Revelation (Amharic)
1
1:1b.REV.001.001ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥
1:2b.REV.001.002እርሱም ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ።
1:3b.REV.001.003ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው።
1:4b.REV.001.004ዮሐንስ በእስያ ላሉት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት፤ ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም፥ በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት፥ ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኵር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን። ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን፥
1:6b.REV.001.006መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።
1:7b.REV.001.007እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን።
1:8b.REV.001.008ያለውና የነበረው የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ። አልፋና ዖሜጋ እኔ ነኝ ይላል።
1:9b.REV.001.009እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ።
1:10b.REV.001.010በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥
1:11b.REV.001.011እንዲሁም። የምታየውን በመጽሐፍ ጽፈህ ወደ ኤፌሶንና ወደ ሰምርኔስ ወደ ጴርጋሞንም ወደ ትያጥሮንም ወደ ሰርዴስም ወደ ፊልድልፍያም ወደ ሎዶቅያም በእስያ ወዳሉት ወደ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላክ አለኝ።
1:12b.REV.001.012የሚናገረኝንም ድምፅ ለማየት ዘወር አልሁ፤ ዘወርም ብዬ ሰባት የወርቅ መቅረዞች አየሁ፥
1:13b.REV.001.013በመቅረዞቹም መካከል የሰው ልጅ የሚመስለውን አየሁ፥ እርሱም እስከ እግሩ ድረስ ልብስ የለበሰው ደረቱንም በወርቅ መታጠቂያ የታጠቀ ነበር።
1:14b.REV.001.014ራሱና የራሱ ጠጕርም እንደ ነጭ የበግ ጠጕር እንደ በረዶም ነጭ ነበሩ፥ ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ነበሩ፤
1:15b.REV.001.015እግሮቹም በእቶን የነጠረ የጋለ ናስ ይመስሉ ነበር፥ ድምፁም እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅ ነበረ።
1:16b.REV.001.016በቀኝ እጁም ሰባት ከዋክብት ነበሩት፥ ከአፉም በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ወጣ፤ ፊቱም በኃይል እንደሚበራ እንደ ፀሐይ ነበረ።
1:17b.REV.001.017ባየሁትም ጊዜ እንደ ሞተ ሰው ሆኜ ከእግሩ በታች ወደቅሁ። ቀኝ እጁንም ጫነብኝ እንዲህም አለኝ። አትፍራ፤ ፊተኛውና መጨረሻው ሕያውም እኔ ነኝ፥
1:18b.REV.001.018ሞቼም ነበርሁ እነሆም፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፥ የሞትና የሲኦልም መክፈቻ አለኝ።
1:19b.REV.001.019እንግዲህ ያየኸውን አሁንም ያለውን ከዚህም በኋላ ይሆን ዘንድ ያለውን ጻፍ።
1:20b.REV.001.020በቀኝ እጄ ያየሃቸው የሰባቱ ከዋክብትና የሰባቱ የወርቅ መቅረዞች ምሥጢር ይህ ነው፤ ሰባቱ ከዋክብት የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መላእክት ናቸው፥ ሰባቱም መቅረዞች ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።
2
2:1b.REV.002.001በኤፌሶን ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። በቀኝ እጁ ሰባቱን ከዋክብት የያዘው በሰባቱም የወርቅ መቅረዞች መካከል የሚሄደው እንዲህ ይላል።
2:2b.REV.002.002ሥራህንና ድካምህን ትዕግሥትህንም አውቃለሁ፤ ክፉዎችንም ልትታገሥ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይሆኑ። ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ሆነው እንዳገኘሃቸው አውቃለሁ፤
2:3b.REV.002.003ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም ብለህ ጸንተህ አልደከምህም።
2:4b.REV.002.004ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና።
2:5b.REV.002.005እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ።
2:6b.REV.002.006ነገር ግን ይህ አለህ፤ እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና።
2:7b.REV.002.007መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ።
2:8b.REV.002.008በሰምርኔስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሞቶ የነበረው ሕያውም የሆነው ፊተኛውና መጨረሻው እንዲህ ይላል።
2:9b.REV.002.009መከራህንና ድህነትህን አውቃለሁ፥ ነገር ግን ባለ ጠጋ ነህ፤ የሰይጣንም ማኅበር ናቸው እንጂ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን የሚሉት የሚሳደቡትን ስድብ አውቃለሁ።
2:10b.REV.002.010ልትቀበለው ያለህን መከራ አትፍራ። እነሆ፥ እንድትፈተኑ ዲያብሎስ ከእናንተ አንዳንዶቻችሁን በወኅኒ ሊያገባችሁ አለው፥ አሥር ቀንም መከራን ትቀበላላችሁ። እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ።
2:11b.REV.002.011መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል የነሣው በሁለተኛው ሞት አይጐዳም።
2:12b.REV.002.012በጴርጋሞንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። በሁለት ወገን የተሳለ ስለታም ሰይፍ ያለው እንዲህ ይላል።
2:13b.REV.002.013የሰይጣን ዙፋን ባለበት የምትኖርበትን አውቃለሁ፤ ስሜንም ትጠብቃለህ፥ ሰይጣንም በሚኖርበት፥ በእናንተ ዘንድ የተገደለው የታመነው ምስክሬ አንቲጳስ በነበረበት ዘመን እንኳ ሃይማኖቴን አልካድህም።
2:14b.REV.002.014ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።
2:15b.REV.002.015እንዲሁ የኒቆላውያንን ትምህርት እንደ እነዚህ የሚጠብቁ ሰዎች ከአንተ ጋር ደግሞ አሉ።
2:16b.REV.002.016እንግዲህ ንስሐ ግባ፤ አለዚያ ፈጥኜ እመጣብሃለሁ፥ በአፌም ሰይፍ እዋጋቸዋለሁ።
2:17b.REV.002.017መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ። ድል ለነሣው ከተሰወረ መና እሰጠዋለሁ፥ ነጭ ድንጋይንም እሰጠዋለሁ፥ በድንጋዩም ላይ ከተቀበለው በቀር አንድ ስንኳ የሚያውቀው የሌለ አዲስ ስም ተጽፎአል።
2:18b.REV.002.018በትያጥሮንም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። እንደ እሳት ነበልባል የሆኑ ዓይኖች ያሉት በእቶንም የነጠረ የጋለ ናስ የሚመስሉ እግሮች ያሉት የእግዚአብሔር ልጅ እንዲህ ይላል።
2:19b.REV.002.019ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።
2:20b.REV.002.020ዳሩ ግን። ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤
2:21b.REV.002.021ንስሐም እንድትገባ ጊዜ ሰጠኋት ከዝሙትዋም ንስሐ እንድትገባ አልወደደችም።
2:22b.REV.002.022እነሆ፥ በአልጋ ላይ እጥላታለሁ፥ ከእርስዋም ጋር የሚያመነዝሩትን ከሥራዋ ንስሐ ባይገቡ በታላቅ መከራ እጥላቸዋለሁ፤
2:23b.REV.002.023ልጆችዋንም በሞት እገድላቸዋለሁ፤ አብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ ኵላሊትንና ልብን የምመረምር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ለእያንዳንዳችሁም እንደ ሥራችሁ እሰጣችኋለሁ።
2:24b.REV.002.024ዳሩ ግን ይህን ትምህርት ለማትይዙ ሁሉ የሰይጣንንም ጥልቅ ነገር እነርሱ እንደሚሉት ለማታውቁ ለእናንተ በትያጥሮን ለቀራችሁት እላለሁ፤ ሌላ ሸክም አልጭንባችሁም፥
2:25b.REV.002.025ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ።
2:26b.REV.002.026ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻም ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልሁ በአሕዛብ ላይ ሥልጣንን እሰጠዋለሁ፥ በብረትም በትር ይገዛቸዋል፥ እንደ ሸክላ ዕቃም ይቀጠቀጣሉ፤
2:28b.REV.002.028የንጋትንም ኮከብ እሰጠዋለሁ።
2:29b.REV.002.029መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
3
3:1b.REV.003.001በሰርዴስም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል። ሥራህን አውቃለሁ ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል።
3:2b.REV.003.002ሥራህን በአምላኬ ፊት ፍጹም ሆኖ አላገኘሁትምና የነቃህ ሁን፥ ሊሞቱም ያላቸውን የቀሩትን ነገሮች አጽና።
3:3b.REV.003.003እንግዲህ እንዴት እንደ ተቀበልህና እንደ ሰማህ አስብ፥ ጠብቀውም ንስሐም ግባ። እንግዲያስ ባትነቃ እንደ ሌባ እመጣብሃለሁ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።
