Ruth (Amharic)

Ruth (Amharic)

1

1:1b.RUT.001.001እንዲህም ሆነ፤ መሳፍንት ይፈርዱ በነበረ ጊዜ በአገሩ ላይ ራብ ሆነ። አንድ ሰውም ከሚስቱና ከሁለቱ ልጆቹ ጋር በሞዓብ ምድር ሊቀመጥ ከቤተ ልሔም ይሁዳ ተነሥቶ ሄደ።

1:2b.RUT.001.002የሰውዮውም ስም አቤሜሌክ፥ የሚስቱም ስም ኑኃሚን፥ የሁለቱም ልጆች ስም መሐሎንና ኬሌዎን ነበረ፤ የቤተ ልሔም ይሁዳም የኤፍራታ ሰዎች ነበሩ። ወደ ሞዓብም ምድር መጡ በዚያም ተቀመጡ።

1:3b.RUT.001.003የኑኃሚንም ባል አቤሜሌክ ሞተ፤ እርስዋና ሁለቱ ልጆችዋ ቀሩ።

1:4b.RUT.001.004እነርሱም ከሞዓባውያን ሴቶች ሚስት አገቡ፤ የአንዲቱ ስም ዖርፋ የሁለተኛይቱም ስም ሩት ነበረ። በዚያም አሥር ዓመት ያህል ተቀመጡ።

1:5b.RUT.001.005መሐሎንና ኬሌዎንም ሁለቱ ሞቱ፤ ሴቲቱም ከሁለቱ ልጆችዋና ከባልዋ ተለይታ ቀረች።

1:6b.RUT.001.006እርስዋም በሞዓብ ምድር ሳለች እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጐበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው ስለ ሰማች፥ ከሞዓብ ምድር ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች።

1:7b.RUT.001.007እርስዋም ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ከተቀመጠችበት ስፍራ ወጣች፤ ወደ ይሁዳም ምድር ሊመለሱ በመንገድ ሄዱ።

1:8b.RUT.001.008ኑኃሚንም ምራቶችዋን። ሂዱ፥ ወደ እናቶቻችሁም ቤት ተመለሱ፤ በእኔና በሞቱት እንዳደረጋችሁ፥ እግዚአብሔር ቸርነት ያድርግላችሁ።

1:9b.RUT.001.009እግዚአብሔር በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ አለቻቸው። ሳመቻቸውም፤ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው አለቀሱ።

1:10b.RUT.001.010እነርሱም። ከአንቺ ጋር ወደ ሕዝብሽ እንመለሳለን አሉአት።

1:11b.RUT.001.011ኑኃሚንም አለች። ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ለምን ከእኔ ጋር ትሄዳላችሁ? ባሎቻችሁ የሚሆኑ ልጆች በሆዴ አሉኝን?

1:12b.RUT.001.012ልጆቼ ሆይ፥ ተመለሱ፤ ባል ለማግባት አርጅቻለሁና ሂዱ፤ ተስፋ አለኝ ብል፥ ዛሬ ሌሊትስ እንኳ ባል ባገባ፥ ወንዶች ልጆችም ብወልድ፥

1:13b.RUT.001.013እነርሱ እስኪያድጉ ድረስ ትቆያላችሁን? ስለ እነርሱስ ባል ማግባት ትተዋላችሁን? ልጆቼ ሆይ፥ እንዲህ አይደለም፤ የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።

1:14b.RUT.001.014ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው እንደ ገና አለቀሱ፤ ዖርፋም አማትዋን ሳመች፤ ሩት ግን ተጠጋቻት።

1:15b.RUT.001.015ኑኃሚንም። እነሆ፥ ባልንጀራሽ ወደ ሕዝብዋና ወደ አማልክትዋ ተመልሳለች፤ አንቺም ደግሞ ከባልንጀራሽ ጋር ተመለሽ አለቻት።

