስ ፈወሰው።
12:23b.MAT.012.023ሕዝቡም ሁሉ ተገረሙና። እንጃ ይህ ሰው የዳዊት ልጅ ይሆንን? አሉ።
12:24b.MAT.012.024ፈሪሳውያን ግን ሰምተው። ይህ በብዔል ዜቡል በአጋንንት አለቃ ካልሆነ በቀር አጋንንትን አያወጣም አሉ።
12:25b.MAT.012.025ኢየሱስ ግን አሳባቸውን አውቆ እንዲህ አላቸው። እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም።
12:26b.MAT.012.026ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?
12:27b.MAT.012.027እኔስ በብዔል ዜቡል አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ ልጆቻችሁ በማን ያወጡአቸዋል? ስለዚህ እነርሱ ፈራጆች ይሆኑባችኋል።
12:28b.MAT.012.028እኔ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ አጋንንትን የማወጣ ከሆንሁ፥ እንግዲህ የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ እናንተ ደርሳለች።
12:29b.MAT.012.029ወይስ ሰው አስቀድሞ ኃይለኛውን ሳያስር ወደ ኃይለኛው ቤት ገብቶ እቃውን ሊነጥቀው እንዴት ይችላል? ከዚያም ወዲያ ቤቱን ይበዘብዛል።
12:30b.MAT.012.030ከእኔ ጋር ያልሆነ ይቃወመኛል፥ ከእኔ ጋርም የማያከማች ይበትናል።
12:31b.MAT.012.031ስለዚህ እላችኋለሁ፥ ኃጢአትና ስድብ ሁሉ ለሰዎች ይሰረይላቸዋል፥ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን ለሰደበ አይሰረይለትም።
12:32b.MAT.012.032በሰው ልጅ ላይ ቃል የሚናገር ሁሉ ይሰረይለታል፤ በመንፈስ ቅዱስ ላይ ግን የሚናገር ሁሉ በዚህ ዓለም ቢሆን ወይም በሚመጣው አይሰረይለትም።
12:33b.MAT.012.033ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ።
12:34b.MAT.012.034እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና።
12:35b.MAT.012.035መልካም ሰው ከልቡ መልካም መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል፥ ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል።
12:36b.MAT.012.036እኔ እላችኋለሁ፥ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤
12:37b.MAT.012.037ከቃልህ የተነሣ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሣ ትኰነናለህ።
12:38b.MAT.012.038በዚያን ጊዜ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን አንዳንዶቹ መለሱና። መምህር ሆይ፥ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን አሉ።
12:39b.MAT.012.039እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።
12:40b.MAT.012.040ዮናስ በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል።
12:41b.MAT.012.041የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
12:42b.MAT.012.042ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።
12:43b.MAT.012.043ርኩስ መንፈስ ግን ከሰው በወጣ ጊዜ፥ ዕረፍት እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፥ አያገኝምም።
12:44b.MAT.012.044በዚያን ጊዜም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤ ቢመጣም ባዶ ሆኖ ተጠርጎና አጊጦ ያገኘዋል።
12:45b.MAT.012.045ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሰባት ሌሎችን አጋንንት ከእርሱ ጋር ይወስዳል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል። ለዚህ ክፉ ትውልድ ደግሞ እንዲሁ ይሆንበታል።
12:46b.MAT.012.046ገናም ለሕዝቡ ሲናገር፥ እነሆ፥ እናቱና ወንድሞቹ ሊነጋገሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።
12:47b.MAT.012.047አንዱም። እነሆ፥ እናትህና ወንድሞችህ ሊነጋገሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል አለው።
12:48b.MAT.012.048እርሱ ግን ለነገረው መልሶ። እናቴ ማን ናት? ወንድሞቼስ እነማን ናቸው? አለው።
12:49b.MAT.012.049እጁንም ወደ ደቀ መዛሙርቱ ዘርግቶ። እነሆ እናቴና ወንድሞቼ፤
12:50b.MAT.012.050በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ፥ እርሱ ወንድሜ እኅቴም እናቴም ነውና አለ።
13
13:1b.MAT.013.001በዚያን ቀን ኢየሱስ ከቤት ወጥቶ በባሕር አጠገብ ተቀመጠ፤
13:2b.MAT.013.002እርሱም በታንኳ ገብቶ እስኪቀመጥ ድረስ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተሰበሰቡ፥ ሕዝቡም ሁሉ በወደቡ ቆመው ነበር።
13:3b.MAT.013.003በምሳሌም ብዙ ነገራቸው እንዲህም አላቸው። እነሆ፥ ዘሪ ሊዘራ ወጣ።
13:4b.MAT.013.004እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፥ ወፎችም መጥተው በሉት።
13:5b.MAT.013.005ሌላውም ብዙ መሬት በሌለበት በጭንጫ ላይ ወደቀ፤ ጥልቅ መሬትም ስላልነበረው ወዲያው በቀለ፥
13:6b.MAT.013.006ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ጠወለገ፥ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ።
13:7b.MAT.013.007ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ፥ እሾህም ወጣና አነቀው።
13:8b.MAT.013.008ሌላውም በመልካም መሬት ወደቀ፤ አንዱም መቶ፥ አንዱም ስድሳ፥ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።
13:9b.MAT.013.009የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
13:10b.MAT.013.010ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። ስለ ምን በምሳሌ ትነግራቸዋለህ? አሉት።
13:11b.MAT.013.011እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። ለእናንተ የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፥ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።
13:12b.MAT.013.012ላለው ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
13:13b.MAT.013.013ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙም ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ።
13:14b.MAT.013.014መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትም ታያላችሁና አትመለከቱም።
13:15b.MAT.013.015በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል።
13:16b.MAT.013.016የእናንተ ግን ዓይኖቻችሁ ስለሚያዩ ጆሮቻችሁም ስለሚሰሙ ብፁዓን ናቸው።
13:17b.MAT.013.017እውነት እላችኋለሁ፥ ብዙዎች ነቢያትና ጻድቃን የምታዩትን ሊያዩ ተመኝተው አላዩም፥ የምትሰሙትንም ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም።
13:18b.MAT.013.018እንግዲህ እናንተ የዘሪውን ምሳሌ ስሙ።
13:19b.MAT.013.019የመንግሥትን ቃል ሰምቶ በማያስተውል ሁሉ፥ ክፉው ይመጣል፥ በልቡ የተዘራውንም ይነጥቃል፤ በመንገድ ዳር የተዘራው ይህ ነው።
13:20b.MAT.013.020በጭንጫ ላይ የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ ወዲያው በደስታ የሚቀበለው ነው፤
13:21b.MAT.013.021ነገር ግን ለጊዜው ነው እንጂ በእርሱ ሥር የለውም፥ በቃሉ ምክንያትም መከራ ወይም ስደት በሆነ ጊዜ ወዲያው ይሰናከላል።
13:22b.MAT.013.022በእሾህ መካከል የተዘራውም ይህ ቃሉን የሚሰማ ነው፥ የዚህም ዓለም አሳብና የባለጠግነት መታለል ቃሉን ያንቃል፥ የማያፈራም ይሆናል።
13:23b.MAT.013.023በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።
13:24b.MAT.013.024ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች።
13:25b.MAT.013.025ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ።
13:26b.MAT.013.026ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ።
13:27b.MAT.013.027የባለቤቱም ባሮች ቀርበው። ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት።
13:28b.MAT.013.028እርሱም። ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም። እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት።
13:29b.MAT.013.029እርሱ ግን። እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም።
13:30b.MAT.013.030ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን። እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ።
13:31b.MAT.013.031ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤
13:32b.MAT.013.032እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።
13:33b.MAT.013.033ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ። መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።
13:34b.MAT.013.034ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም። በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም።
13:36b.MAT.013.036በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው። የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት።
13:37b.MAT.013.037እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤
13:38b.MAT.013.038መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤
13:39b.MAT.013.039እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው።
13:40b.MAT.013.040እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል።
13:41b.MAT.013.041የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥
13:42b.MAT.013.042ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
13:43b.MAT.013.043በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።
13:44b.MAT.013.044ደግሞ መንግሥተ ሰማያት በእርሻ ውስጥ የተሰወረውን መዝገብ ትመስላለች፤ ሰውም አግኝቶ ሰወረው፥ ከደስታውም የተነሣ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ያን እርሻ ገዛ።
13:45b.MAT.013.045ደግሞ መንግሥተ ሰማያት መልካምን ዕንቁ የሚሻ ነጋዴን ትመስላለች፤
13:46b.MAT.013.046ዋጋዋም እጅግ የበዛ አንዲት ዕንቁ በአገኘ ጊዜ ሄዶ ያለውን ሁሉ ሸጠና ገዛት።
13:47b.MAT.013.047ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች፤
13:48b.MAT.013.048በሞላችም ጊዜ ወደ ወደቡ አወጡአት፥ ተቀምጠውም መልካሙን ለቅመው በዕቃዎች ውስጥ አከማቹ ክፉውን ግን ወደ ውጭ ጣሉት።
13:49b.MAT.013.049በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል፤ መላእክት መጥተው ኃጢአተኞችን ከጻድቃን መካከል ይለዩአቸዋል፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤
13:50b.MAT.013.050በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
13:51b.MAT.013.051ኢየሱስም። ይህን ሁሉ አስተዋላችሁን? አላቸው አዎን አሉት።
13:52b.MAT.013.052እርሱም። ስለዚህ የመንግሥተ ሰማያት ደቀ መዝሙር የሆነ ጻፊ ሁሉ ከመዝገቡ አዲሱንና አሮጌውን የሚያወጣ ባለቤትን ይመስላል አላቸው።
13:53b.MAT.013.053ኢየሱስም እነዚህም ምሳሌዎች ከጨረሰ በኋላ ከዚያ ሄደ።
13:54b.MAT.013.054ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፤ እንዲህም አሉ። ይህን ጥበብና ተአምራት ይህ ከወዴት አገኘው?
13:55b.MAT.013.055ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን?