3:4b.REV.003.004ነገር ግን ልብሳቸውን ያላረከሱ በሰርዴስ ጥቂት ሰዎች ከአንተ ጋር አሉ፥ የተገባቸውም ስለ ሆኑ ነጭ ልብስ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።
3:5b.REV.003.005ድል የነሣው እንዲሁ በነጭ ልብስ ይጐናጸፋል፥ ስሙንም ከሕይወት መጽሐፍ አልደመስስም፥ በአባቴና በመላእክቱም ፊት ለስሙ እመሰክርለታለሁ።
3:6b.REV.003.006መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
3:7b.REV.003.007በፊልድልፍያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት፥ የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ፥ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነው እርሱ እንዲህ ይላል።
3:8b.REV.003.008ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፥ በአንተ ፊት የተከፈተ በር ሰጥቼአለሁ ማንምም ሊዘጋው አይችልም፤ ኃይልህ ምንም ትንሽ ቢሆን ቃሌን ጠብቀሃልና፥ ስሜንም አልካድህምና።
3:9b.REV.003.009እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደ ወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።
3:10b.REV.003.010የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።
3:11b.REV.003.011እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ።
3:12b.REV.003.012ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።
3:13b.REV.003.013መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
3:14b.REV.003.014በሎዶቅያም ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ። አሜን የሆነው፥ የታመነውና እውነተኛው ምስክር፥ በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው እንዲህ ይላል።
3:15b.REV.003.015በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር።
3:16b.REV.003.016እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።
3:17b.REV.003.017ሀብታም ነኝና ባለጠጋ ሆኜአለሁ አንድም ስንኳ አያስፈልገኝም የምትል ስለ ሆንህ፥ ጐስቋላና ምስኪንም ድሀም ዕውርም የተራቆትህም መሆንህን ስለማታውቅ፥
3:18b.REV.003.018ባለ ጠጋ እንድትሆን በእሳት የነጠረውን ወርቅ፥ ተጐናጽፈህም የራቁትነትህ ኃፍረት እንዳይገለጥ ነጭ ልብስን፥ እንድታይም ዓይኖችህን የምትኳለውን ኵል ከእኔ ትገዛ ዘንድ እመክርሃለሁ።
3:19b.REV.003.019እኔ የምወዳቸውን ሁሉ እገሥጻቸዋለሁ እቀጣቸውማለሁ፤ እንግዲህ ቅና ንስሐም ግባ።
3:20b.REV.003.020እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።
3:21b.REV.003.021እኔ ደግሞ ድል እንደ ነሣሁ ከአባቴም ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥሁ፥ ድል ለነሣው ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ ይቀመጥ ዘንድ እሰጠዋለሁ።
3:22b.REV.003.022መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ።
4
4:1b.REV.004.001ከዚያ በኋላም አየሁ፥ እነሆም በሰማይ የተከፈተ ደጅ፥ እንደ መለከትም ሆኖ ሲናገረኝ የሰማሁት ፊተኛው ድምፅ። ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ አለ።
4:2b.REV.004.002ወዲያው በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፥ ዙፋን በሰማይ ቆሞአል በዙፋኑም ላይ ተቀማጭ ነበረ፤
4:3b.REV.004.003ተቀምጦም የነበረው በመልኩ የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቍ ይመስል ነበር። በመልኩም መረግድን የመሰለ ቀስተ ደመና በዙፋኑ ዙሪያ ነበረ።
4:4b.REV.004.004በዙፋኑ ዙሪያም ሀያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፥ በዙፋኖቹም ላይ ነጭ ልብስ ለብሰው በራሳቸውም የወርቅ አክሊል ደፍተው ሀያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።
4:5b.REV.004.005ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ ነጐድጓድም ይወጣል፤ በዙፋኑም ፊት ሰባት የእሳት መብራቶች ይበሩ ነበር፥ እነርሱም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።
4:6b.REV.004.006በዙፋኑም ፊት ብርሌ የሚመስል የብርጭቆ ባሕር ነበረ። በዙፋኑም መካከል በዙፋኑም ዙሪያ፥ በፊትና በኋላ ዓይኖች የሞሉአቸው አራት እንስሶች ነበሩ።
4:7b.REV.004.007ፊተኛውም እንስሳ አንበሳን ይመስላል፥ ሁለተኛውም እንስሳ ጥጃን ይመስላል፥ ሦስተኛውም እንስሳ እንደ ሰው ፊት ነበረው፥ አራተኛውም እንስሳ የሚበረውን ንስር ይመስላል።
4:8b.REV.004.008አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም።
4:9b.REV.004.009እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥
4:10b.REV.004.010ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።
5
5:1b.REV.005.001በዙፋኑ ላይም በተቀመጠው በቀኝ እጁ ላይ በውስጥና በኋላ የተጻፈበት በሰባትም ማኅተም የተዘጋ መጽሐፍን አየሁ።
5:2b.REV.005.002ብርቱም መልአክ። መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ማኅተሞቹንም ይፈታ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲያውጅ አየሁ።
5:3b.REV.005.003በሰማይም ቢሆን በምድርም ላይ ቢሆን ከምድርም በታች ቢሆን መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው ማንም አልተቻለውም።
5:4b.REV.005.004መጽሐፉን ሊዘረጋ ወይም ሊመለከተው የሚገባው ማንም ስላልተገኘ እጅግ አለቀስሁ።
5:5b.REV.005.005ከሽማግሌዎቹም አንዱ። አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ ሰባቱንም ማኅተም ይፈታ ዘንድ ድል ነሥቶአል አለኝ።
5:6b.REV.005.006በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ፥ ሰባትም ቀንዶችና ሰባት ዓይኖች ነበሩት እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ የተላኩ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።
5:7b.REV.005.007መጥቶም በዙፋን ላይ ከተቀመጠ ከዚያ ከቀኝ እጁ መጽሐፉን ወሰደው።
5:8b.REV.005.008መጽሐፉንም በወሰደ ጊዜ አራቱ እንስሶችና ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በበጉ ፊት ወደቁ፥ እያንዳንዳቸውም በገናንና የቅዱሳን ጸሎት የሆነ ዕጣን የሞላበትን የወርቅ ዕቃ ያዙ።
5:9b.REV.005.009መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።
5:11b.REV.005.011አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥
5:12b.REV.005.012በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።
5:13b.REV.005.013በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ።
5:14b.REV.005.014አራቱም እንስሶች። አሜን አሉ፥ ሽማግሌዎቹም ወድቀው ሰገዱ።
6
6:1b.REV.006.001በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
6:2b.REV.006.002አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት።
6:3b.REV.006.003ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
6:4b.REV.006.004ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው።
6:5b.REV.006.005ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ።
6:6b.REV.006.006በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ። አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ።
6:7b.REV.006.007አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ። መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ።
6:8b.REV.006.008አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
6:9b.REV.006.009አምስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ፥ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ጠበቁት ምስክር የታረዱትን የሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያ በታች አየሁ።
