Zephaniah (Amharic)
1
1:1b.ZEP.001.001በይሁዳ ንጉሥ በአሞጽ ልጅ በኢዮስያስ ዘመን ወደ ሕዝቅያስ ልጅ ወደ አማርያ ልጅ ወደ ጎዶልያስ ልጅ ወደ ኵሲ ልጅ ወደ ሶፎንያስ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
1:2b.ZEP.001.002ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ፈጽሜ አጠፋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
1:3b.ZEP.001.003ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፤ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
1:4b.ZEP.001.004እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤
1:5b.ZEP.001.005በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፥ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን፥
1:6b.ZEP.001.006እግዚአብሔርንም ከመከተል የተመለሱትን፥ እግዚአብሔርንም ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ።
1:7b.ZEP.001.007የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፥ እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጅቶአልና፥ የጠራቸውንም ቀድሶአልና በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ።
1:8b.ZEP.001.008በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ።
1:9b.ZEP.001.009በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፥ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ።
1:10b.ZEP.001.010በዚያ ቀን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፥ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፥ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል።
1:11b.ZEP.001.011እናንተ በመክቴሽ የምኖሩ ሆይ፥ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ጠፍተዋልና፥ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቈርጠዋልና አልቅሱ።
1:12b.ZEP.001.012በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፥ በልባቸውም። እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፥ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ።
1:13b.ZEP.001.013ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፥ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፥ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፥ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም።
1:14b.ZEP.001.014ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል።
1:15b.ZEP.001.015ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፥ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፥ የጨለማና የጭጋግ ቀን፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፥
1:16b.ZEP.001.016በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው።
1:17b.ZEP.001.017በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፥ ሥጋቸውም እንደ ጕድፍ ይፈስሳል።
1:18b.ZEP.001.018በእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።
2
2:1b.ZEP.002.001እናንተ እፍረት የሌላችሁ ሕዝብ ሆይ፥ ትእዛዝ ሳይወጣ፥ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ትኵሳት ሳይመጣባችሁ፥ የእግዚአብሔርም ቍጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፥ ተከማቹም።
2:3b.ZEP.002.003እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፥ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።
2:4b.ZEP.002.004ጋዛ ትበረበራለች፥ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ አዞጦንንም በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዱአታል፥ አቃሮንም ትነቀላለች።
2:5b.ZEP.002.005በባሕር ዳር ለሚኖሩ ለከሊታውያን ሕዝብ ወዮላቸው! የፍልስጥኤማውያን ምድር ከነዓን ሆይ፥ የእግዚአብሔር ቃል በአንተ ላይ ነው፥ የሚቀመጥብህም ሰው እንዳይኖር አጠፋሃለሁ።
2:6b.ZEP.002.006ቀርጤስም የእረኞች መኖሪያና የመንጎች በረት ይሆናል።
2:7b.ZEP.002.007የባሕሩም ዳር ለይሁዳ ቤት ቅሬታ ይሆናል፥ በዚያም ይሰማራሉ፤ አምላካቸው እግዚአብሔር ይጐበኛቸዋልና፥ ምርኮአቸውንም ይመልሳልና በአስቀሎና ቤቶች ውስጥ ማታ ይተኛሉ።
2:8b.ZEP.002.008በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፥ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ።
2:9b.ZEP.002.009ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፥ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ፥ የሳማ ስፍራና የጨው ጕድጓድ ለዘላለምም ምድረ በዳ ሆነው ይኖራሉ፤ የሕዝቤም ቅሬታ ይበዘብዛቸዋል፥ ከወገኔም የተረፉት ይወርሱአቸዋል።
2:10b.ZEP.002.010በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ አላግጠዋልና፥ እየታበዩም ተናግረዋልና ይህ ስለ ትዕቢታቸው ያገኛቸዋል።
2:11b.ZEP.002.011እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የተፈራ ይሆናል፥ የምድርንም አማልክት ሁሉ ያከሳቸዋል፤ በአሕዛብም ደሴቶች ሁሉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በስፍራቸው ሆነው ለእርሱ ይሰግዳሉ።
2:12b.ZEP.002.012እናንተም ኢትዮጵያውያን ደግሞ፥ በሰይፌ ትገደላላችሁ።
2:13b.ZEP.002.013እርሱም በሰሜን ላይ እጁን ይዘረጋል፥ አሦርንም ያጠፋል፤ ነነዌንም ባድማ፥ እንደ በረሃም ደረቅ ያደርጋታል።
2:14b.ZEP.002.014መንጎችም የምድርም አራዊት ሁሉ በውስጥዋ ይመሰጋሉ፤ ይብራና ጃርት በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፤ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል፤ የዝግባም እንጨት ሥራ ይገለጣልና በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል።
2:15b.ZEP.002.015ተዘልላ የተቀመጠች፥ በልብዋም። እኔ ነኝ፥ ከእኔም በቀር ሌላ የለም ያለች ደስተኛይቱ ከተማ ይህች ናት፤ አራዊት የሚመሰጉባት ባድማ እንዴት ሆነች! በእርስዋ በኩል የሚያልፈው ሁሉ እጁን እያወዛወዘ ያፍዋጫል።
3
3:1b.ZEP.003.001ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት!
