Daniel (Amharic)

Daniel (Amharic)

1

1:1b.DAN.001.001የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በነገሠ በሦስተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ከበባት።

1:2b.DAN.001.002ጌታም የይሁዳን ንጉሥ ኢዮአቄምን ከእግዚአብሔርም ቤት ዕቃ ከፍሎ በእጁ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም ወደ ሰናዖር ምድር ወደ አምላኩ ቤት ወሰደው፥ ዕቃውንም ወደ አምላኩ ግምጃ ቤት አገባው።

1:3b.DAN.001.003ንጉሡም ነውር የሌለባቸውንና መልከ መልካሞቹን፥ በጥበብ ሁሉ የሚያስተውሉትን እውቀትም የሞላባቸውን ብልሃተኞችና አስተዋዮች የሆኑትን፥ በንጉሡም ቤት መቆም የሚችሉትን ብላቴኖች ከእስራኤል ልጆች ከነገሥታቱና ከመሳፍንቱ ዘር ያመጣ ዘንድ የከለዳውያንንም ትምህርትና ቋንቋ ያስተምሩአቸው ዘንድ ለጃንደረቦች አለቃ ለአስፋኔዝ ነገረ።

1:5b.DAN.001.005ንጉሡም ሦስት ዓመት ያሳድጉአቸው ዘንድ፥ ከዚያም በኋላ በንጉሡ ፊት ይቆሙ ዘንድ ከንጉሡ መብል ከሚጠጣውም ጠጅ በየዕለቱ ድርጎአቸውን አዘዘላቸው።

1:6b.DAN.001.006በእነዚህም መካከል ከይሁዳ ልጆች ዳንኤልና አናንያ ሚሳኤልና አዛርያ ነበሩ።

1:7b.DAN.001.007የጃንደረቦቹም አለቃ ስም አወጣላቸው፤ ዳንኤልን ብልጣሶር፥ አናንያንም ሲድራቅ፥ ሚሳኤልንም ሚሳቅ፥ አዛርያንም አብደናጎ ብሎ ጠራቸው።

1:8b.DAN.001.008ዳንኤልም በንጉሡ መብልና በሚጠጣው ጠጅ እንዳይረክስ በልቡ አሰበ፤ እንዳይረክስም የጃንደረቦቹን አለቃ ለመነ።

1:9b.DAN.001.009እግዚአብሔርም በጃንደረቦቹ አለቃ ፊት ለዳንኤል ሞገስንና ምሕረትን ሰጠው።

1:10b.DAN.001.010የጃንደረቦቹም አለቃ ዳንኤልን። መብሉንና መጠጡን ያዘዘላችሁን ጌታዬን ንጉሡን እፈራለሁ፤ በዕድሜ እንደ እናንተ ካሉ ብላቴኖች ይልቅ ፊታችሁ ከስቶ ያየ እንደ ሆነ፥ ከንጉሡ ዘንድ በራሴ ታስፈርዱብኛላችሁ አለው።

1:11b.DAN.001.011ዳንኤልም የጃንደርቦቹ አለቃ በዳንኤልና በአናንያ በሚሳኤልና በአዛርያ ላይ የሾመውን ሜልዳርን።

1:12b.DAN.001.012እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የምንበላውንም ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፤

1:13b.DAN.001.013ከዚያም በኋላ የእኛን ፊትና ከንጉሡ መብል የሚበሉትን የብላቴኖችን ፊት ተመልከት፤ እንዳየኸውም ሁሉ ከባሪያዎችህ ጋር የወደድኸውን አድርግ አለው።

1:14b.DAN.001.014ይህንም ነገራቸውን ሰምቶ አሥር ቀን ፈተናቸው።

1:15b.DAN.001.015ከአሥር ቀንም በኋላ ከንጉሡ መብል ከበሉ ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸው አምሮ ሥጋቸውም ወፍሮ ታየ።

1:16b.DAN.001.016ሜልዳርም መብላቸውንና የሚጠጡትን ጠጅ አስቀርቶ ጥራጥሬውን ሰጣቸው።

1:17b.DAN.001.017ለእነዚህም ለአራቱ ብላቴኖች እግዚአብሔር በትምህርትና በጥበብ ሁሉ እውቀትንና ማስተዋልን ሰጣቸው፤ ዳንኤልም በራእይና በሕልም ሁሉ አስተዋይ ነበረ።

1:18b.DAN.001.018እነርሱም ይገቡ ዘንድ ንጉሡ ያዘዘው ቀን በተፈጸመ ጊዜ፥ የጃንደረቦቹ አለቃ ወደ ናቡከደነፆር ዘንድ አገባቸው።

1:19b.DAN.001.019ንጉሡም በተነጋገራቸው ጊዜ ከብላቴኖቹ ሁሉ እንደ ዳንኤልና እንደ አናንያ እንደ ሚሳኤልና እንደ አዛርያ ያለ አልተገኘም፤ በንጉሡም ፊት ቆሙ።

1:20b.DAN.001.020ንጉሡም በጠየቃቸው በጥበብና በማስተዋል ነገር ሁሉ በግዛቱ ሁሉ ከሚኖሩ የሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ እነርሱ አሥር እጅ የበለጡ ሆነው አገኘባቸው።

1:21b.DAN.001.021ዳንኤልም እስከ ንጉሡ እስከ ቂሮስ መጀመሪያ ዓመት ተቀመጠ።

2

2:1b.DAN.002.001ናቡከደነፆርም በነገሠ በሁለተኛው ዓመት ናቡከደነፆር ሕልም አለመ፤ መንፈሱም ታወከ፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።

2:2b.DAN.002.002ለንጉሡም ሕልሙን እንዲነግሩት ንጉሡ የሕልም ተርጓሚዎቹንና አስማተኞቹን መተተኞቹንና ከለዳውያኑንም ይጠሩ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም ገብተው በንጉሡ ፊት ቆሙ።

2:3b.DAN.002.003ንጉሡም። ሕልም አልሜአለሁ፥ ሕልሙንም ለማወቅ መንፈሴ ታውኮአል አላቸው።

2:4b.DAN.002.004ከለዳውያኑም ንጉሡን በሶርያ ቋንቋ። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ ለባሪያዎችህ ሕልምህን ንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን ብለው ተናገሩት።

2:5b.DAN.002.005ንጉሡም መለሰ ከለዳውያኑንም። ነገሩ ከእኔ ዘንድ ርቆአል፤ ሕልሙንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፥ ትቈረጣላችሁ ቤቶቻችሁም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ።

2:6b.DAN.002.006ሕልሙንና ፍቺውን ግን ብታሳዩ፥ ከእኔ ዘንድ ስጦታና ዋጋ ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ፤ ስለዚህም ሕልሙንና ፍቺውን አሳዩኝ አላቸው።

2:7b.DAN.002.007ሁለተኛም ጊዜ መልሰው። ንጉሡ ለባሪያዎቹ ሕልሙን ይንገር፥ እኛም ፍቺውን እናሳያለን አሉት።

2:8b.DAN.002.008ንጉሡ መልሶ። ነገሩ ከእኔ ዘንድ እንደ ራቀ ታውቃላችሁና ጊዜውን እንድታስረዝሙ እኔ አውቃለሁ።

2:9b.DAN.002.009ሕልሙንም ባታስታውቁኝ አንድ ፍርድ አለባችሁ፤ ጊዜውን ለማሳለፍ የሐሰትንና የተንኰልን ቃል ልትነግሩኝ አዘጋጅታችኋል፤ ስለዚህ ሕልሙን ንገሩኝ፥ ፍቺውንም ማሳየት እንድትችሉ አውቃለሁ አለ።

2:10b.DAN.002.010ከለዳውያኑም በንጉሡ ፊት መልሰው። የንጉሡን ነገር ያሳይ ዘንድ የሚችል ሰው በምድር ላይ የለም፤ ከነገሥታትም ታላቅና ኃይለኛ የሆነ እንደዚህ ያለ ነገር የሕልም ተርጓሚንና አስማተኛን ከለዳዊንም አልጠየቀም።

2:11b.DAN.002.011ንጉሡም የሚጠይቀው ነገር የቸገረ ነው፤ መኖሪያቸው ከሰው ጋር ካልሆነ ከአማልክት በቀር በንጉሡ ፊት የሚያሳየው ማንም የለም አሉ።

2:12b.DAN.002.012ስለዚህም ንጉሡ ተበሳጨ እጅግም ተቈጣ፥ የባቢሎንንም ጠቢባን ሁሉ ያጠፉ ዘንድ አዘዘ።

2:13b.DAN.002.013ትእዛዝም ወጣ፥ ጠቢባንንም ይገድሉ ዘንድ ጀመሩ፤ ዳንኤልንና ባልንጀሮቹንም ይገድሉ ዘንድ ፈለጉአቸው።

2:14b.DAN.002.014የዚያን ጊዜም ዳንኤል የባቢሎንን ጠቢባን ይገድል ዘንድ የወጣውን የንጉሡን የዘበኞቹ አለቃ አርዮክን በፈሊጥና በማስተዋል ተናገረው፤

2:15b.DAN.002.015ለንጉሡም አለቃ ለአርዮክ መልሶ። የንጉሡ ትእዛዝ ስለ ምን ቸኰለ? አለው። አርዮክም ነገሩን ለዳንኤል አስታወቀው።