6:10b.REV.006.010በታላቅ ድምፅም እየጮኹ። ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፥ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድም ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከ መቼ አትበቀልም? አሉ።
6:11b.REV.006.011ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፥ እንደ እነርሱም ደግሞ ይገደሉ ዘንድ ያላቸው የባሪያዎች ባልንጀራዎቻቸውና የወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪፈጸም ድረስ፥ ገና ጥቂት ዘመን እንዲያርፉ ተባለላቸው።
6:12b.REV.006.012ስድስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ፥ ፀሐይም እንደ ማቅ ጠጕር ጥቁር ሆነ፥ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ፥
6:13b.REV.006.013በለስም በብርቱ ነፋስ ተናውጣ ቃርያዋን ፍሬ እንደምትጥል የሰማይ ከዋክብት ወደ ምድር ወደቁ፥
6:14b.REV.006.014ሰማይም እንደ መጽሐፍ ተጠቅልሎ አለፈ፥ ተራራዎችና ደሴቶችም ሁሉ ከስፍራቸው ተወሰዱ።
6:15b.REV.006.015የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ፥
6:16b.REV.006.016ተራራዎችንና ዓለቶችንም። በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን፤
6:17b.REV.006.017ታላቁ የቁጣው ቀን መጥቶአልና፥ ማንስ ሊቆም ይችላል? አሉአቸው።
7
7:1b.REV.007.001ከዚህም በኋላ በአራቱ በምድር ማዕዘን ቆመው አራት መላእክት አየሁ፥ እነርሱም ነፋስ በምድር ቢሆን ወይም በባሕር ወይም በማንም ዛፍ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት ያዙ።
7:2b.REV.007.002የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ።
7:3b.REV.007.003የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው።
7:4b.REV.007.004የታተሙትንም ቍጥር ሰማሁ፤ ከእስራኤል ልጆች ነገድ ሁሉ የታተሙት መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
7:5b.REV.007.005ከይሁዳ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ፥ ከሮቤል ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከጋድ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥
7:6b.REV.007.006ከአሴር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከንፍታሌም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥
7:7b.REV.007.007ከምናሴ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከስምዖን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከሌዊ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከይሳኮር ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥
7:8b.REV.007.008ከዛብሎን ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከዮሴፍ ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ፥ ከብንያም ነገድ አሥራ ሁለት ሺህ ታተሙ።
7:9b.REV.007.009ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤
7:10b.REV.007.010በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።
7:11b.REV.007.011መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ።
7:12b.REV.007.012አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ።
7:13b.REV.007.013ከሽማግሌዎቹም አንዱ ተመልሶ። እነዚህ ነጩን ልብስ የለበሱ እነማን ናቸው? ከወዴትስ መጡ? አለኝ።
7:14b.REV.007.014እኔም። ጌታ ሆይ፥ አንተ ታውቃለህ አልሁት። አለኝም። እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፥ ልብሳቸውንም አጥበው በበጉ ደም አነጹ።
7:15b.REV.007.015ስለዚህ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት አሉ፥ ሌሊትና ቀንም በመቅደሱ ያመልኩታል፥ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው በእነርሱ ላይ ያድርባቸዋል።
7:16b.REV.007.016ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም፥ ከእንግዲህም ወዲህ አይጠሙም፥ ፀሐይም ትኵሳትም ሁሉ ከቶ አይወርድባቸውም፤
7:17b.REV.007.017በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥ ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋልና፤ እግዚአብሔርም እንባዎችን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።
8
8:1b.REV.008.001ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ።
8:2b.REV.008.002በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው።
8:3b.REV.008.003ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው።
8:4b.REV.008.004የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
8:5b.REV.008.005መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ።
8:6b.REV.008.006ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ።
8:7b.REV.008.007ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ።
8:8b.REV.008.008ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ
8:9b.REV.008.009በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ።
8:10b.REV.008.010ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል።
8:11b.REV.008.011የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ።
8:12b.REV.008.012አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት።
8:13b.REV.008.013አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ። ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።
9
9:1b.REV.009.001አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው።
9:2b.REV.009.002የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ።
9:3b.REV.009.003ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው።
9:4b.REV.009.004የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው።
9:5b.REV.009.005አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው።
9:6b.REV.009.006በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል።
9:7b.REV.009.007የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፥ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤
9:8b.REV.009.008የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥
9:9b.REV.009.009የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፥ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ።
9:10b.REV.009.010እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው።
9:11b.REV.009.011በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል።
9:12b.REV.009.012ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል።
9:13b.REV.009.013ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥
9:14b.REV.009.014መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ። በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው።
9:15b.REV.009.015የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ።
9:16b.REV.009.016የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ።
9:17b.REV.009.017ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ።
9:18b.REV.009.018ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ።
9:19b.REV.009.019የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ።