3:2b.ZEP.003.002ድምፅን አልሰማችም፥ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፥ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።
3:3b.ZEP.003.003በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ፈራጆችዋም እስከ ነገ ድረስ ምንም እንደማያስቀሩ እንደ ማታ ተኵላዎች ናቸው።
3:4b.ZEP.003.004ነቢያቶችዋ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው፤ ካህናቶችዋም መቅደሱን አርክሰዋል፥ በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል።
3:5b.ZEP.003.005እግዚአብሔር በውስጥዋ ጻድቅ ነው፤ ክፋትን አያደርግም፤ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፥ ሳያወጣውም አይቀርም፤ ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም።
3:6b.ZEP.003.006አሕዛብን አጥፍቻለሁ፤ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፤ መንገዳቸውን ማንም እንዳያልፍባት ምድረ በዳ አድርጌአለሁ፥ ከተሞቻቸውም ማንም እንዳይኖርባቸው፥ አንድስ እንኳ እንዳይቀመጥባቸው ፈርሰዋል።
3:7b.ZEP.003.007እኔም- ይፈሩኛል፥ ተግሣጽንም ይቀበላሉ፤ ካዘዝኋትም ሁሉ ከዓይንዋ ምንም አይጠፋም ብዬ ነበር፤ እነርሱ ግን በማለዳ ተነሥተው ድርጊታቸውን ሁሉ አረከሱ።
3:8b.ZEP.003.008መዓቴንና የቍጣዬን ትኵሳት ሁሉ አፈስስባቸው ዘንድ ፍርዴ አሕዛብን ለመሰብሰብ፥ መንግሥታትንም ለማከማቸት ነውና፥ ምድርም ሁሉ በቅንዓቴ እሳት ትበላለችና ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሣበት ቀን ድረስ ጠብቁኝ፥ ይላል እግዚአብሔር።
3:9b.ZEP.003.009በዚያን ጊዜም አሕዛብ ሁሉ አንድ ሆነው እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ስሙን እንዲጠሩ ንጹሐን ልሳን እመልስላቸዋለሁ።
3:10b.ZEP.003.010ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ፥ የተበተኑት ሴቶች ልጆቼ፥ ቍርባኔን ያመጡልኛል።
3:11b.ZEP.003.011በዚያን ጊዜ እየታበዩ የሚፎክሩትን ከመካከልሽ አወጣለሁና፥ አንቺም በቅዱስ ተራራዬ ዳግመኛ አትኰሪምና በዚያ ቀን በእኔ ላይ ተላልፈሽ በሠራሽው ሥራ ሁሉ አትፍሪም።
3:12b.ZEP.003.012በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ፤ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ።
3:13b.ZEP.003.013የእስራኤል ቅሬታ ኃጢአትን አይሠሩም፥ ሐሰትንም አይናገሩም፥ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፥ ይመሰጉማል፥ የሚያስፈራቸውም የለም።
3:14b.ZEP.003.014የጽዮን ልጅ ሆይ፥ ዘምሪ፤ እስራኤል ሆይ፥ እልል በል፤ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ በፍጹም ልብሽ ሐሤት አድርጊ ደስም ይበልሽ።
3:15b.ZEP.003.015እግዚአብሔር ፍርድሽን አስወግዶአል፥ ጠላትሽንም ጥሎአል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከልሽ አለ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉ ነገርን አታዪም።
3:16b.ZEP.003.016በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም። ጽዮን ሆይ፥ አትፍሪ፥ እጆችሽም አይዛሉ።
3:17b.ZEP.003.017አምላክሽ እግዚአብሔር በመካከልሽ ታዳጊ ኃያል ነው፤ በደስታ በአንቺ ደስ ይለዋል፥ በፍቅሩም ያርፋል፥ በእልልታም በአንቺ ደስ ይለዋል ይባላል።
3:18b.ZEP.003.018ከጉባኤው ርቀው የሚያዝኑትን፥ ከአንቺም የሆኑትን እሰበስባለሁ፤ ስድብ እንደ ሸክም ከብዶባቸው ነበር።
3:19b.ZEP.003.019በዚያ ዘመን እነሆ፥ ባስጨነቁሽ ሁሉ ላይ አደርግባቸዋለሁ፤ አንካሳይቱንም አድናለሁ፥ የተጣለችውንም እሰበስባታለሁ፤ ባፈሩባትም ምድር ሁሉ ላይ ለምስጋናና ለከበረ ስም አደርጋቸዋለሁ።
3:20b.ZEP.003.020በዚያ ዘመን አስገባችኋለሁ፥ በዚያም ዘመን እሰበስባችኋለሁ፤ ምርኮአችሁንም በዓይናችሁ ፊት በመለስሁ ጊዜ በምድር አሕዛብ ሁሉ መካከል ለከበረ ስምና ለምስጋና አደርጋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
- Holder of rights
- Multilingual Bible Corpus
- Citation Suggestion for this Object
- TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. Zephaniah (Amharic). Zephaniah (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8A7C-2