2:16b.DAN.002.016ዳንኤልም ገብቶ ፍቺውን ለንጉሡ የሚያስታውቅበት ጊዜ ይሰጠው ዘንድ ንጉሡን ለመነ።

2:17b.DAN.002.017የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ቤቱ ሄደ። ዳንኤልም ባልንጀሮቹም ከቀሩት ከባቢሎን ጠቢባን ጋር እንዳይሞቱ ስለዚህ ምሥጢር ምሕረትን ከሰማይ አምላክ ይለምኑ ዘንድ ነገሩን ለባልንጀሮቹ ለአናንያና ለሚሳኤል ለአዛርያ አስታወቃቸው።

2:19b.DAN.002.019የዚያን ጊዜም ምሥጢሩ በሌሊት ራእይ ለዳንኤል ተገለጠለት፤ ዳንኤልም የሰማይን አምላክ አመሰገነ።

2:20b.DAN.002.020ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና የእግዚአብሔር ስም ከዘላለም እስከ ዘላለም ይባረክ፤

2:21b.DAN.002.021ጊዜያትንና ዘመናትን ይለውጣል፤ ነገሥታትን ያፈልሳል፥ ነገሥታትንም ያስነሣል፤ ጥበብን ለጠቢባን እውቀትንም ለአስተዋዮች ይሰጣል።

2:22b.DAN.002.022የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።

2:23b.DAN.002.023ጥበብንና ኃይልን የሰጠኸኝ፥ እኛም የለመንንህን ነገር አሁን ያስታወቅኸኝ፥ አንተ የአባቶቼ አምላክ ሆይ፥ የንጉሡን ነገር አስታውቀኸኛልና እገዛልሃለሁ አመሰግንህማለሁ።

2:24b.DAN.002.024ከዚህም በኋላ ዳንኤል ንጉሡ የባቢሎንን ጠቢባን ያጠፋ ዘንድ ወዳዘዘው ወደ አርዮክ ገባ፤ በገባም ጊዜ። የባቢሎንን ጠቢባን አታጥፋ፤ ወደ ንጉሡ አስገባኝ፥ እኔም ፍቺውን ለንጉሡ አሳያለሁ አለው።

2:25b.DAN.002.025የዚያን ጊዜም አርዮክ ዳንኤልን ፈጥኖ ወደ ንጉሡ አስገባውና። ከይሁዳ ምርኮኞች ያለውን ለንጉሡ ፍቺውን የሚያስታውቀውን ሰው አግኝቼአለሁ አለው።

2:26b.DAN.002.026ንጉሡም መለሰ ብልጣሶርም የሚባለውን ዳንኤልን። ያየሁትን ሕልምና ፍቺውን ታስታውቀኝ ዘንድ ትችላለህን? አለው።

2:27b.DAN.002.027ዳንኤልም በንጉሡ ፊት መልሶ እንዲህ አለ። ንጉሡ የጠየቀውን ምሥጢር ጠቢባንና አስማተኞች የሕልም ተርጓሚዎችና ቃላተኞች ለንጉሡ ያሳዩ ዘንድ አይችሉም፤

2:28b.DAN.002.028ነገር ግን ምሥጢር የሚገልጥ አምላክ በሰማይ ውስጥ አለ፥ እርሱም በኋለኛው ዘመን የሚሆነውን ለንጉሡ ለናቡከደነፆር አስታውቆታል። በአልጋህ ላይ የሆነው ሕልምና የራስህ ራእይ ይህ ነው።

2:29b.DAN.002.029አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በኋላ የሚሆነው ምን እንደ ሆነ በአልጋህ ላይ ታስብ ነበር፤ ምሥጢርንም የሚገልጠው የሚሆነውን ነገር አስታውቆሃል።

2:30b.DAN.002.030ነገር ግን ይህ ምሥጢር ለእኔ መገለጡ ፍቺው ለንጉሡ ይታወቅ ዘንድ፥ አንተም የልብህን አሳብ ታውቅ ዘንድ ነው እንጂ በዚህ ዓለም ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥበብ ስለ በለጥሁ አይደለም።

2:31b.DAN.002.031አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ታላቅ ምስል አየህ፤ ይህም ምስል ታላቅና ብልጭልጭታው የበዛ ነበረ፥ በፊትህም ቆሞ ነበር፤ መልኩም ግሩም ነበረ።

2:32b.DAN.002.032የዚህም ምስል ራስ ጥሩ ወርቅ፥ ደረቱና ክንዶቹም ብር፥ ሆዱና ወገቡም ናስ፥

2:33b.DAN.002.033ጭኖቹም ብረት፥ እግሮቹም እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ ነበረ።

2:34b.DAN.002.034እጅም ሳይነካው ድንጋይ ከተራራው ተፈንቅሎ ከብረትና ከሸክላ የሆነውን የምስሉን እግሮች ሲመታና ሲፈጭ አየህ።

2:35b.DAN.002.035የዚያን ጊዜም ብረቱና ሸክላው፥ ናሱና ብሩ ወርቁም በአንድነት ተፈጨ፥ በመከርም ጊዜ በአውድማ ላይ እንዳለ እብቅ ሆነ፤ ነፋስም ወሰደው፥ ቦታውም አልታወቀም፤ ምስሉንም የመታ ድንጋይ ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ

2:36b.DAN.002.036ሕልሙ ይህ ነው፤ አሁንም ፍቺውን በንጉሡ ፊት እንናገራለን።

2:37b.DAN.002.037አንተ፥ ንጉሥ ሆይ፥ የሰማይ አምላክ መንግሥትንና ኃይልን፥ ብርታትንና ክብርን የሰጠህ የነገሥታት ንጉሥ አንተ ነህ።

2:38b.DAN.002.038በሚቀመጡበትም ስፍራ ሁሉ የሰው ልጆችንና የምድር አራዊትን የሰማይ ወፎችንም በእጅህ አሳልፎ ሰጥቶሃል፥ ለሁሉም ገዥ አድርጎሃል፤ አንተ የወርቁ ራስ ነህ።

2:39b.DAN.002.039ከአንተም በኋላ ከአንተ የሚያንስ ሌላ መንግሥት ይነሣል፤ ከዚያም በኋላ በምድር ሁሉ ላይ የሚገዛ ሌላ ሦስተኛ የናስ መንግሥት ይነሣል።

2:40b.DAN.002.040አራተኛውም መንግሥት ሁሉን እንደሚቀጠቅጥና እንደሚያደቅቅ ብረት ይበረታል፤ እነዚህንም ሁሉ እንደሚፈጭ ብረት ይቀጠቅጣል ይፈጭማል።

2:41b.DAN.002.041እግሮቹና ጣቶቹም እኩሉ ሸክላ እኩሉም ብረት ሆኖ እንዳየህ፥ እንዲሁ የተከፋፈለ መንግሥት ይሆናል፤ ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሁ፥ የብረት ብርታት ለእርሱ ይሆናል።

2:42b.DAN.002.042የእግሮቹም ጣቶች እኩሉ ብረት እኩሉም ሸክላ እንደ ነበሩ፥ እንዲሁ መንግሥቱ እኩሉ ብርቱ እኩሉ ደካማ ይሆናል።

2:43b.DAN.002.043ብረቱም ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየህ፥ እንዲሁ ከሰው ዘር ጋር ይደባለቃሉ፤ ነገር ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ፥ እንዲሁ እርስ በርሳቸው አይጣበቁም።

2:44b.DAN.002.044በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፥ ለዘላለምም ትቆማለች።

2:45b.DAN.002.045ድንጋዩም እጅ ሳይነካው ከተራራ ተፈንቅሎ ብረቱንና ናሱን ሸክላውንና ብሩን ወርቁንም ሲፈጨው እንዳየህ፥ እንዲሁ ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ታላቁ አምላክ ለንጉሡ አስታውቆታል፤ ሕልሙም እውነተኛ ፍቺውም የታመነ ነው።

2:46b.DAN.002.046የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥ የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም ያቀርቡለት ዘንድ አዘዘ።

2:47b.DAN.002.047ንጉሡም ዳንኤልን። ይህን ምሥጢር ትገልጥ ዘንድ ተችሎሃልና በእውነት አምላካችሁ የአማልክት አምላክ፥ የነገሥታትም ጌታ፥ ምሥጢርም ገላጭ ነው ብሎ ተናገረው።

2:48b.DAN.002.048ንጉሡም ዳንኤልን ከፍ ከፍ አደርገው፥ ብዙም ታላቅ ስጦታ ሰጠው፥ በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ ላይ ሾመው፥ በባቢሎንም ጠቢባን ሁሉ ላይ ዋነኛ አለቃ አደረገው።

2:49b.DAN.002.049ዳንኤልም ንጉሡን ለመነ፥ እርሱም ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ ሾማቸው፤ ዳንኤል ግን በንጉሡ በር ነበረ።

3

3:1b.DAN.003.001ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።

3:2b.DAN.003.002ንጉሡም ናቡከደነፆር መኳንንትንና ሹማምቶችን፥ አዛዦችንና አዛውንቶችን፥ በጅሮንዶችንና አማካሪዎችን፥ መጋቢዎችንም፥ አውራጃ ገዦችንም ሁሉ ይሰበስቡ ዘንድ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ይመጡ ዘንድ ላከ።