13:56b.MAT.013.056እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን? እንኪያስ ይህን ሁሉ ከወዴት አገኘው? ተሰናከሉበትም።
13:57b.MAT.013.057ኢየሱስ ግን። ነቢይ ከገዛ አገሩና ከገዛ ቤቱ በቀር ሳይከበር አይቀርም አላቸው።
13:58b.MAT.013.058በአለማመናቸውም ምክንያት በዚያ ብዙ ተአምራት አላደረገም።
14
14:1b.MAT.014.001በዚያ ዘመን የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስ የኢየሱስን ዝና ሰማ፥
14:2b.MAT.014.002ለሎሌዎቹም። ይህ መጥምቁ ዮሐንስ ነው፤ እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል፥ ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
14:3b.MAT.014.003ሄሮድስ በወንድሙ በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ዮሐንስን አስይዞ አሳስሮት በወህኒ አኑሮት ነበርና፤
14:4b.MAT.014.004ዮሐንስ። እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
14:5b.MAT.014.005ሊገድለውም ወዶ ሳለ፥ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለ አዩት ፈራቸው።
14:6b.MAT.014.006ነገር ግን ሄሮድስ የተወለደበት ቀን በሆነ ጊዜ፥ የሄሮድያዳ ልጅ በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤
14:7b.MAT.014.007ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት።
14:8b.MAT.014.008እርስዋም በእናትዋ ተመክራ። የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው።
14:9b.MAT.014.009ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤
14:10b.MAT.014.010ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው።
14:11b.MAT.014.011ራሱንም በወጭት አምጥተው ለብላቴናይቱ ሰጡአት፥ ወደ እናትዋም ወሰደችው።
14:12b.MAT.014.012ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው በድኑን ወሰዱና ቀበሩት፥ መጥተውም ለኢየሱስ አወሩለት።
14:13b.MAT.014.013ኢየሱስም በሰማ ጊዜ ከዚያ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ በታንኳ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡም ሰምተው ከከተማዎቹ በእግር ተከተሉት።
14:14b.MAT.014.014ወጥቶም ብዙ ሕዝብ አየና አዘነላቸው ድውዮቻቸውንም ፈወሰ።
14:15b.MAT.014.015በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም ሰዓቱ አልፎአል፤ ወደ መንደሮች ሄደው ለራሳቸው ምግብ እንዲገዙ ሕዝቡን አሰናብት አሉት።
14:16b.MAT.014.016ኢየሱስም። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው እንጂ ሊሄዱ አያስፈልግም አላቸው።
14:17b.MAT.014.017እነርሱም። ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ በቀር በዚህ የለንም አሉት።
14:18b.MAT.014.018እርሱም። እነዚያን ወደዚህ አምጡልኝ አላቸው።
14:19b.MAT.014.019ሕዝቡም በሣር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፥ አምስቱንም እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።
14:20b.MAT.014.020ሁሉም በልተው ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሡ።
14:21b.MAT.014.021ከሴቶችና ከልጆችም በቀር የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ያህሉ ነበር።
14:22b.MAT.014.022ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳይቱ ገብተው ወደ ማዶ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።
14:23b.MAT.014.023ሕዝቡንም አሰናብቶ ይጸልይ ዘንድ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ። በመሸም ጊዜ ብቻውን በዚያ ነበረ።
14:24b.MAT.014.024ታንኳይቱም አሁን በባሕር መካከል ሳለች፥ ነፋስ ከወደ ፊት ነበርና በማዕበል ትጨነቅ ነበር።
14:25b.MAT.014.025ከሌሊቱም በአራተኛው ክፍል ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ።
14:26b.MAT.014.026ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ። ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ።
14:27b.MAT.014.027ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ አላቸው።
14:28b.MAT.014.028ጴጥሮስም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ አንተስ ከሆንህ በውኃው ላይ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ አለው።
14:29b.MAT.014.029እርሱም። ና አለው። ጴጥሮስም ከታንኳይቱ ወርዶ ወደ ኢየሱስ ሊደርስ በውኃው ላይ ሄደ።
14:30b.MAT.014.030ነገር ግን የነፋሱን ኃይል አይቶ ፈራ፥ ሊሰጥምም በጀመረ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ አድነኝ ብሎ ጮኸ።
14:31b.MAT.014.031ወዲያውም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና። አንተ እምነት የጎደለህ፥ ስለምን ተጠራጠርህ? አለው።
14:32b.MAT.014.032ወደ ታንኳይቱም በወጡ ጊዜ ነፋሱ ተወ።
14:33b.MAT.014.033በታንኳይቱም የነበሩት። በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነህ ብለው ሰገዱለት።
14:34b.MAT.014.034ተሻግረውም ወደ ጌንሴሬጥ ምድር መጡ።
14:35b.MAT.014.035የዚያ ቦታ ሰዎችም ባወቁት ጊዜ በዙርያው ወዳለ አገር ሁሉ ላኩ፥ ሕመምተኞችንም ሁሉ ወደ እርሱ አመጡ፤
14:36b.MAT.014.036የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ።
15
15:1b.MAT.015.001በዚያን ጊዜ ጻፎችና ፈሪሳውያን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢየሱስ ቀረቡና።
15:2b.MAT.015.002ደቀ መዛሙርትህ ስለ ምን የሽማግሎችን ወግ ይተላለፋሉ? እንጀራ ሲበሉ እጃቸውን አይታጠቡምና አሉት።
15:3b.MAT.015.003እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው። እናንተስ ስለ ወጋችሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ስለ ምን ትተላለፋላችሁ?
15:4b.MAT.015.004እግዚአብሔር። አባትህንና እናትህን አክብር፤ ደግሞ። አባቱን ወይም እናቱን የሰደበ ፈጽሞ ይሙት ብሎአልና፤
15:5b.MAT.015.005እናንተ ግን። አባቱን ወይም እናቱን። ከእኔ የምትጠቀምበት መባ ነው የሚል ሁሉ፥
15:6b.MAT.015.006አባቱን ወይም እናቱን አያከብርም ትላላችሁ፤ ስለ ወጋችሁም የእግዚአብሔርን ቃል ሻራችሁ።
15:7b.MAT.015.007እናንተ ግብዞች፥ ኢሳይያስ ስለ እናንተ።
15:8b.MAT.015.008ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤
15:9b.MAT.015.009የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።
15:10b.MAT.015.010ሕዝቡንም ጠርቶ። ስሙ አስተውሉም፤
15:11b.MAT.015.011ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው አላቸው።
15:12b.MAT.015.012በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው። ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደ ተሰናከሉ አወቅህን? አሉት።
15:13b.MAT.015.013እርሱ ግን መልሶ። የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
15:14b.MAT.015.014ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው፤ ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጉድጓድ ይወድቃሉ አለ።
15:15b.MAT.015.015ጴጥሮስም መልሶ። ምሳሌውን ተርጕምልን አለው።
15:16b.MAT.015.016ኢየሱስም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ እስካሁን የማታስተውሉ ናችሁን?
15:17b.MAT.015.017ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ አልፎ ወደ እዳሪ እንዲጣል አትመለከቱምን?
15:18b.MAT.015.018ከአፍ የሚወጣ ግን ከልብ ይወጣል፥ ሰውንም የሚያረክሰው ያ ነው።
15:19b.MAT.015.019ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ ይወጣልና።
15:20b.MAT.015.020ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው እንጂ፥ ባልታጠበ እጅ መብላትስ ሰውን አያረክሰውም።
15:21b.MAT.015.021ኢየሱስም ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ወደ ሲዶና አገር ሄደ።
15:22b.MAT.015.022እነሆም፥ ከነናዊት ሴት ከዚያ አገር ወጥታ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል ብላ ጮኸች።
15:23b.MAT.015.023እርሱ ግን አንዳች አልመለሰላትም። ደቀ መዛሙርቱም ቀርበው። በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት እያሉ ለመኑት።
15:24b.MAT.015.024እርሱም መልሶ። ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች በቀር አልተላክሁም አለ።
15:25b.MAT.015.025እርስዋ ግን መጥታ። ጌታ ሆይ፥ እርዳኝ እያለች ሰገደችለት።
15:26b.MAT.015.026እርሱ ግን መልሶ። የልጆችን እንጀራ ይዞ ለቡችሎች መጣል አይገባም አለ።
15:27b.MAT.015.027እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ አለች።
15:28b.MAT.015.028በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ። አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።
15:29b.MAT.015.029ኢየሱስም ከዚያ አልፎ ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ መጣ፥ ወደ ተራራም ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ።
15:30b.MAT.015.030ብዙ ሕዝብም አንካሶችን፥ ዕውሮችንም፥ ዲዳዎችንም፥ ጉንድሾችንም፥ ሌሎችንም ብዙ ይዘው ወደ እርሱ ቀረቡ፥ በኢየሱስም እግር አጠገብ ጣሉአቸው፤ ፈወሳቸውም፤
15:31b.MAT.015.031ስለዚህም ሕዝቡ ዲዳዎች ሲናገሩ፥ ጉንድሾችም ሲድኑ፥ አንካሶችም ሲሄዱ፥ ዕውሮችም ሲያዩ አይተው ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።
15:32b.MAT.015.032ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ። ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም አላቸው።
15:33b.MAT.015.033ደቀ መዛሙርቱም። ይህን ያህል ሕዝብ የሚያጠግብ ይህን ያህል እንጀራ በምድረ በዳ ከወዴት እናገኛለን? አሉት።
15:34b.MAT.015.034ኢየሱስም። ስንት እንጀራ አላችሁ? አላቸው። እነርሱም። ሰባት፥ ጥቂትም ትንሽ ዓሣ አሉት።
15:35b.MAT.015.035ሕዝቡም በምድር ላይ እንዲቀመጡ አዘዘ፤
15:36b.MAT.015.036ሰባቱንም እንጀራ ዓሣውንም ይዞ አመሰገነ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም ለሕዝቡ።
15:37b.MAT.015.037ሁሉም በሉና ጠገቡ፥ የተረፈውንም ቁርስራሽ ሰባት ቅርጫት ሙሉ አነሡ።
15:38b.MAT.015.038የበሉትም ከሴቶችና ከልጆች በቀር አራት ሺህ ወንዶች ነበሩ።
15:39b.MAT.015.039ሕዝቡንም ካሰናበተ በኋላ ወደ ታንኳይቱ ገብቶ ወደ መጌዶል አገር መጣ።
16
16:1b.MAT.016.001ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያንም ቀርበው ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ለመኑት።
16:2b.MAT.016.002እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አላቸው። በመሸ ጊዜ። ሰማዩ ቀልቶአልና ብራ ይሆናል ትላላችሁ፤
16:3b.MAT.016.003ማለዳም። ሰማዩ ደምኖ ቀልቶአልና ዛሬ ይዘንባል ትላላችሁ። የሰማዩን ፊትማ መለየት ታውቃላችሁ፥ የዘመኑንስ ምልክት መለየት አትችሉምን?
16:4b.MAT.016.004ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም። ትቶአቸውም ሄደ።
16:5b.MAT.016.005ደቀ መዛሙርቱም ወደ ማዶ በመጡ ጊዜ እንጀራ መያዝን ረሱ።
16:6b.MAT.016.006ኢየሱስም። ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ አላቸው።
16:7b.MAT.016.007እነርሱም። እንጀራ ባንይዝ ነው ብለው እርስ በርሳቸው ተነጋገሩ።
16:8b.MAT.016.008ኢየሱስም አውቆ እንዲህ አላቸው። እናንተ እምነት የጐደላችሁ፥ እንጀራ ስለ ሌላችሁ ስለ ምን እርስ በርሳችሁ ትነጋገራላችሁ? ገና አታስተውሉምን?
16:9b.MAT.016.009ለአምስቱ ሺህ አምስቱ እንጀራ፥ ስንት መሶብም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?
16:10b.MAT.016.010ወይስ ለአራቱ ሺህ ሰባቱ እንጀራ፥ ስንት ቅርጫትም እንዳነሣችሁ ትዝ አይላችሁምን?
16:11b.MAT.016.011ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ እንድትጠበቁ ብዬ ስለ እንጀራ እንዳልተናገርኋችሁ እንዴት አታስተውሉምን?
16:12b.MAT.016.012እነርሱም ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት እንጂ ከእንጀራ እርሾ እንዲጠበቁ እንዳላላቸው ያን ጊዜ አስተዋሉ።
16:13b.MAT.016.013ኢየሱስም ወደ ፊልጶስ ቂሣርያ አገር በደረሰ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን። ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል? ብሎ ጠየቀ።
16:14b.MAT.016.014እነርሱም። አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ፥ ሌሎችም ኤልያስ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ አሉት።
16:15b.MAT.016.015እርሱም። እናንተስ እኔን ማን እንደ ሆንሁ ትላላችሁ? አላቸው።
16:16b.MAT.016.016ስምዖን ጴጥሮስም መልሶ። አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ አለ።
16:17b.MAT.016.017ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው። የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ፥ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ።
16:18b.MAT.016.018እኔም እልሃለሁ፥ አንተ ጴጥሮስ ነህ፥ በዚችም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራለሁ፥ የገሃነም ደጆችም አይችሉአትም።
16:19b.MAT.016.019የመንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።
16:20b.MAT.016.020ያን ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ለማንም እንዳይነግሩ ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው።
16:21b.MAT.016.021ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።
16:22b.MAT.016.022ጴጥሮስም ወደ እርሱ ወስዶ። አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገሥጸው ጀመረ።
16:23b.MAT.016.023እርሱ ግን ዘወር ብሎ ጴጥሮስን። ወደ ኋላዬ ሂድ፥ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።
16:24b.MAT.016.024በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ። እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ።
16:25b.MAT.016.025ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል።
16:26b.MAT.016.026ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጐድል ምን ይጠቅመዋል? ወይስ ሰው ስለ ነፍሱ ቤዛ ምን ይሰጣል?