9:20b.REV.009.020በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤
9:21b.REV.009.021ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።
10
10:1b.REV.010.001ሌላም ብርቱ መልአክ ደመና ተጐናጽፎ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበረ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ እግሮቹም እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፥
10:2b.REV.010.002የተከፈተችንም ታናሽ መጽሐፍ በእጁ ያዘ። ቀኝ እግሩንም በባሕር ላይ ግራውንም በምድር ላይ አኖረ፥ እንደሚያገሣም አንበሳ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
10:3b.REV.010.003በጮኸም ጊዜ ሰባቱ ነጐድጓድ በየድምፃቸው ተናገሩ።
10:4b.REV.010.004ሰባቱ ነጐድጓድ በተናገሩ ጊዜ ልጽፍ አሰብሁ፤ ከሰማይም። ሰባቱ ነጐድጓድ የተናገሩትን ነገር በማኅተም ዝጋው አትጻፈውም የሚል ድምፅ ሰማሁ።
10:5b.REV.010.005በባሕርና በምድርም ላይ ሲቆም ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አሻቅቦ ዘረጋ፥
10:6b.REV.010.006ሰማይንና በእርሱም ያሉትን፥ ምድርንና በእርስዋም ያሉትን፥ ባሕርንና በእርሱም ያሉትን በፈጠረው፥ ከዘላለምም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ሆኖ በሚኖረው ምሎ።
10:7b.REV.010.007ወደ ፊት አይዘገይም፥ ዳሩ ግን ሰባተኛው መልአክ ሊነፋ ባለው ጊዜ ድምፁም በሚሰማበት ዘመን፥ ለባሪያዎቹ ለነቢያት የምስራች እንደ ሰበከላቸው የእግዚአብሔር ምሥጢር ይፈጸማል አለ።
10:8b.REV.010.008ከሰማይም የሰማሁት ድምፅ እንደ ገና ሲናገረኝና። ሂድና በባሕርና በምድር ላይ ከሚቆመው መልአክ በእጁ ያለችውን የተከፈተችውን መጽሐፍ ውሰድ ሲል ሰማሁ።
10:9b.REV.010.009ወደ መልአኩም ሄጄ። ታናሺቱን መጽሐፍ ስጠኝ አልሁት። እርሱም። ውሰድና ብላት፥ ሆድህንም መራራ ታደርገዋለች በአፍህ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች አለኝ።
10:10b.REV.010.010ከመልአኩም እጅ ታናሺቱን መጽሐፍ ወስጄ በላኋት በአፌም እንደ ማር ጣፋጭ ሆነች፤ ከበላኋት በኋላም ሆዴ መራራ ሆነ።
10:11b.REV.010.011በብዙ ወገኖችና በአሕዛብም በቋንቋዎችም በነገሥታትም ላይ እንደ ገና ትንቢት ትናገር ዘንድ ይገባሃል ተባለልኝ።
11
11:1b.REV.011.001በትር የሚመስል መለኪያ ለእኔ ተሰጠኝ፥ እንዲህም ተባለልኝ። ተነሥተህ የእግዚአብሔርን መቅደስና መሠዊያውን በዚያም የሚሰግዱትን ለካ።
11:2b.REV.011.002በመቅደሱም ውጭ ያለው እድሞ ለአሕዛብ ተሰጥቶአልና ተወው አትለካውም፤ እነርሱም አርባ ሁለት ወር የተቀደሰችውን ከተማ ይረግጡአታል።
11:3b.REV.011.003ለሁለቱም ምስክሮቼ ማቅ ለብሰው ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት ሊናገሩ እሰጣለሁ።
11:4b.REV.011.004እነዚህ በምድር ጌታ ፊት የሚቆሙ ሁለቱ ወይራዎችና ሁለቱ መቅረዞች ናቸው።
11:5b.REV.011.005ማንምም ሊጐዳቸው ቢወድ እሳት ከአፋቸው ይወጣል ጠላቶቻቸውንም ይበላል፤ ማንም ሊጐዳቸው ቢወድም እንዲሁ ሊገደል ይገባዋል።
11:6b.REV.011.006እነዚህ ትንቢት በሚናገሩበት ወራት ዝናብ እንዳይዘንብ ሰማይን ሊዘጉ ሥልጣን አላቸው፥ ውኃዎችንም ወደ ደም ሊለውጡ በሚፈልጉበትም ጊዜ ሁሉ በመቅሠፍት ሁሉ ምድርን ሊመቱ ሥልጣን አላቸው።
11:7b.REV.011.007ምስክራቸውን ከፈጸሙ በኋላ ከጥልቁ የሚወጣው አውሬ ይዋጋቸዋል ያሸንፋቸውማል ይገድላቸውማል።
11:8b.REV.011.008በድናቸውም በታላቂቱ ከተማ አደባባይ ይተኛል እርስዋም በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ የተባለች ደግሞ ጌታቸው የተሰቀለባት ናት።
11:9b.REV.011.009ከወገኖችና ከነገዶችም ከቋንቋዎችም ከአሕዛብም የሆኑ ሰዎች ሦስት ቀን ተኵል በድናቸውን ይመለከታሉ፥ በድናቸውም ወደ መቃብር ሊገባ አይፈቅዱም።
11:10b.REV.011.010እነዚህም ሁለት ነቢያት በምድር የሚኖሩትን ስለ ሣቀዩ በምድር የሚኖሩት በእነርሱ ላይ ደስ ይላቸዋል በደስታም ይኖራሉ እርስ በርሳቸውም ስጦታ ይሰጣጣሉ።
11:11b.REV.011.011ከሦስቱ ቀን ተኵልም በኋላ ከእግዚአብሔር የወጣ የሕይወት መንፈስ ገባባቸው በእግሮቻቸውም ቆሙ፥ ታላቅም ፍርሃት በሚመለከቱት ላይ ወደቀባቸው።
11:12b.REV.011.012በሰማይም። ወደዚህ ውጡ የሚላቸውን ታላቅ ድምፅ ሰሙ፤ ጠላቶቻቸውም እየተመለከቱአቸው ወደ ሰማይ በደመና ወጡ።
11:13b.REV.011.013በዚያም ሰዓት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፥ ከከተማይቱም አሥረኛው እጅ ወደቀ፥ በመናወጥም ሰባት ሺህ ሰዎች ተገደሉ፥ የቀሩትንም ፍርሃት ያዛቸው፥ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።
11:14b.REV.011.014ሁለተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ሦስተኛው ወዮ በቶሎ ይመጣል።
11:15b.REV.011.015ሰባተኛው መልአክ ነፋ፤ በሰማይም። የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣል
11:16b.REV.011.016የሚሉ ታላላቅ ድምፆች ሆኑ። በእግዚአብሔርም ፊት በዙፋኖቻቸው የተቀመጡ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በግምባራቸው ተደፍተው
11:17b.REV.011.017ለእግዚአብሔር እየሰገዱ እንዲህ አሉ። ያለህና የነበርህ ሁሉን የምትገዛ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ትልቁን ኃይልህን ስለ ያዝህ ስለ ነገሥህም እናመሰግንሃለን፤
11:18b.REV.011.018አሕዛብም ተቈጡ፥ ቍጣህም መጣ፥ በሙታንም ትፈርድ ዘንድ ዘመን መጣ፥ ለባሪያዎችህም ለነቢያትና ለቅዱሳን ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ፥ ምድርንም የሚያጠፉትን ታጠፋ ዘንድ ዘመን መጣ።
11:19b.REV.011.019በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ፥ መብረቅና ድምፅም ነጐድጓድም የምድርም መናወጥ ታላቅም በረዶ ሆነ።
12
12:1b.REV.012.001ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች።
12:2b.REV.012.002እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች።
12:3b.REV.012.003ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥
12:4b.REV.012.004ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ።
12:5b.REV.012.005አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።
12:6b.REV.012.006ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች።
12:7b.REV.012.007በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥
12:8b.REV.012.008ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።
12:9b.REV.012.009ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።
12:10b.REV.012.010ታላቅም ድምፅ በሰማይ ሰማሁ እንዲህ ሲል። አሁን የአምላካችን ማዳንና ኃይል መንግሥትም የክርስቶስም ሥልጣን ሆነ፥ ቀንና ሌሊትም በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሎአልና።
12:11b.REV.012.011እነርሱም ከበጉ ደም የተነሣ ከምስክራቸውም ቃል የተነሣ ድል ነሡት፥ ነፍሳቸውንም እስከ ሞት ድረስ አልወደዱም።
12:12b.REV.012.012ስለዚህ፥ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፥ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፥ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቍጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።
12:13b.REV.012.013ዘንዶውም ወደ ምድር እንደ ተጣለ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ የወለደችውን ሴት አሳደዳት።
12:14b.REV.012.014ከእባቡም ፊት ርቃ አንድ ዘመን፥ ዘመናትም፥ የዘመንም እኵሌታ ወደ ምትመገብበት ወደ ስፍራዋ ወደ በረሀ እንድትበር ለሴቲቱ ሁለት የታላቁ ንሥር ክንፎች ተሰጣት።
12:15b.REV.012.015እባቡም ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያህልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋላዋ አፈሰሰ።
12:16b.REV.012.016ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፥ ምድሪቱም አፍዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው።
12:17b.REV.012.017ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ፤
12:18b.REV.012.018በባሕርም አሸዋ ላይ ቆመ።
13
13:1b.REV.013.001አንድም አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ፤ አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት፥ በቀንዶቹም ላይ አሥር ዘውዶች በራሶቹም ላይ የስድብ ስም ነበረ።