3:3b.DAN.003.003በዚያን ጊዜም መኳንንቱና ሹማምቶቹ፥ አዛዦቹና አዛውንቶቹ፥ በጅሮንዶቹና አማካሪዎቹ፥ መጋቢዎቹና አውራጃ ገዦቹ ሁሉ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ ተሰበሰቡ፤ ናቡከደነፆርም ባቆመው ምስል ፊት ቆሙ።

3:4b.DAN.003.004አዋጅ ነጋሪውም እየጮኸ እንዲህ አለ። ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የምትናገሩ ሆይ፥

3:5b.DAN.003.005የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ፥ ተደፍታችሁ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል እንድትሰግዱ ታዝዛችኋል።

3:6b.DAN.003.006ተደፍቶም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

3:7b.DAN.003.007ስለዚህ በዚያን ጊዜ አሕዛብ ሁሉ የመለከቱንና የእንቢልታውን፥ የመሰንቆውንና የክራሩን፥ የበገናውንና የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ፥ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የተናገሩ ሁሉ ተደፉ፥ ንጉሡም ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቅ ምስል ሰገዱ።

3:8b.DAN.003.008በዚያን ጊዜም ከለዳውያን ቀርበው አይሁድን ከሰሱ።

3:9b.DAN.003.009ለንጉሡም ለናቡከደነፆር ተናገሩ እንዲህም አሉ። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።

3:10b.DAN.003.010አንተ፥ ንጉሥ ሆይ። የመለከትንና የእንቢልታን፥ የመሰንቆንና የክራርን፥ የበገናንና የዋሽንትን፥ የዘፈንንም ሁሉ ድምፅ የሚሰማ ሰው ሁሉ ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ይስገድ፤

3:11b.DAN.003.011ተደፍቶም የማይሰግድ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል ብለህ አዘዝህ።

3:12b.DAN.003.012በባቢሎን አውራጃ ሥራ ላይ የሾምሃቸው ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም የሚባሉ አይሁድ አሉ፤ ንጉሥ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ትእዛዝህን እንቢ ብለዋል፤ አማልክትህን አያመልኩም፥ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል አይሰግዱም።

3:13b.DAN.003.013ናቡከደነፆርም በብስጭትና በቍጣ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም ያመጡ ዘንድ አዘዘ፤ እነዚህንም ሰዎች ወደ ንጉሡ ፊት አመጡአቸው።

3:14b.DAN.003.014ናቡከደነፆርም። ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ሆይ፥ አምላኬን አለማምለካችሁ፥ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?

3:15b.DAN.003.015አሁንም የመለከቱንና የእንቢልታውን የመሰንቆውንና የክራሩን የበገናውንና የዋሽንቱን የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ በሰማችሁ ጊዜ ተደፍታችሁ ላሠራሁት ምስል ብትሰግዱ መልካም ነው፤ ባትሰግዱ ግን በዚያ ጊዜ በሚነድድ እሳት እቶን ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ከእጄስ የሚያድናችሁ አምላክ ማን ነው? ብሎ ተናገራቸው።

3:16b.DAN.003.016ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም መለሱ ንጉሡንም። ናቡከደነፆር ሆይ፥ በዚህ ነገር እንመልስልህ ዘንድ አስፈላጊያችን አይደለም።

3:17b.DAN.003.017የምናመልከው አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፥ ንጉሥ ሆይ!

3:18b.DAN.003.018ነገር ግን፥ ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ባያድነን፥ አማልክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድለት እወቅ አሉት።

3:19b.DAN.003.019የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም ላይ ቍጣ ሞላበት፥ የፊቱም መልክ ተለወጠባቸው፤ እርሱም ተናገረ፥ የእቶንም እሳት ይነድድ ከነበረው ይልቅ ሰባት እጥፍ አድርገው እንዲያነድዱት አዘዘ።

3:20b.DAN.003.020ሲድራቅንና ሚሳቅንም አብደናጎንም ያስሩ ዘንድ፥ ወደሚነድድም ወደ እቶን እሳት ይጥሉአቸው ዘንድ በሠራዊቱ ውስጥ ከነበሩት ኃያላን አዘዘ።

3:21b.DAN.003.021የዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች ከሰናፊላቸውና ከቀሚሳቸው ከመጐናጸፊያቸውም ከቀረውም ልብሳቸው ጋር ታስረው በሚነድድ በእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።

3:22b.DAN.003.022የንጉሡም ትእዛዝ አስቸኳይ ስለሆነ የእቶኑም እሳት እጅግ ስለሚነድድ፥ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም የጣሉአቸውን ሰዎች የእሳቱ ወላፈን ገደላቸው።

3:23b.DAN.003.023እነዚህም ሦስቱ ሰዎች ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም ታስረው በሚነድደው በእቶኑ እሳት ውስጥ ወደቁ።

3:24b.DAN.003.024የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም። ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን? ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም። ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት።

3:25b.DAN.003.025እርሱም። እነሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለሁ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ።

3:26b.DAN.003.026የዚያን ጊዜም ናቡከደነፆር ወደሚነድደው ወደ እሳቱ እቶን በር ቀርቦ። እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች፥ ሲድራቅና ሚሳቅ አብደናጎም፥ ኑ ውጡ ብሎ ተናገራቸው። ሲድራቅና ሚሳቅም አብደናጎም ከእሳቱ መካከል ወጡ።

3:27b.DAN.003.027መሳፍንቱና ሹማምቶቹም አዛዦቹና የንጉሡ አማካሪዎች ተሰብስበው እሳቱ በእነዚያ ሰዎች አካል ላይ ኃይል እንዳልነበረው፥ የራሳቸውም ጠጕር እንዳልተቃጠለች፥ ሰናፊላቸውም እንዳልተለወጠ፥ የእሳቱም ሽታ እንዳልደረሰባቸው አዩ።

3:28b.DAN.003.028ናቡከደነፆርም መልሶ። መልአኩን የላከ፥ ከአምላካቸውም በቀር ማንም አምላክ እንዳያመልኩ ለእርሱም እንዳይሰግዱ ሰውነታቸውን አሳልፈው የሰጡትን የንጉሡንም ቃል የተላለፉትን በእርሱ የታመኑትን ባሪያዎቹን ያዳነ፥ የሲድራቅና የሚሳቅ የአብደናጎም አምላክ ይባረክ።

3:29b.DAN.003.029እኔም እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅና በሚሳቅ በአብደናጎም አምላክ ላይ የስድብን ነገር የሚናገር ወገንና ሕዝብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ይቈረጣሉ፥ ቤቶቻቸውም የጕድፍ መጣያ ይደረጋሉ ብዬ አዝዣለሁ አለ።

3:30b.DAN.003.030የዚያን ጊዜም ንጉሡ ሲድራቅንና ሚሳቅን አብደናጎንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋቸው።

4

4:1b.DAN.004.001ከንጉሡ ከናቡከደነፆር በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ ሰላም ይብዛላችሁ።

4:2b.DAN.004.002ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን አሳያችሁ ዘንድ ወድጃለሁ።

4:3b.DAN.004.003ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።

4:4b.DAN.004.004እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር።

4:5b.DAN.004.005ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ የነበረው አሳቤና የራሴ ራእይ አስጨነቁኝ።

4:6b.DAN.004.006ስለዚህ የሕልሙን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ።

4:7b.DAN.004.007የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፤ ሕልሙንም በፊታቸው ተናገርሁ፥ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም።

4:8b.DAN.004.008በመጨረሻም የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም ሕልሙን ነገርሁት እንዲህም አልሁት።

4:9b.DAN.004.009የሕልም ተርጓሚዎች አለቃ ብልጣሶር ሆይ፥ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ አውቄአለሁና ያለምሁትን የሕልሜን ራእይ ፍቺውንም ንገረኝ።

4:10b.DAN.004.010የራሴ ራእይ በአልጋዬ ላይ ይህ ነበረ፤ እነሆ፥ በምድር መካከል ዛፍ አየሁ፥ ቁመቱም እጅግ ረጅም ነበረ።

4:11b.DAN.004.011ዛፉም ትልቅ ሆነ፥ በረታም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ድረስ ታየ።

4:12b.DAN.004.012ቅጠሉም። የተዋበ ነበረ ፍሬውም ብዙ ነበረ፥ ለሁሉም መብል ነበረበት፤ ከጥላውም በታች የምድር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፥ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።

4:13b.DAN.004.013በአልጋዬም ላይ በራሴ ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ።

4:14b.DAN.004.014በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ። ዛፉን ቍረጡ፥ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፥ ቅጠሎቹንም አራግፉ፥ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊትም ከበታቹ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይሽሹ።

4:15b.DAN.004.015ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፥ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ እድል ፈንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን።

4:16b.DAN.004.016ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት።

4:17b.DAN.004.017ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው።

4:18b.DAN.004.018እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ይህን ሕልም አልሜአለሁ፤ አንተም፥ ብልጣሶር፥ ፍቺውን አስታውቀኝ፥ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ያስታውቁኝ ዘንድ አይችሉምና፤ ነገር ግን የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።

4:19b.DAN.004.019የዚያን ጊዜ ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል አሰበ፥ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ። ብልጣሶር ሆይ፥ ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ አለው። ብልጣሶርም መልሶ አለ። ጌታዬ ሆይ፥ ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን።

4:20b.DAN.004.020ትልቅ የነበረው የበረታውም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ መልኩም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥

4:21b.DAN.004.021ቅጠሉም አምሮ የነበረው፥ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፤ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት ያየኸው ዛፍ፤