1:16b.RUT.001.016ሩትም። ወደምትሄጅበት እሄዳለሁና፥ በምታድሪበትም አድራለሁና እንድተውሽ ከአንቺም ዘንድ እንድመለስ አታስቸግሪኝ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፥ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል፤

1:17b.RUT.001.017በምትሞችበትም ስፍራ እሞታለሁ፥ በዚያም እቀበራለሁ፤ ከሞት በቀር አንቺንና እኔን አንዳች ቢለየን እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ እንዲሁም ይጨምርብኝ አለች።

1:18b.RUT.001.018ኑኃሚንም ከእርስዋ ጋር ለመሄድ እንደ ቈረጠች ባየች ጊዜ እርስዋን ከመናገር ዝም አለች።

1:19b.RUT.001.019ሁሉቱም እስከ ቤተ ልሔም ድረስ ሄዱ። ወደ ቤተ ልሔምም በደረሱ ጊዜ የከተማይቱ ሰዎች ሁሉ ስለ እነርሱ። ይህች ኑኃሚን ናትን? እያሉ ተንጫጩ።

1:20b.RUT.001.020እርስዋም። ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ።

1:21b.RUT.001.021በሙላት ወጣሁ፥ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፥ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ? አለቻቸው።

1:22b.RUT.001.022ኑኃሚንም ከእርስዋም ጋር ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ሞዓባዊቱ ምራትዋ ሩት ተመለሱ። የገብስም መከር በተጀመረ ጊዜ ወደ ቤተልሔም መጡ።

2

2:1b.RUT.002.001ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ።

2:2b.RUT.002.002ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን። በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት።

2:3b.RUT.002.003ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋኋኋ ላ በእርሻ ውስጥ ቃረ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች።

2:4b.RUT.002.004እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት።

2:5b.RUT.002.005ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን። ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው።

2:6b.RUT.002.006የአጫጆቹም አዛዥ። ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤

2:7b.RUT.002.007እርስዋም። ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፤ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው።

2:8b.RUT.002.008ቦዔዝም ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ።

2:9b.RUT.002.009ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ አላት።

2:10b.RUT.002.010በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት። እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን? አለችው።

2:11b.RUT.002.011ቦዔዝም። ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ።

2:12b.RUT.002.012እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን አላት።

2:13b.RUT.002.013እርስዋም። ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ አለችው።

2:14b.RUT.002.014በምሳም ጊዜ ቦዔዝ። ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም።

2:15b.RUT.002.015ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን። በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፤

2:16b.RUT.002.016ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም ብሎ አዘዛቸው።

2:17b.RUT.002.017በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ።

2:18b.RUT.002.018ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት።

2:19b.RUT.002.019አማትዋም። ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን አለቻት። እርስዋም። ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት።

2:20b.RUT.002.020ኑኃሚንም ምራትዋን። ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ። ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው አለቻት።

2:21b.RUT.002.021ሞዓባዊቱ ሩትም። ደግሞ። መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ አለኝ አለቻት።

2:22b.RUT.002.022ኑኃሚንም ምራትዋን ሩትን። ልጄ ሆይ፥ ከገረዶቹ ጋር ብትወጪ፥ በሌላም እርሻ ባያገኙሽ መልካም ነው አለቻት።

2:23b.RUT.002.023ሩትም የገብሱና የስንዴው መከር እስኪጨረስ ድረስ ልትቃርም የቦዔዝን ገረዶች ተጠጋች፤ በአማትዋም ዘንድ ትቀመጥ ነበር።

3

3:1b.RUT.003.001አማትዋም ኑኃሚን አለቻት። ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን?