13:2b.REV.013.002ያየሁትም አውሬ ነብር ይመስል ነበር፥ እግሮቹም እንደ ድብ እግሮች፥ አፉም እንደ አንበሳ አፍ ነበሩ። ዘንዶውም ኃይሉንና ዙፋኑን ትልቅም ሥልጣን ሰጠው።
13:3b.REV.013.003ከራሶቹም ለሞት እንደ ታረደ ሆኖ አንዱን አየሁ፥ ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰ። ምድርም ሁሉ አውሬውን እየተከተለ ተደነቀ፥
13:4b.REV.013.004ለዘንዶውም ሰገዱለት፥ ለአውሬው ሥልጣንን ሰጥቶታልና፤ ለአውሬውም። አውሬውን ማን ይመስለዋል፥ እርሱንስ ሊዋጋ ማን ይችላል? እያሉ ሰገዱለት።
13:5b.REV.013.005ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው፥ በአርባ ሁለት ወርም እንዲሠራ ሥልጣን ተሰጠው።
13:6b.REV.013.006እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ።
13:7b.REV.013.007ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።
13:8b.REV.013.008ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።
13:9b.REV.013.009ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።
13:10b.REV.013.010ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።
13:11b.REV.013.011ሌላም አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፥ የበግ ቀንዶችን የሚመስሉ ሁለት ቀንዶችም ነበሩት እንደ ዘንዶም ይናገር ነበር።
13:12b.REV.013.012በፊተኛውም አውሬ ሥልጣን በእርሱ ፊት ሁሉን ያደርጋል። ለሞቱ የሆነውም ቍስል ተፈወሰለት ለፊተኛው አውሬ ምድርና በእርሱ የሚኖሩት እንዲሰግዱለት ያደርጋል።
13:13b.REV.013.013እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር በሰው ፊት እስኪያወርድ ድረስ ታላላቆችን ምልክቶች ያደርጋል።
13:14b.REV.013.014በአውሬውም ፊት ያደርግ ዘንድ ከተሰጡት ምልክቶች የተነሣ በምድር የሚኖሩትን ያስታል፤ የሰይፍም ቍስል ለነበረውና በሕይወት ለኖረው ለአውሬው ምስልን እንዲያደርጉ በምድር የሚኖሩትን ይናገራል።
13:15b.REV.013.015የአውሬው ምስል ሊናገር እንኳ ለአውሬውም ምስል የማይሰግዱለትን ሁሉ ሊያስገድላቸው፥ ለአውሬው ምስል ትንፋሽ እንዲሰጠው ተሰጠው።
13:16b.REV.013.016ታናናሾችና ታላላቆችም ባለ ጠጋዎችና ድሆችም ጌታዎችና ባሪያዎችም ሁሉ በቀኝ እጃቸው ወይም በግምባራቸው ምልክትን እንዲቀበሉ፥
13:17b.REV.013.017የአውሬውም ስም ወይም የስሙ ቍጥር ያለው ምልክት የሌለበት ማንም ሊገዛ ወይም ሊሸጥ እንዳይችል ያደርጋል። ጥበብ በዚህ አለ።
13:18b.REV.013.018አእምሮ ያለው የአውሬውን ቍጥር ይቍጠረው፤ ቍጥሩ የሰው ቍጥር ነውና፥ ቍጥሩም ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ነው።
14
14:1b.REV.014.001አየሁም፥ እነሆም፥ በጉ በጽዮን ተራራ ቆሞ ነበር፥ ከእርሱም ጋር ስሙና የአባቱ ስም በግምባራቸው የተጻፈላቸው መቶ አርባ አራት ሺህ ነበሩ።
14:2b.REV.014.002እንደ ብዙ ውኃም ድምፅና እንደ ታላቅ ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ከሰማይ ድምፅን ሰማሁ፥ ደርዳሪዎችም በገና እንደሚደረድሩ ያለ ድምፅ ሰማሁ።
14:3b.REV.014.003በዙፋኑም ፊት በአራቱም እንስሶችና በሽማግሌዎቹ ፊት አዲስ ቅኔ ዘመሩ፤ ከምድርም ከተዋጁት ከመቶ አርባ አራት ሺህ በቀር ያን ቅኔ ሊማር ለማንም አልተቻለውም።
14:4b.REV.014.004ከሴቶች ጋር ያልረከሱ እነዚህ ናቸው፥ ድንግሎች ናቸውና። በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው። ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች የተዋጁ እነዚህ ናቸው።
14:5b.REV.014.005በአፋቸውም ውሸት አልተገኘም፤ ነውር የለባቸውም።
14:6b.REV.014.006በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤
14:7b.REV.014.007በታላቅ ድምፅም። የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ።
14:8b.REV.014.008ሌላም ሁለተኛ መልአክ። አሕዛብን ሁሉ የዝሙትዋን ቍጣ ወይን ጠጅ ያጠጣች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች እያለ ተከተለው።
14:9b.REV.014.009ሦስተኛም መልአክ ተከተላቸው፥ በታላቅ ድምፅ እንዲህ እያለ። ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥
14:10b.REV.014.010እርሱ ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል።
14:11b.REV.014.011የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።
14:12b.REV.014.012የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው።
14:13b.REV.014.013ከሰማይም። ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው። መንፈስ። አዎን፥ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፥ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምፅ ሰማሁ።
14:14b.REV.014.014አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው።
14:15b.REV.014.015ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው። የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
14:16b.REV.014.016በደመናውም ላይ የተቀመጠው ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው ምድርም ታጨደች።
14:17b.REV.014.017ሌላ መልአክም በሰማይ ካለው መቅደስ ወጣ፥ እርሱም ደግሞ ስለታም ማጭድ ነበረው።
14:18b.REV.014.018በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጥቶ ስለታም ማጭድ ያለውን። ዘለላዎቹ ፈጽመው በስለዋልና ስለታሙን ማጭድህን ስደድና በምድር ያለውን የወይን ዛፍ ዘለላዎች ቍረጥ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጠራ።
14:19b.REV.014.019መልአኩም ማጭዱን ወደ ምድር ጣለው፥ በምድርም ካለው ከወይን ዛፍ ቈርጦ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር ቍጣ መጥመቂያ ጣለ።
14:20b.REV.014.020የወይኑም መጥመቂያ ከከተማ ውጭ ተረገጠ፥ እስከ ፈረሶች ልጓምም የሚደርስ ደም ርቀቱ ሺህ ስድስት መቶ ምዕራፍ ሆኖ ከመጥመቂያው ወጣ።
15
15:1b.REV.015.001ሌላም ታላቅና ድንቅ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በእነርሱ ስለሚፈጸም ኋለኛዎቹን ሰባት መቅሠፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት ታዩ።
15:2b.REV.015.002በእሳትም የተቀላቀለውን የብርጭቆ ባሕር የሚመስለውን አየሁ፥ በአውሬውና በምስሉም በስሙም ቍጥር ላይ ድል ነሥተው የነበሩት የእግዚአብሔርን በገና ይዘው በብርጭቆ ባሕር ላይ ሲቆሙ አየሁ።
15:3b.REV.015.003ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፥ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፥ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ እያሉ የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ።
15:5b.REV.015.005ከዚህም በኋላ አየሁ፥ የምስክርም ድንኳን መቅደስ በሰማይ ተከፈተ፥
15:6b.REV.015.006ሰባቱንም መቅሠፍት የያዙ ሰባቱ መላእክት ከመቅደሱ ወጡ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ ጥሩ የጌጥ ልብስ ለበሱ ደረታቸውንም በወርቅ መታጠቂያ ታጠቁ።
15:7b.REV.015.007ከአራቱም እንስሶች አንዱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ የሚኖር የእግዚአሔር ቍጣ የሞላባቸውን ሰባት የወርቅ ጽዋዎች ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።
15:8b.REV.015.008ከእግዚአብሔርም ክብርና ከኃይሉ ጢስ በመቅደሱ ሞላበት፥ የሰባቱ መላእክት ሰባቱ መቅሰፍት እስኪፈጸሙ ድረስ አንድ እንኳ ወደ መቅደሱ ይገባ ዘንድ አልቻለም።
16
16:1b.REV.016.001ለሰባቱም መላእክት። ሄዳችሁ የእግዚአብሔርን ቁጣ ጽዋዎች በምድር ውስጥ አፍስሱ የሚል ታላቅ ድምፅ ከመቅደሱ ሰማሁ።
16:2b.REV.016.002ፊተኛውም ሄዶ ጽዋውን በምድር ውስጥ አፈሰሰ፤ የአውሬውም ምልክት ባለባቸው ለምስሉም በሚሰግዱ ሰዎች ክፉኛ የሚነዘንዝ ቍስል ሆነባቸው።
16:3b.REV.016.003ሁለተኛውም ጽዋውን በባሕር ውስጥ አፈሰሰ፤ እንደ ሞተም ሰው ደም ሆነ፥ በባሕርም ከሚኖሩት ሕይወት ያለበት ነፍስ ሁሉ ሞተ።
16:4b.REV.016.004ሦስተኛውም ጽዋውን በወንዞችና በውኃ ምንጮች ውስጥ አፈሰሰ፤ እነርሱም ደም ሆኑ።
16:5b.REV.016.005የውኃውም መልአክ። ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፥ ቅዱስ ሆይ፥ እንዲህ ስለፈረድህ ጻድቅ ነህ፤