4:22b.DAN.004.022ንጉሥ ሆይ፥ እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፥ እስከ ሰማይም ደርሶአል፥ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው።

4:23b.DAN.004.023ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና። ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፈንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፤ ንጉሥ ሆይ፥ ፍቺው ይህ ነው፤

4:24b.DAN.004.024በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤

4:25b.DAN.004.025ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፥ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል።

4:26b.DAN.004.026የዛፉንም ጉቶ ይተዉት ዘንድ ማዘዙ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ ካወቅህ በኋላ መንግሥትህ ይቆይልሃል።

4:27b.DAN.004.027ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር።

4:28b.DAN.004.028ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ።

4:29b.DAN.004.029ከአሥራ ሁለት ወር በኋላ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ይመላለስ ነበር።

4:30b.DAN.004.030ንጉሡም። ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን? ብሎ ተናገረ።

4:31b.DAN.004.031ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ ወደቀና። ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ። መንግሥት ከአንተ ዘንድ አለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤

4:32b.DAN.004.032ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው።

4:33b.DAN.004.033በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ ንስር፥ ጥፍሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፥ እንደ በሬም ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

4:34b.DAN.004.034ዘመኑም ከተፈጸመ በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዓይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፥ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፥ ለዘላለምም የሚኖረውን አመሰገንሁ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና።

4:35b.DAN.004.035በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚከለክላት ወይም። ምን ታደርጋለህ? የሚለው የለም።

4:36b.DAN.004.036በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፥ ለመንግሥቴም ክብር ግርማዬና ውበቴ ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቶቼም ፈለጉኝ፥ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፥ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ።

4:37b.DAN.004.037አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።

5

5:1b.DAN.005.001ንጉሡ ብልጣሶር ለሺህ መኳንንቶቹ ትልቅ ግብዣ አደረገ፥ በሺሁም ፊት የወይን ጠጅ ይጠጣ ነበር።

5:2b.DAN.005.002ብልጣሶርም የወይን ጠጅ በቀመሰ ጊዜ ንጉሡና መኳንንቶቹ ሚስቶቹና ቁባቶቹ ይጠጡባቸው ዘንድ። አባቴ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ ያመጣቸውን የወርቁንና የብሩን ዕቃዎች አምጡ ብሎ አዘዘ።

5:3b.DAN.005.003የዚያን ጊዜም በኢየሩሳሌም ከነበረው ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጡትን የወርቁን ዕቃዎች አመጡ፤ ንጉሡና መኳንንቶቹም ሚስቶቹና ቁባቶቹም ጠጡባቸው።

5:4b.DAN.005.004የወይን ጠጅም እየጠጡ ከወርቅና ከብር ከናስና ከብረት ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት አመሰገኑ።

5:5b.DAN.005.005በዚያም ሰዓት የሰው እጅ ጣቶች ወጥተው በንጉሡ ቤት በተለሰነው ግንብ ላይ በመቅረዙ አንጻር ጻፉ፤ ንጉሡም የሚጽፉትን ጣቶች አየ።

5:6b.DAN.005.006የዚያን ጊዜም የንጉሡ ፊት ተለወጠበት፥ አሳቡም አስቸገረው፥ የወገቡም ጅማቶች ተፈቱ፥ ጕልበቶቹም ተብረከረኩ።

5:7b.DAN.005.007ንጉሡም አስማተኞቹንና ከለዳውያኑን ቃላተኞቹንም ያገቡ ዘንድ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ንጉሡም የባቢሎንን ጠቢባን። ይህን ጽሕፈት ያነበበ ፍቺውንም ያሳየኝ ሐምራዊ ግምጃ ይለብሳል፥ የወርቅም ማርዳ በአንገቱ ዙርያ ይሆንለታል፥ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ ይሆናል ብሎ ተናገረ።

5:8b.DAN.005.008የዚያን ጊዜም የንጉሡ ጠቢባን ሁሉ ገቡ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ያነብቡ፥ ፍቺውንም ለንጉሡ ያስታውቁ ዘንድ አልቻሉም።

5:9b.DAN.005.009ንጉሡም ብልጣሶር እጅግ ደነገጠ፥ ፊቱም ተለወጠበት፥ መኳንንቶቹም ተደናገጡ።

5:10b.DAN.005.010ንግሥቲቱም ስለ ንጉሡና ስለ መኳንንቱ ቃል ወደ ግብዣ ቤት ገባች፤ ንግሥቲቱም ተናገረች እንዲህም አለች። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ፤ አሳብህ አያስቸግርህ፥ ፊትህም አይለወጥ።

5:11b.DAN.005.011የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ሰው በመንግሥትህ ውስጥ አለ፤ በአባትህም ዘመን እንደ አማልክት ጥበብ ያለ ጥበብና ማስተዋል እውቀትም ተገኘበት፤ አባትህ ንጉሡ ናቡከደነፆር የሕልም ተርጓሚዎችና የአስማተኞች የከለዳውያንና የቃላተኞች አለቃ አደረገው።

5:12b.DAN.005.012መልካም መንፈስ፥ እውቀትም፥ ማስተዋልም፥ ሕልምንም መተርጐም፥ እንቈቅልሽንም መግለጥ፥ የተቋጠረውንም መፍታት ንጉሡ ስሙን ብልጣሶር ብሎ በሰየመው በዳንኤል ዘንድ ተገኝቶአልና። አሁንም ዳንኤል ይጠራ፥ እርሱም ፍቺውን ያሳያል።

5:13b.DAN.005.013የዚያን ጊዜም ዳንኤል ወደ ንጉሡ ፊት ገባ፤ ንጉሡም ተናገረው ዳንኤልም እንዲህ አለው። ንጉሡ አባቴ ከይሁዳ ከማረካቸው ከይሁዳ ምርኮኞች የሆንህ ዳንኤል አንተ ነህን?

5:14b.DAN.005.014የአማልክት መንፈስ እንዳለብህ፥ እውቀትና ማስተዋልም መልካምም ጥበብ እንደ ተገኘብህ ስለ አንተ ሰምቻለሁ።

5:15b.DAN.005.015አሁንም ይህን ጽሕፈት ያነብቡ ዘንድ፥ ፍቺውንም ያስታውቁኝ ዘንድ ጠቢባንና አስማተኞች ወደ እኔ ገብተው ነበር፤ ነገር ግን የነገሩን ፍቺ ያሳዩ ዘንድ አልቻሉም።

5:16b.DAN.005.016አንተ ግን ፍቺን ትሰጥ ዘንድ፥ የተቋጠረንም ትፈታ ዘንድ እንድትችል ሰምቻለሁ፤ አሁንም ጽሕፈቱን ታነብብ ዘንድ፥ ፍቺውንም ታስታውቀኝ ዘንድ ብትችል፥ ሐምራዊ ግምጃ ትለብሳለህ፥ የወርቅም ማርዳ በአንገትህ ዙሪያ ይሆንልሃል፥ አንተም በመንግሥት ላይ ሦስተኛ ገዥ ትሆናለህ።

5:17b.DAN.005.017የዚያን ጊዜም ዳንኤል መለሰ በንጉሡም ፊት እንዲህ አለ። ስጦታህ ለአንተ ይሁን፥ በረከትህንም ለሌላ ስጥ፤ ነገር ግን ጽሕፈቱን ለንጉሡ አነብባለሁ ፍቺውንም አስታውቃለሁ።

5:18b.DAN.005.018ንጉሥ ሆይ፥ ልዑል አምላክ ለአባትህ ለናቡከደነፆር መንግሥትንና ታላቅነትን ክብርንና ግርማን ሰጠው።

5:19b.DAN.005.019ስለ ሰጠው ታላቅነት ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ በፊቱ ይንቀጠቀጡና ይፈሩ ነበር፤ የፈቀደውን ይገድል፥ የፈቀደውንም በሕይወት ያኖር ነበር፤ የፈቀደውንም ያነሣ፥ የፈቀደውንም ያዋርድ ነበር።

5:20b.DAN.005.020ልቡ ግን በታበየ በኵራትም ያደርግ ዘንድ መንፈሱ በጠነከረ ጊዜ፥ ከመንግሥቱ ዙፋን ተዋረደ፥ ክብሩም ተለየው።

5:21b.DAN.005.021ልዑል አምላክም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ የሚወድደውንም እንዲሾምበት እስኪያውቅ ድረስ ከሰው ልጆች ተይለቶ ተሰደደ፥ ልቡም እንደ አውሬ ልብ ሆነ፥ መኖሪያውም ከምድረ በዳ አህዮች ጋር ነበረ፤ እንደ በሬ ሣር በላ፥ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።

5:22b.DAN.005.022ብልጣሶር ሆይ፥ አንተ ልጁ ስትሆን ይህን ሁሉ እያወቅህ በሰማይ ጌታ ላይ ኰራህ እንጂ ልብህን አላዋረድህም።

5:23b.DAN.005.023የመቅደሱንም ዕቃዎች በፊትህ አመጡ፥ አንተም መኳንንትህም ሚስቶችህም ቁባቶችህም የወይን ጠጅ ጠጣችሁባቸው፤ ከብርና ከወርቅም ከናስና ከብረትም ከእንጨትና ከድንጋይም የተሠሩትን የማያዩትንም የማይሰሙትንም የማያውቁትንም አማልክት አመሰገንህ፤ ትንፋሽህንና መንገድህን ሁሉ በእጁ የያዘውን አምላክ አላከበርኸውም።