16:27b.MAT.016.027የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በአባቱ ክብር ይመጣ ዘንድ አለውና፤ ያን ጊዜም ለሁሉ እንደ ሥራው ያስረክበዋል።
16:28b.MAT.016.028እውነት እላችኋለሁ፥ የሰው ልጅ በመንግሥቱ ሲመጣ እስኪያዩ ድረስ እዚህ ከሚቆሙት ሞትን የማይቀምሱ አንዳንድ አሉ።
17
17:1b.MAT.017.001ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው።
17:2b.MAT.017.002በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ።
17:3b.MAT.017.003እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው።
17:4b.MAT.017.004ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ።
17:5b.MAT.017.005እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
17:6b.MAT.017.006ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው በፊታቸው ወደቁ እጅግም ፈርተው ነበር።
17:7b.MAT.017.007ኢየሱስም ቀርቦ ዳሰሳቸውና። ተነሡ አትፍሩም አላቸው።
17:8b.MAT.017.008ዓይናቸውንም አቅንተው ሲያዩ ከኢየሱስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም።
17:9b.MAT.017.009ከተራራውም በወረዱ ጊዜ ኢየሱስ። የሰው ልጅ ከሙታን እስኪነሣ ድረስ ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ ብሎ አዘዛቸው።
17:10b.MAT.017.010ደቀ መዛሙርቱም። እንግዲህ ጻፎች። ኤልያስ አስቀድሞ ሊመጣ ይገባዋል ስለ ምን ይላሉ? ብለው ጠየቁት።
17:11b.MAT.017.011ኢየሱስም መልሶ። ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል ሁሉንም ያቀናል፤
17:12b.MAT.017.012ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ኤልያስ ከዚህ በፊት መጣ፤ የወደዱትንም ሁሉ አደረጉበት እንጂ አላወቁትም፤ እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ ከእነርሱ መከራ ይቀበል ዘንድ አለው አላቸው።
17:13b.MAT.017.013በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ መጥምቁ ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ።
17:14b.MAT.017.014ወደ ሕዝቡም ሲደርሱ አንድ ሰው ወደ እርሱ ቀረበና ተንበርክኮ። ጌታ ሆይ፥ ልጄን ማርልኝ፥ በጨረቃ እየተነሣበት ክፉኛ ይሣቀያልና፤
17:15b.MAT.017.015ብዙ ጊዜ በእሳት ብዙ ጊዜም በውኃ ይወድቃልና።
17:16b.MAT.017.016ወደ ደቀ መዛሙርትህም አመጣሁት ሊፈውሱትም አቃታቸው አለው።
17:17b.MAT.017.017ኢየሱስም መልሶ። የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ወደዚህ ወደ እኔ አምጡት አለ።
17:18b.MAT.017.018ኢየሱስም ገሠጸው ጋኔኑም ከእርሱ ወጣ፥ ብላቴናውም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰ።
17:19b.MAT.017.019ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀረቡና። እኛ ልናወጣው ያልቻልን ስለ ምን ነው? አሉት።
17:20b.MAT.017.020ኢየሱስም። ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።
17:21b.MAT.017.021ይህ ዓይነት ግን ከጸሎትና ከጦም በቀር አይወጣም አላቸው።
17:22b.MAT.017.022በገሊላም ሲመላለሱ ኢየሱስ። የሰው ልጅ በሰዎች እጅ አልፎ ይሰጥ ዘንድ አለው፥ ይገድሉትማል፥
17:23b.MAT.017.023በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው። እጅግም አዘኑ።
17:24b.MAT.017.024ወደ ቅፍርናሆምም በመጡ ጊዜ ግብር የሚቀበሉ ሰዎች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና። መምህራችሁ ሁለቱን ዲናር*ፍ1* አይገብርምን? አሉት።
17:25b.MAT.017.025አዎን ይገብራል አለ። ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ። ስምዖን ሆይ፥ ምን ይመስልሃል? የምድር ነገሥታት ቀረጥና ግብር ከማን ይቀበላሉ? ከልጆቻቸውን ወይስ ከእንግዶች? አለው።
17:26b.MAT.017.026ጴጥሮስም። ከእንግዶች ባለው ጊዜ ኢየሱስ። እንኪያስ ልጆቻቸው ነጻ ናቸው።
17:27b.MAT.017.027ነገር ግን እንዳናሰናክላቸው፥ ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል፥ መጀመሪያም የሚወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር*ፍ2* ታገኛለህ፤ ያን ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ስጣቸው አለው። ፍ1 አንድ ዲናር አምሳ የኢት@ ብር ሳንቲም ያህል ነው። ፍ2 እስታቴር ሁለት ብር ያህል ነው።
18
18:1b.MAT.018.001በዚያች ሰዓት ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚበልጥ ማን ይሆን? አሉት።
18:2b.MAT.018.002ሕፃንም ጠርቶ በመካከላቸው አቆመ
18:3b.MAT.018.003እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ካልተመለሳችሁ እንደ ሕፃናትም ካልሆናችሁ፥ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።
18:4b.MAT.018.004እንግዲህ እንደዚህ ሕፃን ራሱን የሚያዋርድ ሁሉ፥ በመንግሥተ ሰማያት የሚበልጥ እርሱ ነው።
18:5b.MAT.018.005እንደዚህም ያለውን አንድ ሕፃን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤
18:6b.MAT.018.006በእኔም ከሚያምኑ ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ሁሉ፥ የወፍጮ ድንጋይ በአንገቱ ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም ይሻለው ነበር።
18:7b.MAT.018.007ወዮ ለዓለም ስለ ማሰናከያ፤ ማሰናከያ ሳይመጣ አይቀርምና፥ ነገር ግን በእርሱ ጠንቅ ማሰናከያ ለሚመጣበት ለዚያ ሰው ወዮለት።
18:8b.MAT.018.008እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል።
18:9b.MAT.018.009ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል።
18:10b.MAT.018.010ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና።
18:11b.MAT.018.011የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።
18:12b.MAT.018.012ምን ይመስላችኋል? ለአንድ ሰው መቶ በጎች ቢኖሩት ከእነርሱም አንዱ ቢባዝን፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ትቶ ሄዶም የባዘነውን አይፈልግምን?
18:13b.MAT.018.013ቢያገኘውም፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ካልባዘኑቱ ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ በእርሱ ደስ ይለዋል።
18:14b.MAT.018.014እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም።
18:15b.MAT.018.015ወንድምህም ቢበድልህ፥ ሄደህ አንተና እርሱ ብቻችሁን ሆናችሁ ውቀሰው። ቢሰማህ፥ ወንድምህን ገንዘብ አደረግኸው፤
18:16b.MAT.018.016ባይሰማህ ግን፥ በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤
18:17b.MAT.018.017እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።
18:18b.MAT.018.018እውነት እላችኋለሁ፥ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።
18:19b.MAT.018.019ደግሞ እላችኋለሁ፥ ከእናንተ ሁለቱ በምድር በማናቸውም በሚለምኑት ነገር ሁሉ ቢስማሙ በሰማያት ካለው ከአባቴ ዘንድ ይደረግላቸዋል።
18:20b.MAT.018.020ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።
18:21b.MAT.018.021በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ወደ እርሱ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? አለው።
18:22b.MAT.018.022ኢየሱስ እንዲህ አለው። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።
18:23b.MAT.018.023ስለዚህ መንግሥተ ሰማያት ባሮቹን ሊቈጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች።
18:24b.MAT.018.024መቈጣጠርም በጀመረ ጊዜ፥ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ።
18:25b.MAT.018.025የሚከፍለውም ቢያጣ፥ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ጌታው አዘዘ።
18:26b.MAT.018.026ስለዚህ ባሪያው ወድቆ ሰገደለትና። ጌታ ሆይ፥ ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው።
18:27b.MAT.018.027የዚያም ባሪያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፥ ዕዳውንም ተወለት።
18:28b.MAT.018.028ነገር ግን ያ ባሪያ ወጥቶ ከባልንጀሮቹ ከባሮቹ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና። ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው።
18:29b.MAT.018.029ስለዚህ ባልንጀራው ባሪያ ወድቆ። ታገሠኝ፥ ሁሉንም እከፍልሃለሁ ብሎ ለመነው።
18:30b.MAT.018.030እርሱም አልወደደም፥ ግን ሄዶ ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ በወኅኒ አኖረው።
18:31b.MAT.018.031ባልንጀሮቹ የሆኑ ባሮችም ያደረገውን አይተው እጅግ አዘኑ፥ መጥተውም የሆነውን ሁሉ ለጌታቸው ገለጡ።
18:32b.MAT.018.032ከዚያ ወዲያ ጌታው ጠርቶ። አንተ ክፉ ባሪያ፥ ስለ ለመንኸኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤
18:33b.MAT.018.033እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህ የሆነውን ያን ባሪያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን? አለው።
18:34b.MAT.018.034ጌታውም ተቈጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚሣቅዩት አሳልፎ ሰጠው።
18:35b.MAT.018.035ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፥ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።
19
19:1b.MAT.019.001ኢየሱስም ይህን ነገር ከፈጸመ በኋላ፥ ከገሊላ ሄዶ ወደ ይሁዳ አውራጃ ወደ ዮርዳኖስ ማዶ መጣ።
19:2b.MAT.019.002ብዙ ሕዝብም ተከተሉት፥ በዚያም ፈወሳቸው።
19:3b.MAT.019.003ፈሪሳውያንም ወደ እርሱ ቀረቡና ሲፈትኑት። ሰው በሆነው ምክንያት ሁሉ ሚስቱን ሊፈታ ተፈቅዶለታልን? አሉት።
19:4b.MAT.019.004እርሱ ግን መልሶ እንዲህ አለ። ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድና ሴት አደረጋቸው፥
19:5b.MAT.019.005አለም። ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፥ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፥ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?