16:6b.REV.016.006የቅዱሳንና የነቢያትን ደም ስላፈሰሱ ደምን ደግሞ አጠጥተሃቸዋል፥ የሚገባቸው ነውና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
16:7b.REV.016.007ከመሰዊያውም። አዎን፥ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፥ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
16:8b.REV.016.008አራተኛውም ጽዋውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰ፤ ሰዎችንም በእሳት ልታቃጥል ተሰጣት።
16:9b.REV.016.009ሰዎችም በታላቅ ትኵሳት ተቃጠሉ፥ በነዚህም መቅሠፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን የእግዚአብሔርን ስም ተሳደቡ፥ ክብርንም እንዲሰጡት ንስሐ አልገቡም።
16:10b.REV.016.010አምስተኛውም ጽዋውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰ፤ መንግሥቱም ጨለማ ሆነች ከስቃይም የተነሳ መላሶቻቸውን ያኝኩ ነበር፥
16:11b.REV.016.011ከስቃያቸውና ከቍስላቸውም የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፥ ከስራቸውም ንስሐ አልገቡም።
16:12b.REV.016.012ስድስተኛውም ጽዋውን በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ ላይ አፈሰሰ፤ ከፀሐይም መውጫ ለሚመጡ ነገሥታት መንገድ እንዲሰናዳላቸው ውኃው ደረቀ።
16:13b.REV.016.013ከዘንዶውም አፍና ከአውሬው አፍ ከሐሰተኛውም ነቢይ አፍ ጓጕንቸሮች የሚመስሉ ሦስት ርኵሳን መናፍስት ሲወጡ አየሁ፤
16:14b.REV.016.014ምልክት እያደረጉ የአጋንንት መናፍስት ናቸውና፥ በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን ወደ ሚሆነው ጦር እንዲያስከትቱአቸው ወደ ዓለም ሁሉ ነገሥታት ይወጣሉ።
16:15b.REV.016.015እነሆ፥ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።
16:16b.REV.016.016በዕብራይስጥም አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ እስከተቱአቸው።
16:17b.REV.016.017ሰባተኛውም ጽዋውን በአየር ውስጥ አፈሰሰ፤ ከመቅደሱም ውስጥ። ተፈጽሞአል የሚል ታላቅ ድምጽ ከዙፋኑ ወጣ።
16:18b.REV.016.018መብረቅና ድምጽም ነጎድጓድም ሆኑ፥ ትልቅም የምድር መናወጥ ሆነ፤ ሰው በምድር ከተፈጠረ ጀምሮ እንዲህ ያለ ታላቅ መናውጥ ከቶ አልነበረም፤ ከሁሉ በለጠ።
16:19b.REV.016.019ታላቂቱም ከተማ በሦስት ተከፋፈለች፥ የአሕዛብም ከተማዎች ወደቁ። ታላቂቱም ባቢሎን የብርቱ ቍጣው ወይን ጠጅ የሞላበትን ጽዋ እንዲሰጣት በእግዚአብሔር ፊት ታሰበች።
16:20b.REV.016.020ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ ተራራዎችም አልተገኙም።
16:21b.REV.016.021በሚዛንም አንድ ታላንት*ፍ1* የሚያህል ታላቅ በረዶ በሰዎች ላይ ከሰማይ ወረደባቸው፤ ሰዎቹም ከበረዶው መቅሰፍት የተነሳ እግዚአብሔርን ተሳደቡ፥ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ነውና። ፍ1 አንድ ታላንት ሦስት ፈረሱላ የሚያህል ነው።
17
17:1b.REV.017.001ሰባቱንም ጽዋዎች ከያዙ ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ና በብዙም ውኃዎች ላይ የተቀመጠችውን የታላቂቱን ጋለሞታ ፍርድ አሳይሃለሁ፤
17:2b.REV.017.002የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ ብሎ ተናገረኝ።
17:3b.REV.017.003በመንፈስም ወደ በረሀ ወሰደኝ፤ የስድብም ስሞች በሞሉበት፥ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ባሉበት በቀይ አውሬ ላይ አንዲት ሴት ተቀምጣ አየሁ።
17:4b.REV.017.004ሴቲቱም በቀይና በሐምራዊ ልብስ ተጐናጽፋ በወርቅና በከበሩ ድንጋዮች በዕንቈችም ተሸልማ ነበር፥ በእጅዋም የሚያስጸይፍ ነገር የዝሙትዋም ርኵሰት የሞላባትን የወርቅ ጽዋ ያዘች፤
17:5b.REV.017.005በግምባርዋም ምስጢር የሆነ ስም። ታላቂቱ ባቢሎን፥ የጋለሞታዎችና የምድር ርኵሰት እናት ተብሎ ተጻፈ።
17:6b.REV.017.006ሴቲቱም በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት። ባየኋትም ጊዜ እጅግ ታላቅ ድንቅ አደነቅሁ።
17:7b.REV.017.007መልአኩም አለኝ። የምትደነቅ ስለ ምንድር ነው? የሴቲቱን ምስጢርና የሚሸከማትን፥ ሰባት ራሶችና አስር ቀንዶች ያሉትን የአውሬውን ምስጢር እኔ እነግርሃለሁ።
17:8b.REV.017.008ያየኸው አውሬ አስቀድሞ ነበረ፥ አሁንም የለም፥ ከጥልቁም ይወጣ ዘንድ አለው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል፤ ስሞቻቸውም ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ በሕይወት መጽሐፍ ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ አውሬው አስቀድሞ እንደነበረ አሁንም እንደሌለ፥ ነገር ግን እንዳለ ሲያዩ ያደንቃሉ።
17:9b.REV.017.009ጥበብ ያለው አእምሮ በዚህ ነው። ሰባቱ ራሶች ሴቲቱ የተቀመጠችባቸው ሰባት ተራራዎች ናቸው፥
17:10b.REV.017.010ሰባት ነገሥታት ደግሞ ናቸው፤ አምስቱ ወድቀዋል አንዱም አለ፥ የቀረውም ገና አልመጣም፤ ሲመጣም፥ ጥቂት ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።
17:11b.REV.017.011የነበረውና የሌለውም አውሬ ራሱ ደግሞ ስምንተኛው ነው ከሰባቱም አንዱ ነው፥ ወደ ጥፋትም ይሄዳል።
17:12b.REV.017.012ያየሃቸውም አስሩ ቀንዶች ገና መንግሥትን ያልተቀበሉ አስር ነገሥታት ናቸው፥ ዳሩ ግን ከአውሬው ጋር ለአንድ ሰዓት እንደ ነገሥታት ሥልጣንን ይቀበላሉ።
17:13b.REV.017.013እነዚህ አንድ አሳብ አላቸው፥ ኃይላቸውንና ሥልጣናቸውንም ለአውሬው ይሰጣሉ።
17:14b.REV.017.014እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ።
17:15b.REV.017.015አለኝም። ጋለሞታይቱ የተቀመጠችባቸው ያየሃቸው ውኃዎች፥ ወገኖችና ብዙ ሰዎች አሕዛብም ቋንቋዎችም ናቸው።
17:16b.REV.017.016ያየኃቸውም አስር ቀንዶችና አውሬው ጋለሞታይቱን ይጣላሉ፤ ባዶዋንና ራቁትዋንም ያደርጓታል፥ ሥጋዋንም ይበላሉ፥ በእሳትም ያቃጥሉአታል።
17:17b.REV.017.017እግዚአብሔር አሳቡን እንዲያደርጉ አንድንም አሳብ እንዲያደርጉ የእግዚአብሔርም ቃል እስኪፈጸም ድረስ መንግሥታቸውን ለአውሬው እንዲሰጡ በልባቸው አግብቶአልና።
17:18b.REV.017.018ያየሃትም ሴት በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ ናት።
18
18:1b.REV.018.001ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፥ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች።
18:2b.REV.018.002በብርቱም ድምፅ። ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፥ ወደቀች፥ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፥ የርኵሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኵሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤
18:3b.REV.018.003አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቍጣ ወይን ጠጅ የተነሳ ወድቀዋልና፥ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሳ ባለ ጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ።
18:4b.REV.018.004ከሰማይም ሌላ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል። ሕዝቤ ሆይ፥ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤
18:5b.REV.018.005ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፥ እግዚአብሔርም ዓመፃዋን አሰበ።
18:6b.REV.018.006እርስዋ እንደ ሰጠች መጠን ብድራት መልሱላት፥ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤
18:7b.REV.018.007ራስዋን እንደ አከበረችና እንደ ተቀማጠለች ልክ ሥቃይና ኀዘን ስጡአት። በልብዋ። ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ ባልቴትም አልሆንም ኀዘንም ከቶ አላይም ስላለች፥
18:8b.REV.018.008ስለዚህ በአንድ ቀን ሞትና ኀዘን ራብም የሆኑ መቅሰፍቶችዋ ይመጣሉ፥ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።
18:9b.REV.018.009ከእርስዋም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርስዋ ዋይ ዋይ እያሉ ያለቅሳሉ፤
18:10b.REV.018.010ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው። አንቺ ታላቂቱ ከተማ፥ ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን፥ ወዮልሽ፥ ወዮልሽ፥ በአንድ ሰዓት ፍርድሽ ደርሶአልና እያሉ ይናገራሉ።
18:11b.REV.018.011የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል ያዝኑላትማል፤