5:24b.DAN.005.024ስለዚህም እነዚህ የእጅ ጣቶች ከእርሱ ዘንድ ተልከዋል፤ ይህም ጽሕፈት ተጽፎአል።

5:25b.DAN.005.025የተጻፈውም ጽሕፈት። ማኔ ቴቄል ፋሬስ ይላል።

5:26b.DAN.005.026የነገሩም ፍቺ ይህ ነው፤ ማኔ ማለት፥ እግዚአብሔር መንግሥትህን ቈጠረው ፈጸመውም ማለት ነው።

5:27b.DAN.005.027ቴቄል ማለት፥ በሚዛን ተመዘንህ፥ ቀልለህም ተገኘህ ማለት ነው።

5:28b.DAN.005.028ፋሬስ ማለት፥ መንግሥትህ ተከፈለ፥ ለሜዶንና ለፋርስ ሰዎችም ተሰጠ ማለት ነው።

5:29b.DAN.005.029የዚያን ጊዜም ብልጣሶር ለዳንኤል ሐምራዊ ግምጃ እንዲያለብሱት፥ የወርቅ ማርዳም በአንገቱ ዙሪያ እንዲያደርጉለት አዘዘ፤ በመንግሥትም ላይ ሦስተኛ ገዥ እንዲሆን አዋጅ አስነገረ።

5:30b.DAN.005.030በዚያ ሌሊት የከለዳውያን ንጉሥ ብልጣሶር ተገደለ።

5:31b.DAN.005.031ሜዶናዊውም ዳርዮስ መንግሥቱን ወሰደ፤ ዕድሜውም ስድሳ ሁለት ዓመት ነበረ።

6

6:1b.DAN.006.001ዳርዮስም በመንግሥቱ ሁሉ ዘንድ እንዲሆኑ መቶ ሀያ መሳፍንት በመንግሥቱ ላይ ይሾም ዘንድ ወደደ።

6:2b.DAN.006.002መሳፍንቱም ሒሳቡን ያመጡላቸው ዘንድ፥ ንጉሡም እንዳይጐዳ ሦስት አለቆች በላያቸው አደረገ፤ ከእነርሱም አንደኛው ዳንኤል ነበረ።

6:3b.DAN.006.003ዳንኤልም መልካም መንፈስ ስላለው ከአለቆችና ከመሳፍንት በለጠ፤ ንጉሡም በመንግሥቱ ሁሉ ላይ ይሾመው ዘንድ አሰበ።

6:4b.DAN.006.004የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፤ ነገር ግን የታመነ ነበረና፥ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም።

6:5b.DAN.006.005እነዚያም ሰዎች። ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ።

6:6b.DAN.006.006የዚያን ጊዜም አለቆቹና መሳፍንቱ ወደ ንጉሡ ተሰብስበው እንዲህ አሉት። ንጉሥ ዳርዮስ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።

6:7b.DAN.006.007የመንግሥቱ አለቆች ሁሉ ሹማምቶችና መሳፍንት አማካሪዎችና አዛዦች። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፥ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ ይጣል የሚል የንጉሥ ሕግና ብርቱ ትእዛዝ ይወጣ ዘንድ ተማከሩ።

6:8b.DAN.006.008አሁንም፥ ንጉሥ ሆይ፥ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ፥ እንዳይለወጥ ትእዛዙን አጽና፥ ጽሕፈቱንም ጻፍ።

6:9b.DAN.006.009ንጉሡም ዳርዮስ ጽሕፈቱንና ትእዛዙን ጻፈ።

6:10b.DAN.006.010ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጕልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።

6:11b.DAN.006.011እነዚያም ሰዎች ተሰብስበው ዳንኤል በአምላኩ ፊት ሲጸልይና ሲለምን አገኙት።

6:12b.DAN.006.012ወደ ንጉሡም ቀርበው ስለ ንጉሡ ትእዛዝ። ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ በቀር እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ከአምላክ ወይም ከሰው የሚለምን ሰው ሁሉ በአንበሶች ጕድጓድ ውስጥ እንዲጣል ትእዛዝ አልጻፍህምን? አሉት። ንጉሡም መልሶ። ነገሩ እንደማይለወጠው እንደ ሜዶንና እንደ ፋርስ ሕግ እውነት ነው አላቸው።

6:13b.DAN.006.013የዚያን ጊዜም በንጉሡ ፊት መልሰው። ንጉሥ ሆይ፥ ከይሁዳ ምርኮኞች የሆነው ዳንኤል በየዕለቱ ሦስት ጊዜ ልመናውን ይለምናል እንጂ አንተንና የጻፍኸውን ትእዛዝ አይቀበልም አሉት።

6:14b.DAN.006.014ንጉሡም ይህን ቃል በሰማ ጊዜ በጣም አዘነ፥ ያድነውም ዘንድ ልቡን ወደ ዳንኤል አደረገ፤ ሊያድነውም ፀሐይ እስኪገባ ድረስ ደከመ።

6:15b.DAN.006.015የዚያን ጊዜም እነዚያ ሰዎች ወደ ንጉሡ ተሰብስበው ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ንጉሡ ያጸናው ትእዛዝ ወይም ሥርዓት ይለወጥ ዘንድ እንዳይገባ የሜዶንና የፋርስ ሕግ እንደ ሆነ እወቅ አሉት።

6:16b.DAN.006.016የዚያን ጊዜም ንጉሡ አዘዘ፥ ዳንኤልንም አምጥተው በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉት፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ እርሱ ያድንህ አለው።

6:17b.DAN.006.017ድንጋይም አምጥተው በጕድጓዱ አፍ ላይ ገጠሙበት፤ ንጉሡም በዳንኤል ላይ የተደረገው እንዳይለወጥ በቀለበቱና በመኳንንቱ ቀለበት አተመው።

6:18b.DAN.006.018ንጉሡም ወደ ቤቱ ሄደ ሳይበላም አደረ፤ መብልም አላመጡለትም፥ እንቅልፉም ከእርሱ ራቀ።

6:19b.DAN.006.019በነጋውም ንጉሡ ማልዶ ተነሣ፥ ፈጥኖም ወደ አንበሶች ጕድጓድ ሄደ።

6:20b.DAN.006.020ወደ ጕድጓዱም ወደ ዳንኤል በቀረበ ጊዜ በኀዘን ቃል ጠራው፤ ንጉሡም ተናገረ ዳንኤልንም። የሕያው አምላክ ባሪያ ዳንኤል ሆይ፥ ሁልጊዜ የምታመልከው አምላክህ ከአንበሶች ያድንህ ዘንድ ችሎአልን? አለው።

6:21b.DAN.006.021ዳንኤልም ንጉሡን። ንጉሥ ሆይ፥ ሺህ ዓመት ንገሥ።

6:22b.DAN.006.022በፊቱ ቅንነት ተገኝቶብኛልና፥ በአንተም ፊት ደግሞ፥ ንጉሥ ሆይ፥ አልበደልሁምና አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ፥ እነርሱም አልጐዱኝም አለው።

6:23b.DAN.006.023የዚያን ጊዜም ንጉሡ እጅግ ደስ አለው፥ ዳንኤልንም ከጕድጓዱ ያወጡት ዘንድ አዘዘ፤ ዳንኤልም ከጕድጓድ ወጣ፥ በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።

6:24b.DAN.006.024ንጉሡም አዘዘ፥ ዳንኤልንም የከሰሱ እነዚያን ሰዎች አመጡአቸው፥ እነርሱንና ልጆቻቸውንም ሚስቶቻቸውንም በአንበሶች ጕድጓድ ጣሉአቸው፤ ወደ ጕድጓዱም መጨረሻ ሳይደርሱ አንበሶች ያዙአቸው አጥንታቸውንም ሁሉ ሰባበሩ።

6:25b.DAN.006.025የዚያን ጊዜም ንጉሥ ዳርዮስ በምድር ሁሉ ላይ ወደሚኖሩ ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩም ቋንቋ ወደሚናገሩ ሁሉ ጻፈ፥ እንዲህም አለ። ሰላም ይብዛላችሁ።

6:26b.DAN.006.026በመንግሥቴ ግዛት ሁሉ ያሉ ሰዎች በዳንኤል አምላክ ፊት እንዲፈሩና እንዲንቀጠቀጡ አዝዣለሁ፤ እርሱ ሕያው አምላክ ለዘላለም የሚኖር ነውና፤ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው፥ ግዛቱም እስከ መጨረሻ ድረስ ይኖራል።

6:27b.DAN.006.027ያድናል ይታደግማል፥ በሰማይና በምድርም ተአምራትንና ድንቅን ይሠራል፥ ዳንኤልንም ከአንበሶች አፍ አድኖታል።

6:28b.DAN.006.028ይህም ዳንኤል በዳርዮስ መንግሥትና በፋርሳዊው በቂሮስ መንግሥት ኑሮው ተቃናለት።

7

7:1b.DAN.007.001በባቢሎን ንጉሥ በብልጣሶር በመጀመሪያው ዓመት ዳንኤል በአልጋው ላይ ሕልምንና የራሱን ራእይ አየ፤ ከዚያም በኋላ ሕልሙን ጻፈ፥ ዋነኛውንም ነገር ተናገረ።

7:2b.DAN.007.002ዳንኤልም ተናገረ እንዲህም አለ። በሌሊት በራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ አራቱ የሰማይ ነፋሳት በታላቁ ባሕር ላይ ይጋጩ ነበር።