19:6b.MAT.019.006ስለዚህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ወደ ፊት ሁለት አይደሉም። እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው።
19:7b.MAT.019.007እነርሱም። እንኪያስ ሙሴ የፍችዋን ጽሕፈት ሰጥተው እንዲፈቱአት ስለ ምን አዘዘ? አሉት።
19:8b.MAT.019.008እርሱም። ሙሴስ ስለ ልባችሁ ጥንካሬ ሚስቶቻችሁን ትፈቱ ዘንድ ፈቀደላችሁ፤ ከጥንት ግን እንዲህ አልነበረም።
19:9b.MAT.019.009እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው።
19:10b.MAT.019.010ደቀ መዛሙርቱም። የባልና የሚስት ሥርዓት እንዲህ ከሆነ መጋባት አይጠቅምም አሉት።
19:11b.MAT.019.011እርሱ ግን። ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤
19:12b.MAT.019.012በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው አላቸው።
19:13b.MAT.019.013በዚያን ጊዜ እጁን እንዲጭንባቸውና እንዲጸልይ ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ገሠጹአቸው።
19:14b.MAT.019.014ነገር ግን ኢየሱስ። ሕፃናትን ተዉአቸው፥ ወደ እኔም ይመጡ ዘንድ አትከልክሉአቸው፤ መንግሥተ ሰማያት እንደነዚህ ላሉ ናትና አለ፤
19:15b.MAT.019.015እጁንም ጫነባቸውና ከዚያ ሄደ።
19:16b.MAT.019.016እነሆም፥ አንድ ሰው ቀርቦ። መምህር ሆይ፥ የዘላለምን ሕይወት እንዳገኝ ምን መልካም ነገር ላድርግ? አለው።
19:17b.MAT.019.017እርሱም። ስለ መልካም ነገር ለምን ትጠይቀኛለህ? መልካም የሆነ አንድ ነው፤ ወደ ሕይወት መግባት ብትወድ ግን ትእዛዛትን ጠብቅ አለው።
19:18b.MAT.019.018እርሱም። የትኞችን? አለው። ኢየሱስም። አትግደል፥ አታመንዝር፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥
19:19b.MAT.019.019አባትህንና እናትህን አክብር፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ አለው።
19:20b.MAT.019.020ጐበዙም። ይህንማ ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ፥ ደግሞስ የሚጐድለኝ ምንድር ነው? አለው።
19:21b.MAT.019.021ኢየሱስም። ፍጹም ልትሆን ብትወድ፥ ሂድና ያለህን ሸጠህ ለድሆች ስጥ፥ መዝገብም በሰማያት ታገኛለህ፥ መጥተህም ተከተለኝ አለው።
19:22b.MAT.019.022ጐበዙም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነ ሄደ።
19:23b.MAT.019.023ኢየሱስም ለደቀ መዛሙርቱ። እውነት እላችኋለሁ፥ ለባለጠጋ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ጭንቅ ነው።
19:24b.MAT.019.024ዳግመኛም እላችኋለሁ፥ ባለጠጋ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል አለ።
19:25b.MAT.019.025ደቀ መዛሙርቱም ሰምተው እጅግ ተገረሙና። እንኪያስ ማን ሊድን ይችላል? አሉ።
19:26b.MAT.019.026ኢየሱስም እነርሱን ተመልክቶ። ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል አላቸው።
19:27b.MAT.019.027በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ። እነሆ፥ እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ፤ እንኪያስ ምን እናገኝ ይሆን? አለው።
19:28b.MAT.019.028ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ እናንተስ የተከተላችሁኝ፥ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጊዜ፥ እናንተ ደግሞ በአሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ስትፈርዱ በአሥራ ሁለት ዙፋን ትቀመጣላችሁ።
19:29b.MAT.019.029ስለ ስሜም ቤቶችን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ መቶ እጥፍ ይቀበላል የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።
19:30b.MAT.019.030ነገር ግን ብዙዎቹ ፊተኞች ኋለኞች፥ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።
20
20:1b.MAT.020.001መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ አትክልት ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ሰውን ትመስላለችና።
20:2b.MAT.020.002ሠራተኞችንም በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው።
20:3b.MAT.020.003በሦስት ሰዓትም ወጥቶ ሥራ የፈቱ ሌሎችን በአደባባይ ቆመው አየ፥
20:4b.MAT.020.004እነዚያንም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ አላቸው። እነርሱም ሄዱ።
20:5b.MAT.020.005ደግሞም በስድስትና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ።
20:6b.MAT.020.006በአሥራ አንደኛውም ሰዓት ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና። ሥራ ፈትታችሁ ቀኑን ሁሉ በዚህ ስለ ምን ትቆማላችሁ? አላቸው።
20:7b.MAT.020.007የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው አሉት። እርሱም። እናንተ ደግሞ ወደ ወይኔ አትክልት ሂዱ የሚገባውንም ትቀበላላችሁ አላቸው።
20:8b.MAT.020.008በመሸም ጊዜ የወይኑ አትክልት ጌታ አዛዡን። ሠራተኞችን ጥራና ከኋለኞች ጀምረህ እስከ ፊተኞች ድረስ ደመወዝ ስጣቸው አለው።
20:9b.MAT.020.009በአሥራ አንደኛው ሰዓትም የገቡ መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።
20:10b.MAT.020.010ፊተኞችም በመጡ ጊዜ አብዝተው የሚቀበሉ መስሎአቸው ነበር፤ እነርሱም ደግሞ እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር ተቀበሉ።
20:11b.MAT.020.011ተቀብለውም። እነዚህ ኋለኞች አንድ ሰዓት ሠሩ፥ የቀኑንም ድካምና ትኩሳት ከተሸከምን ከእኛ ጋር አስተካከልሃቸው ብለው በባለቤቱ ላይ አንጐራጐሩ።
20:13b.MAT.020.013እርሱ ግን መልሶ ከእነርሱ ለአንዱ እንዲህ አለው። ወዳጄ ሆይ፥ አልበደልሁህም በአንድ ዲናር አልተስማማኸኝምን?
20:14b.MAT.020.014ድርሻህን ውሰድና ሂድ፤ እኔ ለዚህ ለኋለኛው እንደ አንተ ልሰጠው እወዳለሁ፤ በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን?
20:15b.MAT.020.015ወይስ እኔ መልካም ስለ ሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን?
20:16b.MAT.020.016እንዲሁ ኋለኞች ፊተኞች፥ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ፤ የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።
20:17b.MAT.020.017ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ሊወጣ ሳለ፥ በመንገድ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ብቻቸውን ወደ እርሱ አቅርቦ።
20:18b.MAT.020.018እነሆ፥ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፥
20:19b.MAT.020.019ሊዘባበቱበትም ሊገርፉትም ሊሰቅሉትም ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል አላቸው።
20:20b.MAT.020.020በዚያን ጊዜ የዘብዴዎስ ልጆች እናት ከልጆችዋ ጋር እየሰገደችና አንድ ነገር እየለመነች ወደ እርሱ ቀረበች።
20:21b.MAT.020.021እርሱም። ምን ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም። እነዚህ ሁለቱ ልጆቼ አንዱ በቀኝህ አንዱም በግራህ በመንግሥትህ እንዲቀመጡ እዘዝ አለችው።
20:22b.MAT.020.022ኢየሱስ ግን መልሶ። የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ ልጠጣው ያለውን ጽዋ ልትጠጡ እኔም የምጠመቀውን ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን? አለ። እንችላለን አሉት።
20:23b.MAT.020.023እርሱም። ጽዋዬንስ ትጠጣላችሁ፤ በቀኝና በግራ መቀመጥ ግን ከአባቴ ዘንድ ለተዘጋጀላቸው ነው እንጂ እኔ የምሰጥ አይደለሁም አላቸው።
20:24b.MAT.020.024አሥሩም ሰምተው በሁለቱ ወንድማማች ተቈጡ።
20:25b.MAT.020.025ኢየሱስ ግን ወደ እርሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው። የአሕዛብ አለቆች እንዲገዙአቸው ታላላቆቹም በላያቸው እንዲሠለጥኑ ታውቃላችሁ።
20:26b.MAT.020.026በእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ የእናንተ አገልጋይ ይሁን፥
20:27b.MAT.020.027ከእናንተም ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፤
20:28b.MAT.020.028እንዲሁም የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም።
20:29b.MAT.020.029ከኢያሪኮም ሲወጡ ብዙ ሕዝብ ተከተሉት።
20:30b.MAT.020.030እነሆም፥ ሁለት ዕውሮች በመንገድ ዳር ተቀምጠው፥ ኢየሱስ እንዲያልፍ በሰሙ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን ብለው ጮኹ።
20:31b.MAT.020.031ሕዝቡም ዝም እንዲሉ ገሠጹአቸው፤ እነርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ የዳዊት ልጅ፥ ማረን እያሉ አብዝተው ጮኹ።
20:32b.MAT.020.032ኢየሱስም ቆሞ ጠራቸውና። ምን ላደርግላችሁ ትወዳላችሁ? አለ።
20:33b.MAT.020.033ጌታ ሆይ፥ ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ አሉት።
20:34b.MAT.020.034ኢየሱስም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፥ ወዲያውም አዩና ተከተሉት።
21
21:1b.MAT.021.001ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ፥ ያንጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፥
21:2b.MAT.021.002እንዲህም አላቸው። በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፥ በዚያን ጊዜም የታሰረችን አህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ።
21:3b.MAT.021.003ማንም አንዳች ቢላችሁ። ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል።
21:4b.MAT.021.004ለጽዮን ልጅ። እነሆ፥ ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት ተብሎ በነቢይ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ።
21:6b.MAT.021.006ደቀ መዛሙርቱም ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ፥
21:7b.MAT.021.007አህያይቱንና ውርንጫዋንም አመጡለት፥ ልብሳቸውንም በእነርሱ ላይ ጫኑ፥ ተቀመጠባቸውም።
21:8b.MAT.021.008ከሕዝቡም እጅግ ብዙዎች ልብሳቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፥ ሌሎችም ከዛፍ ጫፍ ጫፉን እየቈረጡ በመንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር።
21:9b.MAT.021.009የሚቀድሙትም ሕዝብ የሚከተሉትም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ይጮኹ ነበር።
21:10b.MAT.021.010ወደ ኢየሩሳሌምም በገባ ጊዜ መላው ከተማ። ይህ ማን ነው? ብሎ ተናወጠ።
21:11b.MAT.021.011ሕዝቡም። ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው አሉ።
21:12b.MAT.021.012ኢየሱስም ወደ መቅደስ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ፥ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና።
21:13b.MAT.021.013ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።
21:14b.MAT.021.014በመቅደስም ዕውሮችና አንካሶች ወደ እርሱ ቀረቡና ፈወሳቸው።
21:15b.MAT.021.015ነገር ግን የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ድንቃ ድንቅ በመቅደስም። ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ፥ ተቈጥተው።
21:16b.MAT.021.016እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን? አሉት። ኢየሱስም። እሰማለሁ፤ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን? አላቸው።
21:17b.MAT.021.017ትቶአቸውም ከከተማ ወደ ቢታንያ ወጣ በዚያም አደረ።
21:18b.MAT.021.018በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ።
21:19b.MAT.021.019በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።
21:20b.MAT.021.020ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ።
21:21b.MAT.021.021ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤
21:22b.MAT.021.022አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።
21:23b.MAT.021.023ወደ መቅደስም ገብቶ ሲያስተምር የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሎች ወደ እርሱ ቀረቡና። በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? አሉት።
21:24b.MAT.021.024ኢየሱስም መልሶ። እኔ ደግሞ አንዲት ነገር እጠይቃችኋለሁ፤ እናንተም ያችን ብትነግሩኝ እኔ ደግሞ እነዚህን በምን ሥልጣን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፤
21:25b.MAT.021.025የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይን ወይስ ከሰው? አላቸው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ። ከሰማይ ብንል። እንኪያስ ስለ ምን አላመናችሁበትም? ይለናል፤
21:26b.MAT.021.026ከሰው ግን ብንል፥ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ያዩታልና ሕዝቡን እንፈራለን አሉ።
21:27b.MAT.021.027ለኢየሱስም መልሰው። አናውቅም አሉት። እርሱም ደግሞ። እኔም በምን ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ አልነግራችሁም አላቸው።
21:28b.MAT.021.028ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ። ልጄ ሆይ፥ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው።
21:29b.MAT.021.029እርሱም መልሶ። አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ።
21:30b.MAT.021.030ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ። እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም።
21:31b.MAT.021.031ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው? ፊተኛው አሉት። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። እውነት እላችኋለሁ፥ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል።
21:32b.MAT.021.032ዮሐንስ በጽድቅ መንገድ መጥቶላችሁ ነበርና፥ አላመናችሁበትም፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ግን አመኑበት፤ እናንተም ይህን አይታችሁ ታምኑበት ዘንድ በኋላ ንስሐ አልገባችሁም።
21:33b.MAT.021.033ሌላ ምሳሌ ስሙ። የወይን አትክልት የተከለ ባለቤት ሰው ነበረ፤ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።
21:34b.MAT.021.034የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ፥ ፍሬውን ሊቀበሉ ባሮቹን ወደ ገበሬዎች ላከ።
21:35b.MAT.021.035ገበሬዎቹም ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውንም ወገሩት።
21:36b.MAT.021.036ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ፥ እንዲሁም አደረጉባቸው።
21:37b.MAT.021.037በኋላ ግን። ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው።
21:38b.MAT.021.038ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው። ወራሹ ይህ ነው፤ ኑ፥ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ።
21:39b.MAT.021.039ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት።
21:40b.MAT.021.040እንግዲህ የወይኑ አትክልት ጌታ በሚመጣ ጊዜ በእነዚህ ገበሬዎች ምን ያደርግባቸዋል?