3:2b.RUT.003.002አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል።

3:3b.RUT.003.003እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው።

3:4b.RUT.003.004በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።

3:5b.RUT.003.005ሩትም። የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት።

3:6b.RUT.003.006ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች።

3:7b.RUT.003.007ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች።

3:8b.RUT.003.008መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች።

3:9b.RUT.003.009እርሱም። ማን ነሽ? አለ። እርስዋም። እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው።

3:10b.RUT.003.010ቦዔዝም አላት። ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል።

3:11b.RUT.003.011አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።

3:12b.RUT.003.012የቅርብ ዘመድ መሆኔ እውነት ነው፤ ነገር ግን ከእኔ የቀረበ ዘመድ አለ።

3:13b.RUT.003.013ዛሬ ሌሊት እደሪ፤ ነገም እርሱ ዋርሳ መሆን ቢወድድ መልካም ነው፥ ዋርሳ ይሁን፤ ዋርሳ ሊሆን ባይወድድ ግን፥ ሕያው እግዚአብሔርን እኔ ዋርሳ እሆንሻለሁ፤ እስኪነጋ ድረስ ተኚ።

3:14b.RUT.003.014እስኪነጋም በእግርጌው ተኛች፤ ቦዔዝም። ሴት ወደ አውድማው እንደ መጣች ማንም እንዳያውቅ ብሎ ነበርና ገና ሰውና ሰው ሳይተያይ ተነሣች።

3:15b.RUT.003.015እርሱም። የለበስሽውን ኩታ አምጥተሽ ያዢው አላት፤ በያዘችም ጊዜ ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰፈረላት አሸከማትም።

3:16b.RUT.003.016እርሱም ወደ ከተማይቱ ሄደ። ወደ አማትዋም መጣች፥ አማትዋም። ልጄ ሆይ እንዴት ነሽ? አለቻት፤ እርስዋም ሰውዮው ያደረገላትን ሁሉ ነገረቻት።

3:17b.RUT.003.017ወደ አማትሽ ባዶ እጅሽን አትሂጂ ብሎ ይህን ስድስት መስፈሪያ ገብስ ሰጠኝ አለቻት።

3:18b.RUT.003.018እርስዋም። ልጄ ሆይ፥ ሰውዮው ይህን ነገር ዛሬ እስኪጨርስ ድረስ አያርፍምና ፍጻሜው እስኪታወቅ ድረስ ዝም በዪ አለች።

4

4:1b.RUT.004.001ቦዔዝም ወደ ከተማይቱ በር አደባባይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ። እነሆም፥ ቦዔዝ ስለ እርሱ ይናገር የነበረው የቅርብ ዘመድ ሲያልፍ ቦዔዝ። አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው። እርሱም ቀረብ ብሎ ተቀመጠ። - አንተ ቀርበህ በዚህ ተቀመጥ አለው።

4:2b.RUT.004.002ቦዔዝም ከከተማይቱ ሽማግሌዎች አሥር ሰዎች ጠርቶ። በዚህ ተቀመጡ አላቸው።

4:3b.RUT.004.003እነርሱም ተቀመጡ። ቦዔዝም የቅርብ ዘመዱን። ከሞዓብ ምድር የተመለሰችው ኑኃሚን የወንድማችንን የአቤሜሌክን ጢንጦ ትሸጣለች።

4:4b.RUT.004.004እኔም በዚህ በተቀመጡት በሕዝቤ ሽማግሌዎች ፊት እንድትገዛው አስታውቅህ ዘንድ አሰብሁ። መቤዠት ብትወድድ ተቤዠው፤ መቤዠት ባትወድድ ግን ከአንተ በቀር ሌላ ወራሽ የለምና፥ እኔም ከእአንተ በኋላ ነኝና እንዳውቀው ንገረኝ አለው። እርሱም። እቤዠዋለሁ አለው።

4:5b.RUT.004.005ቦዔዝም። እርሻውን ከኑኃሚን እጅ በምትገዛበት ቀን፥ ለሞተው በርስቱ ስሙን እንድታስነሣለት ከምዋቹ ሚስት ከሞዓባዊቱ ከሩት ደግሞ ትገዛለህ አለ።

4:6b.RUT.004.006የቅርብ ዘመዱም። የራሴን ርስት እንዳላበላሽ መቤዠት አልችልም፤ እኔ መቤዠቱን አልችልምና አንተ ከእኔ መቤዠቱን ውሰደው አለ።