7:3b.DAN.007.003አራትም ታላላቅ አራዊት ከባሕር ወጡ፥ እያንዳንዲቱም ልዩ ልዩ ነበረች።

7:4b.DAN.007.004መጀመሪያይቱ አንበሳ ትመስል ነበር፥ የንስርም ክንፍ ነበራት፤ ክንፎችዋም ከእርስዋ እስኪነቀሉ ድረስ አይ ነበር፥ ከምድርም ከፍ ከፍ ተደረገች፥ እንደ ሰውም በሁለት እግር እንድትቆም ተደረገች፥ የሰውም ልብ ተሰጣት።

7:5b.DAN.007.005እነሆም፥ ሁለተኛይቱ ድብ የምትመስል ሌላ አውሬ ነበረች፥ በአንድ ወገንም ቆመች፥ ሦስትም የጐድን አጥንቶች በአፍዋ ውስጥ በጥርስዋ መካከል ነበሩ፤ እንደዚህም። ተነሥተሽ እጅግ ሥጋ ብዪ ተባለላት።

7:6b.DAN.007.006ከዚህም በኋላ፥ እነሆ፥ ነብር የምትመስል በጀርባዋም ላይ አራት የወፍ ክንፎች የነበሩአት ሌላ አውሬ አየሁ፤ ለአውሬይቱም አራት ራሶች ነበሩአት፥ ግዛትም ተሰጣት።

7:7b.DAN.007.007ከዚህም በኋላ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የምታስፈራና የምታስደነግጥ እጅግም የበረታች፥ ታላላቅም የብረት ጥርሶች የነበሩአት አራተኛ አውሬ ነበረች፤ ትበላና ታደቅቅ ነበር፥ የቀረውንም በእግርዋ ትረግጥ ነበር፤ ከእርስዋም በፊት ከነበሩት አራዊት ሁሉ የተለየች ነበረች፤ አሥር ቀንዶችም ነበሩአት።

7:8b.DAN.007.008ቀንዶችንም ተመለከትሁ፤ እነሆም፥ በመካከላቸው ሌላ ትንሽ ቀንድ ወጣ፥ በፊቱም ከቀደሙት ቀንዶች ሦስት ተነቃቀሉ፤ እነሆም፥ በዚያ ቀንድ እንደ ሰው ዓይኖች የነበሩ ዓይኖች በትዕቢትም የሚናገር አፍ ነበሩበት።

7:9b.DAN.007.009ዙፋኖችም እስኪዘረጉ ድረስ አየሁ፥ በዘመናት የሸመገለውም ተቀመጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ፥ የራሱም ጠጕር እንደ ጥሩ ጥጥ ነበረ፤ ዙፋኑም የእሳት ነበልባል ነበረ፥ መንኰራኵሮቹም የሚነድድ እሳት ነበሩ።

7:10b.DAN.007.010የእሳትም ፈሳሽ ከፊቱ ይፈልቅና ይወጣ ነበር፤ ሺህ ጊዜ ሺህ ያገለግሉት ነበር፥ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር፤ ፍርድም ሆነ፥ መጻሕፍትም ተገለጡ።

7:11b.DAN.007.011የዚያን ጊዜም ቀንዱ ይናገረው ከነበረው ከታላቁ ቃል ድምፅ የተነሣ አየሁ፤ አውሬይቱም እስክትገደል፥ አካልዋም እስኪጠፋ ድረስ፥ በእሳትም ለመቃጠል እስክትሰጥ ድረስ አየሁ።

7:12b.DAN.007.012ከቀሩትም አራዊት ግዛታቸው ተወሰደ፤ የሕይወታቸው ዕድሜ ግን እስከ ዘመንና እስከ ጊዜ ድረስ ረዘመ።

7:13b.DAN.007.013በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከሰማይ ደመናት ጋር መጣ በዘመናት ወደ ሸመገለውም ደረሰ፤ ወደ ፊቱም አቀረቡት።

7:14b.DAN.007.014ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ ይገዙለት ዘንድ ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፥ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።

7:15b.DAN.007.015በእኔም በዳንኤል በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ ደነገጠች፥ የራሴም ራእይ አስቸገረኝ።

7:16b.DAN.007.016በዚያም ከቆሙት ወደ አንዱ ቀርቤ ስለዚህ ሁሉ እውነቱን ጠየቅሁት፤ እርሱም ነገረኝ፥ የነገሩንም ፍቺ አስታወቀኝ።

7:17b.DAN.007.017እነዚህ አራቱ ታላላቅ አራዊት ከምድር የሚነሡ አራት ነገሥታት ናቸው።

7:18b.DAN.007.018ነገር ግን የልዑሉ ቅዱሳን መንግሥቱን ይወስዳሉ፥ እስከ ዘላለም ዓለምም መንግሥቱን ይወርሳሉ።

7:19b.DAN.007.019ከዚህም በኋላ ከቀሩት ሁሉ ተለይታ እጅግ ስለምታስፈራው፥ ጥርሶችዋም የብረት ጥፍሮችዋም የናስ ስለሆኑት፥ ስለምትበላውና ስለምታደቅቀው የቀረውንም በእግርዋ ስለምትረግጠው ስለ አራተኛይቱ አውሬ፥

7:20b.DAN.007.020በራስዋም ላይ ስለ ነበሩ ስለ አሥር ቀንዶች፥ በኋላም ስለ ወጣው፥ በፊቱም ሦስቱ ስለ ወደቁ፥ ዓይኖችና ትዕቢት የተናገረ አፍ ስለ ነበሩት፥ መልኩም ከሌሎች ስለ በለጠ ስለ ሌላው ቀንድ እውነቱን ለማወቅ ፈቀድሁ።

7:21b.DAN.007.021እነሆም፥ ያ ቀንድ ከቅዱሳን ጋር ሲዋጋ አየሁ፥

7:22b.DAN.007.022በዘመናት የሸመገለው እስኪመጣ ድረስ፥ ፍርድም ለልዑሉ ቅዱሳን እስኪሰጥ ድረስ፥ ቅዱሳኑም መንግሥቱን የሚወስዱበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ አሸነፋቸውም።

7:23b.DAN.007.023እንዲህም አለ። አራተኛይቱ አውሬ በምድር ላይ አራተኛ መንግሥት ትሆናለች፤ እርሱም ከመንግሥታት ሁሉ የተለየ ይሆናል፥ ምድሪቱንም ሁሉ ይበላል፥ ይረግጣታል ያደቅቃትማል።

7:24b.DAN.007.024አሥሩም ቀንዶች ከዚያ መንግሥት የሚነሡ አሥር ነገሥታት ናቸው፤ ከእነርሱም በኋላ ሌላ ይነሣል፥ እርሱም ከፊተኞች የተለየ ይሆናል፥ ሦስቱንም ነገሥታት ያዋርዳል።

7:25b.DAN.007.025በልዑሉም ላይ ቃልን ይናገራል፥ የልዑልንም ቅዱሳን ይሰባብራል፥ ዘመናትንና ሕግን ይለውጥ ዘንድ ያስባል፤ እስከ ዘመንና እስከ ዘመናት እስከ እኵሌታ ዘመንም በእጁ ይሰጣሉ።

7:26b.DAN.007.026ነገር ግን ፍርድ ይሆናል፥ እስከ ፍጻሜም ድረስ ያፈርሱትና ያጠፉት ዘንድ ግዛቱን ያስወግዱታል።

7:27b.DAN.007.027መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።

7:28b.DAN.007.028የነገሩም ፍጻሜ እስከዚህ ድረስ ነው። እኔም ዳንኤል በአሳቤ እጅግ ተቸገርሁ፥ ፊቴም ተለወጠብኝ፤ ዳሩ ግን ነገሩን በልቤ ጠብቄአለሁ።

8

8:1b.DAN.008.001በመጀመሪያ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ፥ ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፥ ለእኔ ለዳንኤል ራእይ ተገለጠልኝ።

8:2b.DAN.008.002በራእዩም አየሁ፤ ባየሁም ጊዜ በኤላም አውራጃ ባለው በሱሳ ግንብ ነበርሁ፤ በራእዩም አየሁ በኡባል ወንዝም አጠገብ ነበርሁ።

8:3b.DAN.008.003ዓይኔን አንሥቼ አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግ በወንዙ ፊት ቆሞ ነበር፥ ሁለቱም ቀንዶቹ ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፤ አንዱ ግን ከሁለተኛው ከፍ ያለ ነበረ፥ ታላቁም ወደ ኋላው ወጥቶ ነበር።

8:4b.DAN.008.004አውራውም በግ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ፤ አራዊትም ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ አልቻሉም፥ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፤ እንደ ፈቃዱም አደረገ፥ ራሱንም ታላቅ አደረገ።

8:5b.DAN.008.005እኔም ስመለከት፥ እነሆ፥ ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፥ ምድርንም አልነካም፤ ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው።

8:6b.DAN.008.006ሁለትም ቀንድ ወዳለው በወንዝም ፊት ቆሞ ወዳየሁት አውራ በግ መጣ፥ በኃይሉም ቍጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ።

8:7b.DAN.008.007ወደ አውራውም በግ ሲቀርብ አየሁት፤ እርሱም ተመረረበት፥ አውራውንም በግ መታ፥ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፤ አውራውም በግ ሊቋቋመው ኃይል አልነበረውም፥ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፤ አውራውንም በግ ከእጁ ያድነው ዘንድ የሚችል አልነበረም።