21:41b.MAT.021.041እነርሱም። ክፉዎችን በክፉ ያጠፋቸዋል፥ የወይኑንም አትክልት ፍሬውን በየጊዜው ለሚያስረክቡ ለሌሎች ገበሬዎች ይሰጠዋል አሉት።
21:42b.MAT.021.042ኢየሱስ እንዲህ አላቸው። ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ ሆነ፤ ይህም ከጌታ ዘንድ ሆነ፥ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ነው የሚለውን ከቶ በመጽሐፍ አላነበባችሁምን?
21:43b.MAT.021.043ስለዚህ እላችኋለሁ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት ከእናንተ ትወሰዳለች ፍሬዋንም ለሚያደርግ ሕዝብ ትሰጣለች።
21:44b.MAT.021.044በዚህም ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይቀጠቀጣል፤ ድንጋዩ ግን የሚወድቅበትን ሁሉ ይፈጨዋል።
21:45b.MAT.021.045የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ምሳሌዎቹን ሰምተው ስለ እነርሱ እንደ ተናገረ አስተዋሉ፤
21:46b.MAT.021.046ሊይዙትም ሲፈልጉት ሳሉ ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስላዩት ፈሩአቸው።
22
22:1b.MAT.022.001ኢየሱስም መለሰ ደግሞም በምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ።
22:2b.MAT.022.002መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሰርግ ያደረገ ንጉሥን ትመስላለች።
22:3b.MAT.022.003የታደሙትንም ወደ ሰርጉ ይጠሩ ዘንድ ባሮቹን ላከ ሊመጡም አልወደዱም።
22:4b.MAT.022.004ደግሞ ሌሎችን ባሮች ልኮ። የታደሙትን። እነሆ፥ ድግሴን አዘጋጀሁ፥ ኮርማዎቼና የሰቡት ከብቶቼ ታርደዋል፥ ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ በሉአቸው አለ።
22:5b.MAT.022.005እነርሱ ግን ቸል ብለው አንዱ ወደ እርሻው፥ ሌላውም ወደ ንግዱ ሄደ፤
22:6b.MAT.022.006የቀሩትም ባሮቹን ይዘው አንገላቱአቸው ገደሉአቸውም።
22:7b.MAT.022.007ንጉሡም ተቈጣ፥ ጭፍሮቹንም ልኮ እነዚያን ገዳዮች አጠፋ፤ ከተማቸውንም አቃጠለ።
22:8b.MAT.022.008በዚያን ጊዜ ባሮቹን። ሰርጉስ ተዘጋጅቶአል፥ ነገር ግን የታደሙት የማይገባቸው ሆኑ፤
22:9b.MAT.022.009እንግዲህ ወደ መንገድ መተላለፊያ ሄዳችሁ ያገኛችሁትን ሁሉ ወደ ሰርጉ ጥሩ አለ።
22:10b.MAT.022.010እነዚያም ባሮች ወደ መንገድ ወጥተው ያገኙትን ሁሉ ክፉዎችንም በጎዎችንም ሰበሰቡ፤ የሰርጉንም ቤት ተቀማጮች ሞሉት።
22:11b.MAT.022.011ንጉሡም የተቀመጡትን ለማየት በገባ ጊዜ በዚያ የሰርግ ልብስ ያለበሰ አንድ ሰው አየና። ወዳጄ ሆይ፥
22:12b.MAT.022.012የሰርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት ወደዚህ ገባህ? አለው እርሱም ዝም አለ።
22:13b.MAT.022.013በዚያን ጊዜ ንጉሡ አገልጋዮቹን። እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል አለ።
22:14b.MAT.022.014የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና።
22:15b.MAT.022.015ስለዚህ ፈሪሳውያን ሄዱና እንዴት አድርገው በነገር እንዲያጠምዱት ተማከሩ።
22:16b.MAT.022.016ደቀ መዛሙርታቸውንም ከሄሮድስ ወገን ጋር ላኩበት፥ እነርሱም። መምህር ሆይ፥ እውነተኛ እንደ ሆንህ በእውነትም የእግዚአብሔርን መንገድ እንድታስተምር እናውቃለን፥ ለማንምም አታደላም፥ የሰውን ፊት አትመለከትምና፤
22:17b.MAT.022.017እንግዲህ ምን ይመስልሃል? ንገረን ለቄሣር ግብር መስጠት ተፈቅዶአልን ወይስ አልተፈቀደም? አሉት።
22:18b.MAT.022.018ኢየሱስም ክፋታቸውን አውቆ። እናንተ ግብዞች፥ ስለ ምን ትፈትኑኛላችሁ?
22:19b.MAT.022.019የግብሩን ብር አሳዩኝ አለ። እነርሱም ዲናር አመጡለት።
22:20b.MAT.022.020እርሱም። ይህች መልክ ጽሕፈቲቱስ የማን ናት? አላቸው።
22:21b.MAT.022.021የቄሣር ነው አሉት። በዚያን ጊዜ። እንኪያስ የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ አላቸው።
22:22b.MAT.022.022ይህንም ሰምተው ተደነቁ፥ ትተውትም ሄዱ።
22:23b.MAT.022.023በዚያን ቀን። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ ቀረቡ፥
22:24b.MAT.022.024እንዲህም ብለው ጠየቁት። መምህር ሆይ፥ ሙሴ አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ሲሞት ወንድሙ ሚስቱን አግብቶ ለወንድሙ ዘር ይተካ አለ።
22:25b.MAT.022.025ሰባት ወንድማማች በእኛ ዘንድ ነበሩ፤ ፊተኛውም ሚስት አግብቶ ሞተ፥ ዘርም ስለሌለው ሚስቱን ለወንድሙ ተወለት፤
22:26b.MAT.022.026እንዲሁ ደግሞ ሁለተኛው ሦስተኛውም፥ እስከ ሰባተኛው ድረስ።
22:27b.MAT.022.027ከሁሉም በኋላ ሴቲቱ ሞተች።
22:28b.MAT.022.028ሁሉ አግብተዋታልና በትንሣኤ ቀንስ፥ ከሰባቱ ለማናቸው ሚስት ትሆናለች?
22:29b.MAT.022.029ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ።
22:30b.MAT.022.030በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም።
22:31b.MAT.022.031ስለ ትንሣኤ ሙታን ግን። እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።
22:33b.MAT.022.033ሕዝቡም ይህን ሰምተው በትምህርቱ ተገረሙ።
22:34b.MAT.022.034ፈሪሳውያንም ሰዱቃውያንን ዝም እንዳሰኛቸው በሰሙ ጊዜ አብረው ተሰበሰቡ።
22:35b.MAT.022.035ከእነርሱም አንድ ሕግ አዋቂ ሊፈትነው።
22:36b.MAT.022.036መምህር ሆይ፥ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ብሎ ጠየቀው።
22:37b.MAT.022.037ኢየሱስም እንዲህ አለው። ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።
22:38b.MAT.022.038ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።
22:39b.MAT.022.039ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም። ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።
22:40b.MAT.022.040በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።
22:41b.MAT.022.041ፈሪሳውያንም ተሰብስበው ሳሉ፥ ኢየሱስ። ስለ ክርስቶስ ምን ይመስላችኋል? የማንስ ልጅ ነው? ብሎ ጠየቃቸው። የዳዊት ልጅ ነው አሉት።
22:43b.MAT.022.043እርሱም። እንኪያስ ዳዊት። ጌታ ጌታዬን። ጠላቶችህን የእግርህ መረገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲል እንዴት በመንፈስ ጌታ ብሎ ይጠራዋል?
22:45b.MAT.022.045ዳዊትስ ጌታ ብሎ ከጠራው፥ እንዴት ልጁ ይሆናል? አላቸው።
22:46b.MAT.022.046አንድም ቃል ስንኳ ይመልስለት ዘንድ የተቻለው የለም፥ ከዚያ ቀንም ጀምሮ ወደ ፊት ማንም ሊጠይቀው አልደፈረም።
23
23:1b.MAT.023.001በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለሕዝቡና ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሎ ነገራቸው።
23:2b.MAT.023.002ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል።
23:3b.MAT.023.003ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፥ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።
23:4b.MAT.023.004ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም።
23:5b.MAT.023.005ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ፤ ስለዚህ አሽንክታባቸውን ያሰፋሉ ዘርፉንም ያስረዝማሉ፥
23:6b.MAT.023.006በምሳም የከበሬታ ስፍራ፥ በምኵራብም የከበሬታ ወንበር፥
23:7b.MAT.023.007በገበያም ሰላምታና። መምህር ሆይ መምህር ሆይ ተብለው እንዲጠሩ ይወዳሉ።
23:8b.MAT.023.008እናንተ ግን። መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ።
23:9b.MAT.023.009አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም። አባት ብላችሁ አትጥሩ።
23:10b.MAT.023.010ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና። ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።
23:11b.MAT.023.011ከእናንተም የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል።
23:12b.MAT.023.012ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል።
23:13b.MAT.023.013እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።
23:14b.MAT.023.014እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ።
23:15b.MAT.023.015እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።
23:16b.MAT.023.016እናንተ። ማንም በቤተ መቅደስ የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በቤተ መቅደስ ወርቅ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል የምትሉ፥ ዕውሮች መሪዎች፥ ወዮላችሁ።
23:17b.MAT.023.017እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? ወርቁ ነውን? ወይስ ወርቁን የቀደሰው ቤተ መቅደስ?
23:18b.MAT.023.018ደግማችሁም። ማንም በመሠዊያው የሚምል ምንም የለበትም፤ ማንም በላዩ ባለው መባ የሚምል ግን በመሐላው ይያዛል ትላላችሁ።
23:19b.MAT.023.019እናንተ ደንቆሮዎችና ዕውሮች፥ ማናቸው ይበልጣል? መባው ነውን? ወይስ መባውን የሚቀድሰው መሠዊያው?