18:12b.REV.018.012ጭነትም ወርቅና ብር የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር ቀይም ሐርም ሐምራዊም ልብስ የሚሸትም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት ከናስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሰራ ዕቃ ሁሉ፥
18:13b.REV.018.013ቀረፋም ቅመምም የሚቃጠልም ሽቱ ቅባትም ዕጣንም የወይን ጠጅም ዘይትም የተሰለቀ ዱቄትም ስንዴም ከብትም በግም ፈረስም ሰረገላም ባሪያዎችም የሰዎችም ነፍሳት ነው።
18:14b.REV.018.014ነፍስሽም የጎመጀችው ፍሬ ከአንቺ ዘንድ አልፎአል፥ የሚቀማጠልና የሚያጌጥም ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፥ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አያገኙአቸውም።
18:15b.REV.018.015እነዚህን የነገዱ በእርስዋም ባለ ጠጋዎች የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ። በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ ይህን የሚያህል ታላቅ ባለ ጠግነት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና እያሉ ስቃይዋን ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ይቆማሉ። የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፥
18:18b.REV.018.018የመቃጠልዋንም ጢስ ባዩ ጊዜ። ታላቂቱን ከተማ የምትመስላት ምን ከተማ ነበረች? እያሉ ጮኹ።
18:19b.REV.018.019በራሳቸውም ላይ ትቢያ ነስንሰው እያለቀሱና እያዘኑ። በባሕር መርከቦች ያሉአቸውን ሁሉ ከባለ ጠግነትዋ የተነሣ ባለ ጠጋዎች ላደረገች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት፥ ወዮላት፥ በአንድ ሰዓት ጠፍታለችና እያሉ ጮኹ።
18:20b.REV.018.020ሰማይ ሆይ፥ ቅዱሳን ሐዋርያት ነቢያትም ሆይ፥ በእርስዋ ላይ ደስ ይበላችሁ፥ እግዚአብሔር ፈርዶላችኋልና።
18:21b.REV.018.021አንድም ብርቱ መልአክ ትልቅን ወፍጮ የሚመስልን ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር ወረወረው እንዲህ ሲል። ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ ተገፍታ ትወድቃለች ከእንግዲህም ወዲህ ከቶ አትገኝም።
18:22b.REV.018.022በገና የሚመቱና የሚዘምሩም ድምፅ እንቢልታንና መለከትንም የሚነፉ ድምፅ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥ የእጅ ጥበብም ሁሉ አንድ ብልሃተኛ እንኳ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፥ የወፍጮ ድምጽም ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፥
18:23b.REV.018.023የመብራትም ብርሃን ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፥ የሙሽራና የሙሽራይቱም ድምጽ ከእንግዲህ ወዲህ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ነጋዴዎችሽ የምድር መኳንንት ነበሩና፥ በአስማትሽም አሕዛብ ሁሉ ስተዋልና።
18:24b.REV.018.024በእርስዋም ውስጥ የነቢያትና የቅዱሳን ደም በምድርም የታረዱ ሁሉ ደም ተገኘባት።
19
19:1b.REV.019.001ከዚህ በኋላ በሰማይ። ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፥ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ።
19:3b.REV.019.003ደግመውም። ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።
19:4b.REV.019.004ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር። አሜን፥ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት።
19:5b.REV.019.005ድምፅም። ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ
19:6b.REV.019.006ሲል ከዙፋኑ ወጣ። እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል። ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።
19:7b.REV.019.007የበጉ ሰርግ ስለ ደረሰ ሚስቱም ራስዋን ስላዘጋጀች ደስ ይበለን ሐሤትም እናድርግ ክብርንም ለእርሱ እናቅርብ።
19:8b.REV.019.008ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ተሰጥቶአታል። ቀጭኑ የተልባ እግር የቅዱሳን ጽድቅ ሥራ ነውና።
19:9b.REV.019.009እርሱም። ወደ በጉ ሰርግ እራት የተጠሩ ብፁዓን ናቸው ብለህ ጻፍ አለኝ። ደግሞም። ይህ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቃል ነው አለኝ።
19:10b.REV.019.010ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም። እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ።
19:11b.REV.019.011ሰማይም ተከፍቶ አየሁ፥ እነሆም አምባላይ ፈረስ፥ የተቀመጠበትም የታመነና እውነተኛ ይባላል፥ በጽድቅም ይፈርዳል ይዋጋልም።
19:12b.REV.019.012ዓይኖቹም እንደ እሳት ነበልባል ናቸው፥ በራሱ ላይም ብዙ ዘውዶች አሉ፥ ከእርሱም በቀር አንድ እንኳ የማያውቀው የተጻፈ ስም አለው፤
19:13b.REV.019.013በደምም የተረጨ ልብስ ተጐናጽፎአል፥ ስሙም የእግዚአብሔር ቃል ተብሎአል።
19:14b.REV.019.014በሰማይም ያሉት ጭፍራዎች ነጭና ጥሩ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ ለብሰው በአምባላዮች ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር።
19:15b.REV.019.015አሕዛብንም ይመታበት ዘንድ ስለታም ሰይፍ ከአፉ ይወጣል፤ እርሱም በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እርሱም ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔርን የብርቱ ቍጣውን ወይን መጥመቂያ ይረግጣል።
19:16b.REV.019.016በልብሱና በጭኑም የተጻፈበት። የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው።
19:17b.REV.019.017አንድም መልአክ በፀሐይ ውስጥ ቆሞ አየሁ፥ በሰማይም መካከል ለሚበሩ ወፎች ሁሉ። መጥታችሁ የነገሥታትን ሥጋና የሻለቃዎችን ሥጋ የብርቱዎችንም ሥጋ የፈረሶችንም በእነርሱም የተቀመጡትን ሥጋ የጌታዎችንና የባሪያዎችንም የታናናሾችንና የታላላቆችንም ሁሉ ሥጋ እንድትበሉ ወደ ታላቁ ወደ እግዚአብሔር እራት ተከማቹ ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።
19:19b.REV.019.019በፈረሱም የተቀመጠውን ጭፍራዎቹንም ይወጉ ዘንድ አውሬውና የምድር ነገሥታት ጭፍራዎቻቸውም ተከማችተው አየሁ።
19:20b.REV.019.020አውሬውም ተያዘ በእርሱም ፊት ተአምራትን እያደረገ የአውሬውን ምልክት የተቀበሉትን ለምስሉም የሰገዱትን ያሳተ ሐሰተኛው ነቢይ ከእርሱ ጋር ተያዘ፤ ሁለቱም በሕይወት ሳሉ በዲን ወደሚቃጠል ወደ እሳት ባሕር ተጣሉ።
19:21b.REV.019.021የቀሩትም በፈረስ ላይ ከተቀመጠው ከአፉ በሚወጣው ሰይፍ ተገደሉ፤ ወፎችም ሁሉ ከሥጋቸው ጠገቡ።
20
20:1b.REV.020.001የጥልቁንም መክፈቻና ታላቁን ሰንሰለት በእጁ የያዘ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።
20:2b.REV.020.002የቀደመውንም እባብ ዘንዶውን እርሱም ዲያብሎስና ሰይጣን የተባለውን ያዘው፥
20:3b.REV.020.003ሺህ ዓመትም አሰረው፥ ወደ ጥልቅም ጣለው አሕዛብንም ወደ ፊት እንዳያስት ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በእርሱ ላይ ዘግቶ ማኅተም አደረገበት፤ ከዚያም በኋላ ለጥቂት ጊዜ ይፈታ ዘንድ ይገባዋል።
20:4b.REV.020.004ዙፋኖችንም አየሁ፥ በእነርሱም ላይ ለተቀመጡት ዳኝነት ተሰጣቸው፤ ስለ ኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች ነፍሳት፥ ለአውሬውና ለምስሉም ያልሰገዱትን ምልክቱንም በግምባራቸው በእጆቻቸውም ላይ ያልተቀበሉትን አየሁ፤ ከክርስቶስም ጋር ሺህ ዓመት ኖሩና ነገሡ።
20:5b.REV.020.005የቀሩቱ ሙታን ግን ይህ ሺህ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ በሕይወት አልኖሩም። ይህ የፊተኛው ትንሣኤ ነው።
20:6b.REV.020.006በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።
20:7b.REV.020.007ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፥
20:8b.REV.020.008በአራቱም በምድር ማዕዘን ያሉትን አሕዛብ፥ ጎግንና ማጎግን፥ እንዲያስታቸው ለሰልፍም እንዲያስከትታቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸውም እንደ ባሕር አሸዋ የሚያህል ነው።
20:9b.REV.020.009ወደ ምድርም ስፋት ወጡ የቅዱሳንንም ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ እሳትም ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወርዳ በላቻቸው።
20:10b.REV.020.010ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።
20:11b.REV.020.011ታላቅና ነጭ ዙፋንን በእርሱም ላይ የተቀመጠውን አየሁ፥ ምድርና ሰማይም ከፊቱ ሸሹ ስፍራም አልተገኘላቸውም።