8:8b.DAN.008.008አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፤ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፥ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።

8:9b.DAN.008.009ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፥ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ።

8:10b.DAN.008.010እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፤ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም።

8:11b.DAN.008.011እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፤ ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፥ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ።

8:12b.DAN.008.012ሠራዊቱም ከኃጢአት የተነሣ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠው፤ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፥ አደረገም ተከናወነም።

8:13b.DAN.008.013ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፤ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ። ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፥ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኃጢአት የሆነው ራእይ እስከ መቼ ይሆናል? አለው።

8:14b.DAN.008.014እርሱም። እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፤ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ።

8:15b.DAN.008.015እኔም ዳንኤል ራእዩን ባየሁ ጊዜ ማስተዋሉን ፈለግሁ፤ እነሆም፥ የሰው ምስያ በፊቴ ቆሞ ነበር።

8:16b.DAN.008.016በኡባልም ወንዝ መካከል። ገብርኤል ሆይ፥ ራእዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮኸውን የሰውን ድምፅ ሰማሁ።

8:17b.DAN.008.017እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፤ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም። የሰው ልጅ ሆይ፥ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል አለኝ።

8:18b.DAN.008.018ሲናገረኝም ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ፤ እርሱም ዳሰሰኝ ቀጥ አድርጎም አቆመኝ።

8:19b.DAN.008.019እንዲህም አለኝ። እነሆ፥ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፤ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና።

8:20b.DAN.008.020ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው።

8:21b.DAN.008.021አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፤ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው።

8:22b.DAN.008.022እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፥ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፥ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም።

8:23b.DAN.008.023በመንግሥታቸውም መጨረሻ፥ ኃጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፥ እንቈቅልሽን የሚያስተውል ፊተ ጨካኝ ንጉሥ ይነሣል።

8:24b.DAN.008.024ኃይሉም ይበረታል፥ ነገር ግን በራሱ ኃይል አይደለም፤ በድንቅም ያጠፋል፥ ያደርግማል፥ ይከናወንማል፤ ኃያላንንና የቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል።

8:25b.DAN.008.025በመታለሉ ተንኰልን በእጁ ያከናውናል፤ በልቡም ይታበያል፥ ታምነውም የሚኖሩትን ብዙዎችን ያጠፋል፤ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቋቋማል፤ ያለ እጅም ይሰበራል።

8:26b.DAN.008.026የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፤ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ።

8:27b.DAN.008.027እኔም ዳንኤል ተኛሁ፥ አያሌም ቀን ታመምሁ፤ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ የንጉሡን ሥራ እሠራ ነበር፤ ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር፥ የሚያስተውለው ግን አልነበረም።

9

9:1b.DAN.009.001በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያ ዓመት፥

9:2b.DAN.009.002በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል የኢየሩሳሌም መፍረስ የሚፈጸምበትን ሰባውን ዓመት፥ እግዚአብሔር በቃሉ ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረውን የዓመቱን ቍጥር በመጽሐፍ አስተዋልሁ።

9:3b.DAN.009.003ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ።

9:4b.DAN.009.004ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥ ተናዝዤም እንዲህ አልሁ። ጌታ ሆይ፥ ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ፥

9:5b.DAN.009.005ኃጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፋትንም አድርገናል፥ ዐምፀንማል፥ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤

9:6b.DAN.009.006በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን ለአባቶቻችንም ለአገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም።

9:7b.DAN.009.007ጌታ ሆይ፥ ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት አገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው።

9:8b.DAN.009.008ጌታ ሆይ፥ በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው።

9:9b.DAN.009.009በእርሱ ላይ ምንም እንኳ ያመፅን ብንሆን፥ በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን ባኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ምንም እንኳ ባንሰማ፥ ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው።

9:11b.DAN.009.011እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፥ ቃልህንም እንዳይሰሙ ፈቀቅ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኃጢአት ሠርተናልና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላና እርግማን ፈሰሰብን።

9:12b.DAN.009.012እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም።

9:13b.DAN.009.013በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኃጢአታችንም እንመለስ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም።

9:14b.DAN.009.014ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገሩን ጠብቆ በእኛ ላይ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፥ እኛም ቃሉን አልሰማንምና።

9:15b.DAN.009.015አሁንም ሕዝብህን ከግብጽ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ዝና ለአንተ ያገኘህ ጌታ አምላካችን ሆይ፥ ኃጢአትን ሠርተናል፥ ክፋትንም አድርገናል።

9:16b.DAN.009.016ጌታ ሆይ፥ ስለ ኃጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና እንደ ጽድቅህ ሁሉ ቍጣህና መዓትህ ከከተማህ ከኢየሩሳሌም ከቅዱስ ተራራህ እንዲመለስ እለምንሃለሁ።

9:17b.DAN.009.017አሁንም፥ አምላካችን ሆይ፥ የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ፥ በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ።

9:18b.DAN.009.018አምላኬ ሆይ፥ በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዓይንህን ገልጠህ ጥፋታችንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት።

9:19b.DAN.009.019አቤቱ፥ ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ፥ አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ፥ ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።

9:20b.DAN.009.020እኔም ገና ስናገር ስጸልይ፥ በኃጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኃጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ስለምን፥

9:21b.DAN.009.021ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይቼው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ።

9:22b.DAN.009.022አስተማረኝም፥ ተናገረኝም እንዲህም አለ። ዳንኤል ሆይ፥ ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።

9:23b.DAN.009.023አንተ እጅግ የተወደድህ ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ትእዛዝ ወጥቶአል፥ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፥ ራእዩንም አስተውል።

9:24b.DAN.009.024ዓመፃን ይጨርስ፥ ኃጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘላለምን ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል።

9:25b.DAN.009.025ስለዚህ እወቅ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ አለቃው እስከ መሢሕ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ እርስዋም በጭንቀት ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች።

9:26b.DAN.009.026ከስድሳ ሁለት ጊዜ ሰባትም በኋላ መሢሕ ይገደላል፥ በእርሱም ዘንድ ምንም የለም፤ የሚመጣውም አለቃ ሕዝብ ከተማይቱንና መቅደሱን ያጠፋሉ፤ ፍጻሜውም በጐርፍ ይሆናል፥ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል።

9:27b.DAN.009.027እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ጽኑ ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያደርጋል፤ በሱባዔውም እኵሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በርኵሰትም ጫፍ ላይ አጥፊው ይመጣል፤ እስከ ተቈረጠውም ፍጻሜ ድረስ መቅሠፍት በአጥፊው ላይ ይፈስሳል።

10

10:1b.DAN.010.001በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ በሦስተኛው ዓመት ብልጣሶር ለተባለው ለዳንኤል ነገር ተገለጠለት፤ ነገሩም እውነት ነበረ፥ እርሱም ታላቅ ጦርነት ነው፤ ነገሩንም አስተዋለ፥ በራእዩም ውስጥ ማስተዋል ተሰጠው።

10:2b.DAN.010.002በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ።

10:3b.DAN.010.003ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም፥ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፥ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም።

10:4b.DAN.010.004ከመጀመሪያውም ወር በሀያ አራተኛው ቀን ጤግሮስ በተባለው በታላቁ ወንዝ አጠገብ ሳለሁ፥ ዓይኔን አነሣሁ፥

10:5b.DAN.010.005እነሆም፥ በፍታ የለበሰውን ጥሩም የአፌዝን ወርቅ በወገቡ ላይ የታጠቀውን ሰው አየሁ።

10:6b.DAN.010.006አካሉም እንደ ቢረሌ ይመስል ነበር፥ ፊቱም እንደ መብረቅ ምስያ ነበረ፥ ዓይኖቹም እንደሚንበለበል ፋና፥ ክንዶቹና እግሮቹም እንደ ጋለ ናስ፥ የቃሉም ድምፅ እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ ነበረ።

10:7b.DAN.010.007እኔም ዳንኤል ብቻዬን ራእዩን አየሁ፥ ከእኔ ጋር የነበሩ ሰዎች ግን ራእዩን አላዩም፤ ነገር ግን ጽኑ መንቀጥቀጥ ወደቀባቸው፥ ሊሸሸጉም ሸሹ።

10:8b.DAN.010.008እኔም ብቻዬን ቀረሁ ይህንም ታላቅ ራእይ አየሁ፤ ኃይልም አልቀረልኝም፥ ደም ግባቴም ወደ ማሸብሸብ ተለወጠብኝ፥ ኃይልም አጣሁ።

10:9b.DAN.010.009የቃሉንም ድምፅ ሰማሁ፤ የቃሉንም ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ።

10:10b.DAN.010.010እነሆም፥ አንዲት እጅ ዳሰሰችኝ፥ በጕልበቴና በእጄም አቆመችኝ።

10:11b.DAN.010.011እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ዳንኤል ሆይ፥ እኔ ዛሬ ወደ አንተ ተልኬአለሁና የምነግርህን ቃል አስተውል፥ ቀጥ ብለህም ቁም አለኝ። ይህንም ቃል ባለኝ ጊዜ እየተንቀጠቀጥሁ ቆምሁ።

10:12b.DAN.010.012እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ አትፍራ፤ ልብህ ያስተውል ዘንድ፥ ሰውነትህም በአምላክህ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረግህበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም ስለ ቃልህ መጥቻለሁ።