23:20b.MAT.023.020እንግዲህ በመሠዊያው የሚምለው በእርሱና በእርሱ ላይ ባለው ሁሉ ይምላል፤
23:21b.MAT.023.021በቤተ መቅደስም የሚምለው በእርሱና በእርሱ በሚኖረው ይምላል፤
23:22b.MAT.023.022በሰማይም የሚምለው በእግዚአብሔር ዙፋንና በእርሱ ላይ በተቀመጠው ይምላል።
23:23b.MAT.023.023እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።
23:24b.MAT.023.024እናንተ ዕውሮች መሪዎች፥ ትንኝን የምታጠሩ ግመልንም የምትውጡ።
23:25b.MAT.023.025እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ።
23:26b.MAT.023.026አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፥ ውጭው ደግሞ ጥሩ እንዲሆን አስቀድመህ የጽዋውንና የወጭቱን ውስጡን አጥራ።
23:27b.MAT.023.027እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።
23:28b.MAT.023.028እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል።
23:29b.MAT.023.029እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ የጻድቃንንም መቃብር ስለምታስጌጡና።
23:30b.MAT.023.030በአባቶቻችን ዘመን ኖረን በሆነስ በነቢያት ደም ባልተባበርናቸውም ነበር ስለምትሉ፥ ወዮላችሁ።
23:31b.MAT.023.031እንግዲያስ የነቢያት ገዳዮች ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ።
23:32b.MAT.023.032እናንተ ደግሞ የአባቶቻችሁን መስፈሪያ ሙሉ።
23:33b.MAT.023.033እናንተ እባቦች፥ የእፉኝት ልጆች፥ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?
23:34b.MAT.023.034ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤
23:35b.MAT.023.035ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።
23:36b.MAT.023.036እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል።
23:37b.MAT.023.037ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም።
23:38b.MAT.023.038እነሆ፥ ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል።
23:39b.MAT.023.039እላችኋለሁና፥ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩኝም።
24
24:1b.MAT.024.001ኢየሱስም ከመቅደስ ወጥቶ ሄደ፥ ደቀ መዛሙርቱም የመቅደሱን ግንቦች ሊያሳዩት ቀረቡ።
24:2b.MAT.024.002እርሱ ግን መልሶ። ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፥ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም አላቸው።
24:3b.MAT.024.003እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው ወደ እርሱ ቀርበው። ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው? አሉት።
24:4b.MAT.024.004ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው። ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።
24:5b.MAT.024.005ብዙዎች። እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
24:6b.MAT.024.006ጦርንም የጦርንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠበቁ፥ አትደንግጡ፤ ዳሩ ግን መጨረሻው ገና ነው።
24:7b.MAT.024.007ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፥ ራብም ቸነፈርም የምድርም መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል፤
24:8b.MAT.024.008እነዚህም ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
24:9b.MAT.024.009በዚያን ጊዜ ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋል ይገድሉአችሁማል፥ ስለ ስሜም በአሕዛብ ሁሉ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።
24:10b.MAT.024.010በዚያን ጊዜም ብዙዎች ይሰናከላሉ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፤
24:11b.MAT.024.011ብዙ ሐሰተኞች ነቢያትም ይነሣሉ ብዙዎችንም ያስታሉ፤
24:12b.MAT.024.012ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች።
24:13b.MAT.024.013እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።
24:14b.MAT.024.014ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።
24:15b.MAT.024.015እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋትን ርኩሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥
24:16b.MAT.024.016በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉት ወደ ተራራዎች ይሽሹ፥
24:17b.MAT.024.017በሰገነትም ያለ በቤቱ ያለውን ሊወስድ አይውረድ፥
24:18b.MAT.024.018በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።
24:19b.MAT.024.019በዚያችም ወራት ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።
24:20b.MAT.024.020ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ፤
24:21b.MAT.024.021በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያልሆነ እንግዲህም ከቶ የማይሆን ታላቅ መከራ ይሆናልና።
24:22b.MAT.024.022እነዚያ ቀኖችስ ባያጥሩ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም ነበር፤ ነገር ግን እነዚያ ቀኖች ስለ ተመረጡት ሰዎች ያጥራሉ።
24:23b.MAT.024.023በዚያን ጊዜ ማንም። እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ ወይም። ከዚያ አለ ቢላችሁ አትመኑ፤
24:24b.MAT.024.024ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ምልክትና ድንቅ ያሳያሉ።
24:25b.MAT.024.025እነሆ፥ አስቀድሜ ነገርኋችሁ።
24:26b.MAT.024.026እንግዲህ። እነሆ፥ በበረሀ ነው ቢሉአችሁ፥ አትውጡ፤ እነሆ፥ በእልፍኝ ነው ቢሉአችሁ፥ አትመኑ፤
24:27b.MAT.024.027መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤
24:28b.MAT.024.028በድን ወዳለበት በዚያ አሞራዎች ይሰበሰባሉ።
24:29b.MAT.024.029ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፥ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥
24:30b.MAT.024.030የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ። በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፥ በዚያን ጊዜም የምድር ወገኖች ሁሉ ዋይ ዋይ ይላሉ፥ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፤
24:31b.MAT.024.031መላእክቱንም ከታላቅ መለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፥ ከሰማያትም ዳርቻ እስከ ዳርቻው ከአራቱ ነፋሳት ለእርሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።
24:32b.MAT.024.032ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤
24:33b.MAT.024.033እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ።
24:34b.MAT.024.034እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።
24:35b.MAT.024.035ሰማይና ምድር ያልፋሉ፥ ቃሌ ግን አያልፍም።
24:36b.MAT.024.036ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።
24:37b.MAT.024.037የኖኅ ዘመን እንደ ነበረ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና።
24:38b.MAT.024.038በዚያች ወራት ከጥፋት ውኃ በፊት፥ ኖኅ ወደ መርከብ እስከገባበት ቀን ድረስ፥ ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም እንደ ነበሩ፥
24:39b.MAT.024.039የጥፋት ውኃም መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ እንዳላወቁ፥ የሰው ልጅ መምጣት ደግሞ እንዲሁ ይሆናል።
24:40b.MAT.024.040በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤
24:41b.MAT.024.041ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ፤ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች።
24:42b.MAT.024.042ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
24:43b.MAT.024.043ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር።
24:44b.MAT.024.044ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።
24:45b.MAT.024.045እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎች ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?
24:46b.MAT.024.046ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤
24:47b.MAT.024.047እውነት እላችኋለሁ፥ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።
24:48b.MAT.024.048ያ ክፉ ባሪያ ግን። ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፥
24:49b.MAT.024.049ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፥
24:50b.MAT.024.050የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፥
24:51b.MAT.024.051ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፥ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
25
25:1b.MAT.025.001በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቆነጃጅትን ትመስላለች።
25:2b.MAT.025.002ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ።
25:3b.MAT.025.003ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤
25:4b.MAT.025.004ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።
25:5b.MAT.025.005ሙሽራውም በዘገየ ጊዜ ሁሉ እንቅልፍ እንቅልፍ አላቸውና ተኙ።
25:6b.MAT.025.006እኩል ሌሊትም ሲሆን። እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ።
25:7b.MAT.025.007በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።
25:8b.MAT.025.008ሰነፎቹም ልባሞቹን። መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።
25:9b.MAT.025.009ልባሞቹ ግን መልሰው። ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው።
25:10b.MAT.025.010ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።
25:11b.MAT.025.011በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና። ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፥ ክፈትልን አሉ።
25:12b.MAT.025.012እርሱ ግን መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ አላውቃችሁም አለ።
25:13b.MAT.025.013ቀኒቱንና ሰዓቲቱን አታውቁምና እንግዲህ ንቁ።
25:14b.MAT.025.014ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤
25:15b.MAT.025.015ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፥ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።
25:16b.MAT.025.016አምስት መክሊትም የተቀበለው ሄዶ ነገደበት ሌላም አምስት አተረፈ፤
25:17b.MAT.025.017እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ።
25:18b.MAT.025.018አንድ የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ገንዘብ ቀበረ።
25:19b.MAT.025.019ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቆጣጠራቸው።
25:20b.MAT.025.020አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና ሌላ አምስት መክሊት አስረክቦ። ጌታ ሆይ፥ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ አምስት መክሊት አተረፍሁበት አለ።
25:21b.MAT.025.021ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
25:22b.MAT.025.022ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ።
25:23b.MAT.025.023ጌታውም። መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው።
25:24b.MAT.025.024አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ። ጌታ ሆይ፥ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ፤
25:25b.MAT.025.025ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፥ መክሊትህ አለህ አለ።
25:26b.MAT.025.026ጌታውም መልሶ እንዲህ አለው። አንተ ክፉና ሃኬተኛ ባሪያ፥ ካልዘራሁባት እንዳጭድ ካልበተንሁባትም እንድሰበስብ ታውቃለህን?
25:27b.MAT.025.027ስለዚህ ገንዘቤን ለለዋጮች አደራ ልትሰጠው በተገባህ ነበር፥ እኔም መጥቼ ያለኝን ከትርፉ ጋር እወስደው ነበር።
25:28b.MAT.025.028ስለዚህ መክሊቱን ውሰዱበት አሥር መክሊትም ላለው ስጡት፤
25:29b.MAT.025.029ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
25:30b.MAT.025.030የማይጠቅመውንም ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ አውጡት፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
25:31b.MAT.025.031የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤
25:32b.MAT.025.032አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥
25:33b.MAT.025.033በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል።
25:34b.MAT.025.034ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።
25:35b.MAT.025.035ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥
25:36b.MAT.025.036ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና።
25:37b.MAT.025.037ጻድቃንም መልሰው ይሉታል። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ አይተን መቼ አበላንህስ? ወይስ ተጠምተህ አይተን መቼ አጠጣንህ?
25:38b.MAT.025.038እንግዳ ሆነህስ አይተን መቼ ተቀበልንህ? ወይስ ታርዘህ አይተን መቼ አለበስንህ?
25:39b.MAT.025.039ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ አይተን መቼ ወደ አንተ መጣን?
25:40b.MAT.025.040ንጉሡም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል።
25:41b.MAT.025.041በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።
25:42b.MAT.025.042ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥
25:43b.MAT.025.043ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና።
25:44b.MAT.025.044እነርሱ ደግሞ ይመልሱና። ጌታ ሆይ፥ ተርበህ ወይስ ተጠምተህ ወይስ እንግዳ ሆነህ ወይስ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ አይተን አላገለገልንህም? ይሉታል።
25:45b.MAT.025.045ያን ጊዜ። እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም ብሎ ይመልስላቸዋል።
25:46b.MAT.025.046እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።
26
26:1b.MAT.026.001ኢየሱስም እነዚህን ቃሎች ሁሉ በፈጸመ ጊዜ፥
26:2b.MAT.026.002ለደቀ መዛሙርቱ። ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፥ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል አለ።
26:3b.MAT.026.003በዚያን ጊዜ የካህናት አለቆች የሕዝብም ሽማግሎች ቀያፋ በሚባለው በሊቀ ካህናቱ ግቢ ተሰበሰቡ፥
26:4b.MAT.026.004ኢየሱስንም በተንኰል ሊያስይዙት ሊገድሉትም ተማከሩ፤
26:5b.MAT.026.005ነገር ግን። በሕዝቡ ዘንድ ሁከት እንዳይነሣ በበዓል አይሁን አሉ።
26:6b.MAT.026.006ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ፥
26:7b.MAT.026.007አንዲት ሴት ዋጋው እጅግ የበዛ ሽቱ የሞላው የአልባስጥሮስ ብልቃጥ ይዛ ወደ እርሱ ቀረበች በማዕድም ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው።
26:8b.MAT.026.008ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው ተቈጡና። ይህ ጥፋት ለምንድር ነው?
26:9b.MAT.026.009ይህ በብዙ ዋጋ ተሽጦ ለድሆች ሊሰጥ ይቻል ነበርና አሉ።
26:10b.MAT.026.010ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው። መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ?