4:7b.RUT.004.007በጥንት ጊዜም፥ ማንም ቢሸጥ ቢለውጥም፥ ነገሩን ለማጽናት ሰው ጫማውን እንዲያወልቅ ለባልንጀራውም እንዲሰጠው በእስራኤል ዘንድ ልማድ ነበረ። ይህም በእስራኤል ምስክር ነበረ።

4:8b.RUT.004.008የቅርብ ዘመዱም ቦዔዝን። አንተ ግዛው አለው፤ ጫማውንም አወለቀ።

4:9b.RUT.004.009ቦዔዝም ሽማግሌዎችንና ሕዝቡን ሁሉ። ለአቤሜሌክና ለኬሌዎን ለመሐሎንም የነበረውን ሁሉ ከኑኃሚን እጅ እንደ ገዛሁ እናንተ ዛሬ ምስክሮች ናችሁ።

4:10b.RUT.004.010ደግሞም የምዋቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል ከአገሩም ደጅ እንዳይጠፋ፥ የምዋቹን ስም በርስቱ ላይ እንዳስነሣ የመሐሎንን ሚስት ሞዓባዊቱን ሩትን ሚስት ትሆነኝ ዘንድ ወሰድሁአት፤ እናንተም ዛሬ ምስክሮች ናችሁ አላቸው።

4:11b.RUT.004.011በከተማይቱ በር አደባባይም የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ሽማግሌዎቹም። እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ይህችን ወደ ቤትህ የምትገባውን ሴት የእስራኤልን ቤት እንደ ሠሩ እንደ ሁለቱ እንደ ራሔልና እንደ ልያ ያድርጋት፤ አንተም በኤፍራታ ባለ ጠጋ ሁን፥ ስምህም በቤተ ልሔም ይጠራ።

4:12b.RUT.004.012ቤትህም እግዚአብሔር ከዚህች ቈንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን አሉት።

4:13b.RUT.004.013ቦዔዝም ሩትን ወሰደ፥ ሚስትም ሆነችው፤ ደረሰባትም፥ እግዚአብሔርም ፅንስ ሰጣት፥ ወንድ ልጅም ወለደች።

4:14b.RUT.004.014ሴቶችም ኑኃሚንን። ዛሬ ዋርሳ ያላሳጣሽ እግዚአብሔር ይባረክ፤ ስሙም በእስራኤል ይጠራ።

4:15b.RUT.004.015ከሰባትም ወንዶች ልጆች ይልቅ ለአንቺ ከምትሻል ከምትወድድሽ ምራት ተወልዶአልና ሰውነትሽን ያሳድሰዋል፥ በእርጅናሽም ይመግብሻል አሉአት።

4:16b.RUT.004.016ኑኃሚንም ሕፃኑን ወሰደች አቀፈችውም፥ ሞግዚትም ሆነችው።

4:17b.RUT.004.017ሴቶችም ጎረቤቶችዋ፥ ለኑኃሚን ወንድ ልጅ ተወለደላት እያሉ ስም አወጡለት፤ ስሙንም ኢዮቤድ ብለው ጠሩት። እርሱም የዳዊት አባት የእሴይ አባት ነው።

4:18b.RUT.004.018የፋሬስም ትውልድ ይህ ነው፤ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፥

4:19b.RUT.004.019ኤስሮምም አራምን ወለደ፥ አራምም አሚናዳብን ወለደ፥

4:20b.RUT.004.020አሚናዳብም ነአሶንን ወለደ፥ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፥

4:21b.RUT.004.021ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፥

4:22b.RUT.004.022ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፥ ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፥ እሴይም ዳዊትን ወለደ።


Holder of rights
Multilingual Bible Corpus

Citation Suggestion for this Object
TextGrid Repository (2025). Amharic Collection. Ruth (Amharic). Ruth (Amharic). Multilingual Parallel Bible Corpus. Multilingual Bible Corpus. https://hdl.handle.net/21.11113/0000-0016-8A28-0