10:13b.DAN.010.013የፋርስ መንግሥት አለቃ ግን ሀያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ እነሆም፥ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም ከፋርስ ነገሥታት ጋር በዚያ ተውሁት።

10:14b.DAN.010.014ራእዩም ገና ለብዙ ዘመን ነውና በኋለኛው ዘመን ለሕዝብህ የሚሆነውን አስታውቅህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ።

10:15b.DAN.010.015ይህንም ቃል በተናገረኝ ጊዜ ፊቴን ወደ ምድር አቀረቀርሁ፥ ዲዳም ሆንሁ።

10:16b.DAN.010.016እነሆም፥ የሰው ልጅ የሚመስል ከንፈሬን ዳሰሰኝ፤ የዚያን ጊዜም አፌን ከፍቼ ተናገርሁ በፊቴም ቆሞ የነበረውን። ጌታዬ ሆይ፥ ከራእዩ የተነሣ ሕመሜ መጣብኝ፥ ኃይልም አጣሁ።

10:17b.DAN.010.017ይህ የጌታዬ ባሪያ ከዚህ ከጌታዬ ጋር ይናገር ዘንድ እንዴት ይችላል? አሁንም ኃይል አጣሁ፥ እስትንፋስም አልቀረልኝም አልሁት።

10:18b.DAN.010.018ደግሞ ሰው የሚመስል ዳሰሰኝ፥ አበረታኝም።

10:19b.DAN.010.019እርሱም። እጅግ የተወደድህ ሰው ሆይ፥ አትፍራ፤ ሰላም ለአንተ ይሁን፤ በርታ፥ ጽና አለኝ። በተናገረኝም ጊዜ በረታሁና። አበርትተኸኛልና ጌታዬ ይናገር አልሁ።

10:20b.DAN.010.020እርሱም እንዲህ አለኝ። ወደ አንተ የመጣሁት ስለ ምን እንደ ሆነ፥ ታውቃለህን? አሁንም ከፋርስ አለቃ ጋር እዋጋ ዘንድ እመለሳለሁ፤ እኔም ስወጣ፥ እነሆ፤ የግሪክ አለቃ ይመጣል።

10:21b.DAN.010.021ነገር ግን በእውነት ጽሑፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር ማንም የሚያጸናኝ የለም።

11

11:1b.DAN.011.001እኔም በሜዶናዊ በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር።

11:2b.DAN.011.002አሁንም እውነትን አሳይሃለሁ። እነሆ፥ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፤ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፤ በባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል።

11:3b.DAN.011.003ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፥ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፥ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል።

11:4b.DAN.011.004እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፤ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፤ መንግሥቱ ይነቀላልና፤ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።

11:5b.DAN.011.005የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም አንዱ ይበረታሉ፤ እርሱም ይበረታበታል ይሠለጥንማል፤ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል።

11:6b.DAN.011.006ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ፤ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፤ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፥ እርሱና ክንዱም አይጸናም፤ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ።

11:7b.DAN.011.007ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፤ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፥ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፥ በላያቸውም ያደርጋል፥ ያሸንፍማል።

11:8b.DAN.011.008አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፤ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል።

11:9b.DAN.011.009ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።

11:10b.DAN.011.010ልጆቹም ይዋጋሉ፤ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፤ እርሱም ይመጣል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል፤ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል።

11:11b.DAN.011.011የደቡብም ንጉሥ ይቈጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፤ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፥ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል።

11:12b.DAN.011.012ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፤ አእላፋትንም ይጥላል፥ ነገር ግን አያሸንፍም።

11:13b.DAN.011.013የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ያቆማል፤ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል።

11:14b.DAN.011.014በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፤ ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፤ ነገር ግን ይወድቃሉ።

11:15b.DAN.011.015የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፥ አፈርንም ይደለድላል፥ የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፤ የደቡብም ሠራዊት የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፤ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም።

11:16b.DAN.011.016በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ በፊቱም የሚቆም የለም፤ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፥ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል።

11:17b.DAN.011.017ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፥ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፤ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፤ እርስዋም አትጸናም ለእርሱም አትሆንም።

11:18b.DAN.011.018ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፥ ብዙዎችንም ይወስዳል፤ አንድ አለቃ ግን ስድቡን ይሽራል፥ ስድቡንም በራሱ ላይ ይመልሳል።

11:19b.DAN.011.019ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች ይመልሳል፤ ተሰናክሎም ይወድቃል፥ አይገኝምም።

11:20b.DAN.011.020የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል፤ ነገር ግን በቍጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል።

11:21b.DAN.011.021በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፤ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል።

11:22b.DAN.011.022የሚጐርፍም ሠራዊት ከፊቱ ይወሰዳል፥ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃ ይሰበራሉ።

11:23b.DAN.011.023ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ በተንኰል ያደርጋል፤ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል።

11:24b.DAN.011.024በቀስታ ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፤ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፤ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፤ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን ይፈጥራል።

11:25b.DAN.011.025በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፤ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፤ ነገር ግን አሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም።

11:26b.DAN.011.026መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፤ ሠራዊቱም ይጐርፋል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ።

11:27b.DAN.011.027እነዚህም ሁለት ነገሥታት ክፋትን ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ያስባሉ፥ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ፤ ነገር ግን ፍጻሜው እስከ ተወሰነው ጊዜ ነውና አይከናወንላቸውም።

11:28b.DAN.011.028ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰ ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፤ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል።

11:29b.DAN.011.029በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፤ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም።

11:30b.DAN.011.030የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፤ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል።

11:31b.DAN.011.031ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ።

11:32b.DAN.011.032ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፤ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም።

11:33b.DAN.011.033በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፤ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ።

11:34b.DAN.011.034በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ፤ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ።

11:35b.DAN.011.035እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።

11:36b.DAN.011.036ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፥ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፤ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፥ የተወሰነው ይደረጋልና።

11:37b.DAN.011.037የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፤ ራሱንም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም።

11:38b.DAN.011.038በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፤ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል።

11:39b.DAN.011.039በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፤ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፥ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፥ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል።

11:40b.DAN.011.040በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፤ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፤ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል።

11:41b.DAN.011.041ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፥ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ፤ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ።

11:42b.DAN.011.042እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፥ የግብጽም ምድር አታመልጥም።

11:43b.DAN.011.043በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፤ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል።

11:44b.DAN.011.044ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፤ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል።

11:45b.DAN.011.045ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱስ ተራራ መካከል ይተክላል፤ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፥ ማንም አይረዳውም።

12

12:1b.DAN.012.001በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል።

12:2b.DAN.012.002በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ፤ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።

12:3b.DAN.012.003ጥበበኞቹም እንደ ሰማይ ፀዳል፥ ብዙ ሰዎችንም ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ።

12:4b.DAN.012.004ዳንኤል ሆይ፥ አንተ ግን እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ቃሉን ዝጋ፥ መጽሐፉንም አትም፤ ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፥ እውቀትም ይበዛል።

12:5b.DAN.012.005እኔም ዳንኤል አየሁ፤ እነሆም፥ ሁለት ሌሎች ቆመው ነበር፥ አንዱ በዚህ በወንዙ ዳር፥ ሌላውም በዚያ በወንዙ ዳር።

12:6b.DAN.012.006አንዱም ከወንዙ ውኃ በላይ የነበረውን በፍታም የለበሰውን። የዚህ ድንቅ ፍጻሜ እስከ መቼ ነው? አለው።

12:7b.DAN.012.007ከወንዙም ውኃ በላይ የነበረው በፍታም የለበሰው ሰው ቀኝና ግራ እጁን ወደ ሰማይ አንሥቶ። ለዘመንና ለዘመናት ለዘመንም እኵሌታ ነው፤ የተቀደሰውም ሕዝብ ኃይል መበተን በተጨረሰ ጊዜ ይህ ሁሉ ይፈጸማል ብሎ ለዘላለም ሕያው ሆኖ በሚኖረው ሲምል ሰማሁ።

12:8b.DAN.012.008ሰማሁም ነገር ግን አላስተዋልሁም፤ የዚያን ጊዜም። ጌታዬ ሆይ፥ የዚህ ሁሉ ፍጻሜ ምንድር ነው? አልሁ።

12:9b.DAN.012.009እርሱም እንዲህ አለኝ። ዳንኤል ሆይ፥ ቃሉ እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ነውና ሂድ፤

12:10b.DAN.012.010ብዙ ሰዎች ሰውነታቸውን ያጠራሉ ያነጡማል ይነጥሩማል፤ ክፉዎች ግን ክፋትን ያደርጋሉ፤ ክፉዎችም ሁሉ አያስተውሉም፥ ጥበበኞች ግን ያስተውላሉ።

12:11b.DAN.012.011የዘወትሩም መሥዋዕት ከቀረ ጀምሮ፥ የጥፋትም ርኵሰት ከቆመ ጀምሮ ሺህ ሁለት መቶ ዘጠና ቀን ይሆናል።

12:12b.DAN.012.012የሚታገሥ፥ እስከ ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ አምስት ቀንም የሚደርስ ምስጉን ነው።

12:13b.DAN.012.013አንተ ግን እስከ ፍጻሜው ድረስ ሂድ፤ አንተም ታርፋለህ፥ በቀኑም መጨረሻ በዕጣ ክፍልህ ትቆማለህ።


Holder of rights
Multilingual Bible Corpus

Citation Suggestion for this Object
TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. Daniel (Amharic). Daniel (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8A61-F