26:11b.MAT.026.011ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም፤
26:12b.MAT.026.012እርስዋ ይህን ሽቱ በሰውነቴ ላይ አፍስሳ ለመቃብሬ አደረገች።
26:13b.MAT.026.013እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።
26:14b.MAT.026.014በዚያን ጊዜ የአስቆሮቱ ይሁዳ የሚባለው ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ወደ ካህናት አለቆች ሄዶ።
26:15b.MAT.026.015ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ? እነርሱም ሠላሳ ብር መዘኑለት።
26:16b.MAT.026.016ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ አሳልፎ ሊሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር።
26:17b.MAT.026.017በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት።
26:18b.MAT.026.018እርሱም። ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ። መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ።
26:19b.MAT.026.019ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ።
26:20b.MAT.026.020በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።
26:21b.MAT.026.021ሲበሉም። እውነት እላችኋለሁ፥ ከእናንተ አንዱ እኔን አሳልፎ ይሰጣል አለ።
26:22b.MAT.026.022እጅግም አዝነው እያንዳንዱ። ጌታ ሆይ፥ እኔ እሆንን? ይሉት ጀመር።
26:23b.MAT.026.023እርሱም መልሶ። ከእኔ ጋር እጁን በወጭቱ ያጠለቀ፥ እኔን አሳልፎ የሚሰጥ እርሱ ነው።
26:24b.MAT.026.024የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሄዳል፥ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት፤ ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር አለ።
26:25b.MAT.026.025አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳም መልሶ። መምህር ሆይ፥ እኔ እሆንን? አለ፤ አንተ አልህ አለው።
26:26b.MAT.026.026ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና። እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው አለ።
26:27b.MAT.026.027ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው እንዲህም አለ። ሁላችሁ ከእርሱ ጠጡ፤
26:28b.MAT.026.028ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።
26:29b.MAT.026.029ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በአባቴ መንግሥት ከእናንተ ጋር ከዚህ ከወይን ፍሬ አዲሱን እስከምጠጣበት እስከዚያ ቀን ድረስ ከዛሬ ጀምሬ አልጠጣውም።
26:30b.MAT.026.030መዝሙርም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ።
26:31b.MAT.026.031በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። በዚች ሌሊት ሁላችሁ በእኔ ትሰናከላላችሁ፤ እረኛውን እመታለሁ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ የሚል ተጽፎአልና፤
26:32b.MAT.026.032ከተነሣሁ በኋላ ግን ወደ ገሊላ እቀድማችኋለሁ አላቸው።
26:33b.MAT.026.033ጴጥሮስም መልሶ። ሁሉም በአንተ ቢሰናከሉ እኔ ከቶ አልሰናከልም አለው።
26:34b.MAT.026.034ኢየሱስ። እውነት እልሃለሁ፥ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ አለው።
26:35b.MAT.026.035ጴጥሮስ። ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልገኝ ቢሆን፥ ከቶ አልክድህም አለው። ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ደግሞ እንደዚሁ አሉ።
26:36b.MAT.026.036በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ከእነርሱ ጋር ጌቴሴማኒ ወደምትባል ስፍራ መጣ ደቀ መዛሙርቱንም። ወዲያ ሄጄ ስጸልይ ሳለ በዚህ ተቀመጡ አላቸው።
26:37b.MAT.026.037ጴጥሮስንም ሁለቱንም የዘብዴዎስን ልጆች ወስዶ ሊያዝን ሊተክዝም ጀመር።
26:38b.MAT.026.038ነፍሴ እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዘነች፤ በዚህ ቆዩ ከእኔም ጋር ትጉ አላቸው።
26:39b.MAT.026.039ጥቂትም ወደ ፊት እልፍ ብሎ በፊቱ ወደቀና ሲጸልይ። አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።
26:40b.MAT.026.040ወደ ደቀ መዛሙርቱም መጣ፤ ተኝተውም አገኛቸውና ጴጥሮስን። እንዲሁም ከእኔ ጋር አንዲት ሰዓት እንኳ ልትተጉ አልቻላችሁምን?
26:41b.MAT.026.041ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው አለው።
26:42b.MAT.026.042ደግሞ ሁለተኛ ሄዶ ጸለየና። አባቴ፥ ይህች ጽዋ ሳልጠጣት ታልፍ ዘንድ የማይቻል እንደ ሆነ፥ ፈቃድህ ትሁን አለ።
26:43b.MAT.026.043ደግሞም መጥቶ ዓይኖቻቸው በእንቅልፍ ከብደው ነበርና ተኝተው አገኛቸው።
26:44b.MAT.026.044ደግሞም ትቶአቸው ሄደ፥ ሦስተኛም ያንኑ ቃል ደግሞ ጸለየ።
26:45b.MAT.026.045ከዚያ ወዲያ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጥቶ። እንግዲህስ ተኙ ዕረፉም፤ እነሆ፥ ሰዓቲቱ ቀርባለች የሰው ልጅም በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ይሰጣል።
26:46b.MAT.026.046ተነሡ፥ እንሂድ፤ እነሆ፥ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቦአል አላቸው።
26:47b.MAT.026.047ይህንም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ መጣ፥ ከእርሱም ጋር ብዙ ሕዝብ ሰይፍና ጐመድ ይዘው ከካህናት አለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሎች ዘንድ መጡ።
26:48b.MAT.026.048አሳልፎ የሚሰጠውም። የምስመው እርሱ ነው፤ ያዙት ብሎ ምልክት ሰጥቶአቸው ነበር።
26:49b.MAT.026.049ወዲያውም ወደ ኢየሱስ ቀረበና። መምህር ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን ብሎ ሳመው።
26:50b.MAT.026.050ኢየሱስም። ወዳጄ ሆይ፥ ለምን ነገር መጣህ? አለው። በዚያን ጊዜ ቀረቡ እጃቸውንም በኢየሱስ ላይ ጭነው ያዙት።
26:51b.MAT.026.051እነሆም፥ ከኢየሱስ ጋር ከነበሩት አንዱ እጁን ዘርግቶ ሰይፉን መዘዘና የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን ቈረጠው።
26:52b.MAT.026.052በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለው። ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ።
26:53b.MAT.026.053ወይስ አባቴን እንድለምን እርሱም አሁን ከአሥራ ሁለት ጭፍሮች የሚበዙ መላእክት እንዲሰድልኝ የማይቻል ይመስልሃልን?
26:54b.MAT.026.054እንዲህ ከሆነስ። እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?
26:55b.MAT.026.055በዚያን ሰዓት ኢየሱስ ለሕዝቡ። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ልትይዙኝ ወጣችሁን? በመቅደስ ዕለት ዕለት እያስተማርሁ ከእናንተ ጋር ስቀመጥ ሳለሁ አልያዛችሁኝም።
26:56b.MAT.026.056ነገር ግን ይህ ሁሉ የሆነ የነቢያት መጻሕፍት ይፈጸሙ ዘንድ ነው አለ። በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ሁሉ ትተውት ሸሹ።
26:57b.MAT.026.057ኢየሱስን የያዙትም ጻፎችና ሽማግሎች ወደ ተከማቹበት ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወሰዱት።
26:58b.MAT.026.058ጴጥሮስ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስ ሩቅ ሆኖ ተከተለው፥ የነገሩንም ፍጻሜ ያይ ዘንድ ወደ ውስጥ ገብቶ ከሎሌዎቹ ጋር ተቀመጠ።
26:59b.MAT.026.059የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ሸንጐውም ሁሉ እንዲገድሉት በኢየሱስ ላይ የሐሰት ምስክር ይፈልጉ ነበር፥ አላገኙም፤
26:60b.MAT.026.060ብዙም የሐሰት ምስክሮች ምንም ቢቀርቡ አላገኙም።
26:61b.MAT.026.061በኋላም ሁለት ቀርበው። ይህ ሰው። የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ልሠራው እችላለሁ ብሎአል አሉ።
26:62b.MAT.026.062ሊቀ ካህናቱም ተነሥቶ። እነዚህ ለሚመሰክሩብህ አንድ ስንኳ አትመልስምን? አለው።
26:63b.MAT.026.063ኢየሱስ ግን ዝም አለ። ሊቀ ካህናቱም። አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ የሆንህ እንደ ሆነ እንድትነግረን በሕያው እግዚአብሔር አምልሃለሁ አለው።
26:64b.MAT.026.064ኢየሱስም። አንተ አልህ ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህ የሰው ልጅ በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ አለው።
26:65b.MAT.026.065በዚያን ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ልብሱን ቀዶ። ተሳድቦአል እንግዲህ ወዲህ ምስክሮች ስለ ምን ያስፈልገናል? እነሆ፥ ስድቡን አሁን ሰምታችኋል፤ ምን ይመስላችኋል? አለ።
26:66b.MAT.026.066እነርሱም። ሞት ይገባዋል ብለው መለሱ።
26:67b.MAT.026.067በዚያን ጊዜ በፊቱ ተፉበት፤ ጐሰሙትም፥ ሌሎችም በጥፊ መትተው። ክርስቶስ ሆይ፥ በጥፊ የመታህ ማን ነው?