20:12b.REV.020.012ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፥ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ።
20:13b.REV.020.013ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፥ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ።
20:14b.REV.020.014ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።
20:15b.REV.020.015በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።
21
21:1b.REV.021.001አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፥ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፥ ባሕርም ወደ ፊት የለም።
21:2b.REV.021.002ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ፥ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።
21:3b.REV.021.003ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤
21:4b.REV.021.004እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
21:5b.REV.021.005በዙፋንም የተቀመጠው። እነሆ፥ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ።
21:6b.REV.021.006አለኝም። ተፈጽሞአል። አልፋና ዖሜጋ፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ። ለተጠማ ከሕይወት ውኃ ምንጭ እንዲያው እኔ እሰጣለሁ።
21:7b.REV.021.007ድል የሚነሣ ይህን ይወርሳል አምላክም እሆነዋለሁ እርሱም ልጅ ይሆነኛል።
21:8b.REV.021.008ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።
21:9b.REV.021.009ሰባቱም ኋለኛዎች መቅሠፍቶች የሞሉባቸውን ሰባቱን ጽዋዎች ከያዙት ከሰባቱ መላእክት አንዱ መጥቶ። ወደዚህ ና፥ የበጉንም ሚስት ሙሽራይቱን አሳይሃለሁ ብሎ ተናገረኝ።
21:10b.REV.021.010በመንፈስም ወደ ታላቅና ወደ ረጅም ተራራ ወሰደኝ፥ የእግዚአብሔርም ክብር ያለባትን ቅድስቲቱን ከተማ ኢየሩሳሌምን ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አሳየኝ፤ ብርሃንዋም እጅግ እንደ ከበረ ድንጋይ እንደ ኢያሰጲድ ድንጋይ ሆኖ እንደ ብርሌ የጠራ ነበረ፤
21:12b.REV.021.012ታላቅና ረጅም ቅጥር ነበራት፥ አሥራ ሁለትም ደጆች ነበሩአት በደጆቹም አሥራ ሁለት መላእክት ቆሙ፥ የአሥራ ሁለቱም የእስራኤል ልጆች ነገዶች ስሞች ተጽፈውባቸው ነበር።
21:13b.REV.021.013በምሥራቅ ሦስት ደጆች፥ በሰሜንም ሦስት ደጆች፥ በደቡብም ሦስት ደጆች፥ በምዕራብም ሦስት ደጆች ነበሩ።
21:14b.REV.021.014ለከተማይቱም ቅጥር አሥራ ሁለት መሠረቶች ነበሩአት፥ በእነርሱም ውስጥ የአሥራ ሁለቱ የበጉ ሐዋርያት ስሞች ተጽፈው ነበር።
21:15b.REV.021.015የተናገረኝም ከተማይቱንና ደጆችዋን ቅጥርዋንም ይለካ ዘንድ የወርቅ ዘንግ ነበረው።
21:16b.REV.021.016ከተማይቱም አራት ማዕዘን ነበራት፥ ርዝመትዋም እንደ ስፋትዋ ልክ ነበረ። ከተማይቱንም በዘንግ ለካት አሥራ ሁለትም ሺህ ምዕራፍ ሆነች፤ ርዝመትዋና ስፋትዋ ከፍታዋም ትክክል ነው።
21:17b.REV.021.017ቅጥርዋንም ለካ፥ መቶ አርባ አራት ክንድ በሰው ልክ፥ እርሱም በመልአክ ልክ።
21:18b.REV.021.018ቅጥርዋም ከኢያሰጲድ የተሠራ ነበረ፥ ከተማይቱም ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረች።
21:19b.REV.021.019የከተማይቱም ቅጥር መሠረት በከበረ ድንጋይ ሁሉ ተጌጦ ነበር፤ ፊተኛው መሠረት ኢያሰጲድ፥ ሁለተኛው ሰንፔር፥ ሦስተኛው ኬልቄዶን፥ አራተኛው መረግድ፥
21:20b.REV.021.020አምስተኛው ሰርዶንክስ፥ ስድስተኛው ሰርድዮን፥ ሰባተኛው ክርስቲሎቤ፥ ስምንተኛው ቢረሌ፥ ዘጠነኛው ወራውሬ፥ አሥረኛው ክርስጵራስስ፥ አሥራ አንደኛው ያክንት፥ አሥራ ሁለተኛው አሜቴስጢኖስ ነበረ።
21:21b.REV.021.021አሥራ ሁለቱም ደጆች አሥራ ሁለት ዕንቆች ነበሩ፤ እየአንዳንዱ ደጅ ከአንድ ዕንቍ የተሠራ ነበረ። የከተማይቱም አደባባይ ጥሩ ብርጭቆ የሚመስል ጥሩ ወርቅ ነበረ።
21:22b.REV.021.022ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርስዋ ዘንድ አላየሁም።
21:23b.REV.021.023ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለ ሆነ፥ ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።
21:24b.REV.021.024አሕዛብም በብርሃንዋ ይመላለሳሉ፥ የምድርም ነገሥታት ክብራቸውን ወደ እርስዋ ያመጣሉ፤
21:25b.REV.021.025በዚያም ሌሊት ስለሌለ ደጆችዋ በቀን ከቶ አይዘጉም፥
21:26b.REV.021.026የአሕዛብንም ግርማና ክብር ወደ እርስዋ ያመጣሉ።
21:27b.REV.021.027ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።
22
22:1b.REV.022.001በአደባባይዋም መካከል ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብርሌ የሚያንጸባርቀውን የሕይወትን ውኃ ወንዝ አሳየኝ።
22:2b.REV.022.002በወንዙም ወዲያና ወዲህ በየወሩ እያፈራ አሥራ ሁለት ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፥ የዛፉም ቅጠሎች ለሕዝብ መፈወሻ ነበሩ።
22:3b.REV.022.003ከእንግዲህም ወዲህ መርገም ከቶ አይሆንም። የእግዚአብሔርና የበጉም ዙፋን በእርስዋ ውስጥ ይሆናል፥ ባሪያዎቹም ያመልኩታል፥ ፊቱንም ያያሉ፥
22:4b.REV.022.004ስሙም በግምባሮቻቸው ይሆናል።
22:5b.REV.022.005ከእንግዲህም ወዲህ ሌሊት አይሆንም፥ ጌታ አምላክም በእነርሱ ላይ ያበራላቸዋልና የመብራት ብርሃንና የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሣሉ።
22:6b.REV.022.006እርሱም። እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው፥ የነቢያትም መናፍስት ጌታ አምላክ በቶሎ ሊሆን የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ መልአኩን ሰደደ።
22:7b.REV.022.007እነሆም፥ በቶሎ እመጣለሁ። የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል የሚጠብቅ ብፁዕ ነው አለኝ።
22:8b.REV.022.008ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ። በሰማሁትና ባየሁትም ጊዜ ይህን ባሳየኝ በመልአኩ እግር ፊት እሰግድ ዘንድ ተደፋሁ።
22:9b.REV.022.009እርሱም። እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር ከወንድሞችህም ከነቢያት ጋር የዚህንም መጽሐፍ ቃል ከሚጠብቁ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ አለኝ።
22:10b.REV.022.010ለእኔም። ዘመኑ ቀርቦአልና የዚህን መጽሐፍ ትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው።
22:11b.REV.022.011ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ።
22:12b.REV.022.012እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ።
22:13b.REV.022.013አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።
22:14b.REV.022.014ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው።
22:15b.REV.022.015ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።
22:16b.REV.022.016እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልአኬን ላክሁ። እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፥ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ።
22:17b.REV.022.017መንፈሱና ሙሽራይቱም። ና ይላሉ። የሚሰማም። ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።
22:18b.REV.022.018በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል ለሚሰማ ሁሉ እኔ እመሰክራለሁ፤ ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል፤
22:19b.REV.022.019ማንምም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ቢያጎድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተጻፉት ከሕይወት ዛፍና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ዕድሉን ያጎድልበታል።
22:20b.REV.022.020ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።
22:21b.REV.022.021የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን።
- Holder of rights
- Multilingual Bible Corpus
- Citation Suggestion for this Object
- TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. Revelation (Amharic). Revelation (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8AD6-B