26:68b.MAT.026.068ትንቢት ተናገርልን አሉ።
26:69b.MAT.026.069ጴጥሮስም ከቤት ውጭ በአጥሩ ግቢ ተቀምጦ ነበር፤ አንዲት ገረድም ወደ እርሱ ቀርባ። አንተ ደግሞ ከገሊላው ከኢየሱስ ጋር ነበርህ አለችው።
26:70b.MAT.026.070እርሱ ግን። የምትዪውን አላውቀውም ብሎ በሁሉ ፊት ካደ።
26:71b.MAT.026.071ወደ በሩም ሲወጣ ሌላይቱ አየችውና በዚያ ላሉት። ይህ ደግሞ ከናዝሬቱ ከኢየሱስ ጋር ነበረ አለች።
26:72b.MAT.026.072ዳግመኛም ሲምል። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ካደ።
26:73b.MAT.026.073ጥቂትም ቈይተው በዚያ ቆመው የነበሩ ቀርበው ጴጥሮስን። አነጋገርህ ይገልጥሃልና በእውነት አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አሉት።
26:74b.MAT.026.074በዚያን ጊዜ። ሰውየውን አላውቀውም ብሎ ሊራገምና ሊምል ጀመረ። ወዲያውም ዶሮ ጮኸ።
26:75b.MAT.026.075ጴጥሮስም። ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ያለው የኢየሱስ ቃል ትዝ አለው፤ ወደ ውጭም ወጥቶ መራራ ልቅሶ አለቀሰ።
27
27:1b.MAT.027.001ሲነጋም የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሎች ሁሉ ሊገድሉት በኢየሱስ ላይ ተማከሩ፤
27:2b.MAT.027.002አስረውም ወሰዱት፥ ለገዢው ለጴንጤናዊው ጲላጦስም አሳልፈው ሰጡት።
27:3b.MAT.027.003በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ።
27:4b.MAT.027.004ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን። እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ።
27:5b.MAT.027.005ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።
27:6b.MAT.027.006የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው። የደም ዋጋ ነውና ወደ መባ ልንጨምረው አልተፈቀደም አሉ።
27:7b.MAT.027.007ተማክረውም የሸክላ ሠሪውን መሬት ለእንግዶች መቃብር ገዙበት።
27:8b.MAT.027.008ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ የደም መሬት ተባለ።
27:9b.MAT.027.009በዚያን ጊዜ በነቢዩ በኤርምያስ የተባለው። ከእስራኤል ልጆችም አንዳንዶቹ የገመቱትን፥ የተገመተውን ዋጋ ሠላሳ ብር ያዙ፥
27:10b.MAT.027.010ጌታም እንዳዘዘኝ ስለ ሸክላ ሠሪ መሬት ሰጡት። የሚል ተፈጸመ።
27:11b.MAT.027.011ኢየሱስም በገዢው ፊት ቆመ፤ ገዢውም። የአይሁድ ንጉሥ አንተ ነህን? ብሎ ጠየቀው፤ ኢየሱስም። አንተ አልህ አለው።
27:12b.MAT.027.012የካህናት አለቆችም ሽማግሎችም ሲከሱት ምንም አልመለሰም።
27:13b.MAT.027.013በዚያን ጊዜ ጲላጦስ። ስንት ያህል እንዲመሰክሩብህ አትሰማምን? አለው።
27:14b.MAT.027.014ገዢውም እጅግ እስኪደነቅ ድረስ አንዲት ቃል ስንኳ አልመለሰለትም።
27:15b.MAT.027.015በዚያም በዓል ሕዝቡ የወደዱትን አንድ እስረኛ ሊፈታላቸው ለገዢው ልማድ ነበረው።
27:16b.MAT.027.016በዚያን ጊዜም በርባን የሚባል በጣም የታወቀ እስረኛ ነበራቸው።
27:17b.MAT.027.017እንግዲህ እነርሱ ተሰብስበው ሳሉ ጲላጦስ። በርባንን ወይስ ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤
27:18b.MAT.027.018በቅንዓት አሳልፈው እንደ ሰጡት ያውቅ ነበርና።
27:19b.MAT.027.019እርሱም በፍርድ ወንበር ተቀምጦ ሳለ ሚስቱ። ስለ እርሱ ዛሬ በሕልም እጅግ መከራ ተቀብያለሁና በዚያ ጻድቅ ሰው ምንም አታድርግ ብላ ላከችበት።
27:20b.MAT.027.020የካህናት አለቆችና ሽማግሎች ግን በርባንን እንዲለምኑ ኢየሱስን ግን እንዲያጠፉ ሕዝቡን አባበሉ።
27:21b.MAT.027.021ገዢውም መልሶ። ከሁለቱ ማንኛውን ልፈታላችሁ ትወዳላችሁ? አላቸው፤ እነርሱም። በርባንን አሉ።
27:22b.MAT.027.022ጲላጦስ። ክርስቶስ የተባለውን ኢየሱስን እንግዲህ ምን ላድርገው? አላቸው፤ ሁሉም። ይሰቀል አሉ።
27:23b.MAT.027.023ገዢውም። ምን ነው? ያደረገው ክፋት ምንድር ነው? አለ፤ እነርሱ ግን። ይሰቀል እያሉ ጩኸት አበዙ።
27:24b.MAT.027.024ጲላጦስም ሁከት እንዲጀመር እንጂ አንዳች እንዳይረባ ባየ ጊዜ፥ ውኃ አንሥቶ። እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ፤ እናንተ ተጠንቀቁ ሲል በሕዝቡ ፊት እጁን ታጠበ።
27:25b.MAT.027.025ሕዝቡም ሁሉ መልሰው። ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን አሉ።
27:26b.MAT.027.026በዚያን ጊዜ በርባንን ፈታላቸው፥ ኢየሱስን ግን ገርፎ ሊሰቀል አሳልፎ ሰጠ።
27:27b.MAT.027.027በዚያን ጊዜ የገዢው ወታደሮች ኢየሱስን ወደ ገዢው ግቢ ውስጥ ወሰዱት ጭፍራውንም ሁሉ ወደ እርሱ አከማቹ።
27:28b.MAT.027.028ልብሱንም ገፈው ቀይ ልብስ አለበሱት፥
27:29b.MAT.027.029ከእሾህም አክሊል ጎንጉነው በራሱ ላይ፥ በቀኝ እጁም መቃ አኖሩ፥ በፊቱም ተንበርክከው። የአይሁድ ንጉሥ ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን እያሉ ዘበቱበት፤
27:30b.MAT.027.030ተፉበትም መቃውንም ይዘው ራሱን መቱት።
27:31b.MAT.027.031ከዘበቱበትም በኋላ ቀዩን ልብስ ገፈፉት፥ ልብሱንም አለበሱት ሊሰቅሉትም ወሰዱት።
27:32b.MAT.027.032ሲወጡም ስምዖን የተባለው የቀሬናን ሰው አገኙ፤ እርሱንም መስቀሉን ይሸከም ዘንድ አስገደዱት።
27:33b.MAT.027.033ትርጓሜው የራስ ቅል ስፍራ ወደሚሆን ጎልጎታ ወደሚባለው ስፍራ በደረሱ ጊዜም፥
27:34b.MAT.027.034በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፤ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም።
27:35b.MAT.027.035ከሰቀሉትም በኋላ ልብሱን ዕጣ ጥለው ተካፈሉ፥
27:36b.MAT.027.036በዚያም ተቀምጠው ይጠብቁት ነበር።
27:37b.MAT.027.037ይህ ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ ነው የሚል የክሱን ጽሕፈት ከራሱ በላይ አኖሩ።
27:38b.MAT.027.038በዚያን ጊዜ ሁለት ወንበዶች አንዱ በቀኝ አንዱም በግራ ከእርሱ ጋር ተሰቀሉ።
27:39b.MAT.027.039የሚያልፉትም ራሳቸውን እየነቀነቁ ይሰድቡት ነበርና።
27:40b.MAT.027.040ቤተ መቅደስን የምታፈርስ በሦስት ቀንም የምትሠራው፥ ራስህን አድን፤ የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ ከመስቀል ውረድ አሉት።
27:41b.MAT.027.041እንዲሁም ደግሞ የካህናት አለቆች ከጻፎችና ከሽማግሎች ጋር እየዘበቱበት እንዲህ አሉ።
27:42b.MAT.027.042ሌሎችን አዳነ፥ ራሱን ሊያድን አይችልም፤ የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ፥ አሁን ከመስቀል ይውረድ እኛም እናምንበታለን።
27:43b.MAT.027.043በእግዚአብሔር ታምኖአል፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሎአልና ከወደደውስ አሁን ያድነው።
27:44b.MAT.027.044ከእርሱ ጋር የተሰቀሉት ወንበዶች ደግሞ ያንኑ እያሉ ይነቅፉት ነበር።
27:45b.MAT.027.045ከስድስት ሰዓትም ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ።
27:46b.MAT.027.046በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህም። አምላኬ አምላኬ፥ ስለ ምን ተውኸኝ? ማለት ነው።
27:47b.MAT.027.047በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። ይህስ ኤልያስን ይጠራል አሉ።
27:48b.MAT.027.048ወዲያውም ከእነርሱ አንዱ ሮጠ፤ ሰፍነግም ይዞ ሆምጣጤ ሞላበት፥ በመቃም አድርጎ አጠጣው።
27:49b.MAT.027.049ሌሎቹ ግን። ተው፥ ኤልያስ መጥቶ ያድነው እንደ ሆነ እንይ አሉ።
27:50b.MAT.027.050ኢየሱስም ሁለተኛ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ተወ።
27:51b.MAT.027.051እነሆም፥ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፥ ምድርም ተናወጠች፥ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤
27:52b.MAT.027.052መቃብሮችም ተከፈቱ፥ ተኝተው ከነበሩትም ከቅዱሳን ብዙ ሥጋዎች ተነሡ፤
27:53b.MAT.027.053ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ገቡና ለብዙዎች ታዩ።
27:54b.MAT.027.054የመቶ አለቃም ከእርሱም ጋር ኢየሱስን የሚጠብቁ መናወጡንና የሆነውን ነገር አይተው። ይህ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ ብለው እጅግ ፈሩ።
27:55b.MAT.027.055ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፤
27:56b.MAT.027.056ከእነርሱም መግደላዊት ማርያምና የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ነበሩ።
27:57b.MAT.027.057በመሸም ጊዜ ዮሴፍ የተባለው ባለ ጠጋ ሰው ከአርማትያስ መጣ፥ እርሱም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበረ፤
27:58b.MAT.027.058ይኸውም ወደ ጲላጦስ ቀርቦ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።
27:59b.MAT.027.059ጲላጦስም እንዲሰጡት አዘዘ። ዮሴፍም ሥጋውን ይዞ በንጹሕ በፍታ ከፈነው፥
27:60b.MAT.027.060ከዓለት በወቀረው በአዲሱ መቃብርም አኖረው፥ በመቃብሩም ደጃፍ ታላቅ ድንጋይ አንከባሎ ሄደ።
27:61b.MAT.027.061መግደላዊት ማርያምም ሁለተኛይቱም ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጠው በዚያ ነበሩ።
27:62b.MAT.027.062በማግሥቱም ከመዘጋጀት በኋላ በሚሆነው ቀን፥ የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ወደ ጲላጦስ ተሰበሰቡና።
27:63b.MAT.027.063ጌታ ሆይ፥ ያ አሳች በሕይወቱ ገና ሳለ። ከሦስት ቀን በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን።
27:64b.MAT.027.064እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው በሌሊት እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም። ከሙታን ተነሣ እንዳይሉ፥ የኋለኛይቱ ስሕተት ከፊተኛይቱ ይልቅ የከፋች ትሆናለችና መቃብሩ እስከ ሦስተኛ ቀን ድረስ እንዲጠበቅ እዘዝ አሉት።
27:65b.MAT.027.065ጲላጦስም። ጠባቆች አሉአችሁ፤ ሄዳችሁ እንዳወቃችሁ አስጠብቁ አላቸው።
27:66b.MAT.027.066እነርሱም ሄደው ከጠባቆች ጋር ድንጋዩን አትመው መቃብሩን አስጠበቁ።
28
28:1b.MAT.028.001በሰንበትም መጨረሻ መጀመሪያው ቀን ሲነጋ መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ።
28:2b.MAT.028.002እነሆም፥ የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ።
28:3b.MAT.028.003መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ።
28:4b.MAT.028.004ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ሆኑ።
28:5b.MAT.028.005መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፤
28:6b.MAT.028.006እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ።
28:7b.MAT.028.007ፈጥናችሁም ሂዱና። ከሙታን ተነሣ፥ እነሆም፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው።
28:8b.MAT.028.008እነሆም፥ ነገርኋችሁ። በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ሊያወሩ ሮጡ።
28:9b.MAT.028.009እነሆም፥ ኢየሱስ አገኛቸውና። ደስ ይበላችሁ አላቸው። እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት።
28:10b.MAT.028.010በዚያን ጊዜ ኢየሱስ። አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ተናገሩ፥ በዚያም ያዩኛል አላቸው።
28:11b.MAT.028.011ሲሄዱም ሳሉ እነሆ፥ ከጠባቆቹ አንዳንድ ወደ ከተማ መጥተው የሆነውን ሁሉ ለካህናት አለቆች አወሩ።
28:12b.MAT.028.012ከሽማግሎች ጋርም ተሰብስበው ተማከሩና ለጭፍሮች ብዙ ገንዘብ ሰጥተዋቸው።
28:13b.MAT.028.013እኛ ተኝተን ሳለን ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት በሉ።
28:14b.MAT.028.014ይህም በገዢው ዘንድ የተሰማ እንደ ሆነ፥ እኛ እናስረዳዋለን እናንተም ያለ ሥጋት እንድትሆኑ እናደርጋለን አሉአቸው።
28:15b.MAT.028.015እነርሱም ገንዘቡን ተቀብለው እንደ አስተማሩአቸው አደረጉ። ይህም ነገር በአይሁድ ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ሲወራ ይኖራል።
28:16b.MAT.028.016አሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥
28:17b.MAT.028.017ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ የተጠራጠሩ ግን ነበሩ።
28:18b.MAT.028.018ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።
28:19b.MAT.028.019እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።
- Holder of rights
- Multilingual Bible Corpus
- Citation Suggestion for this Object
- TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. Matthew (Amharic). Matthew (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8A88-3